በጌታ ደስ ይበላችሁ

በጌታ ደስ ይበላችሁ ሲል ለምን እንዳለ ማወቁ በጣም ይረዳናል። ሰዎች የሚደሰቱት "ይህ አለን" ብለውና ይህን ያላቸውን ነገር በማሰብና በማሰላሰል ነው። ነቢዩ እንባቆምን በጽሑፉ ስናየው በህይወቱ ሲያስደስቱት የነበሩ ነገሮች ነበሩ።

እነዚህ የሚያስደስቱት ነገሮች ከህይወቱ በጎደሉ ጊዜ የሚደሰትበትን ነገር ሲያስብ ጎድሎበት አየ። በዚህ ጊዜ ነው አንድ ከሁሉ በላይ ሊታሰብ የሚገባውን ነገር የተረዳው፤ ይኸውም እግዚአብሔር። ይህ እግዚአብሔር ወገኑ መሆኑን ሲረዳና ሲያስብ ደስታውም በእርሱ መሆኑን ተረዳው። ይህ እግዚአብሔር ለእንባቆም የመድኃኒቱ አምላክ ነበር።  

ትንቢተ ዕንባቆም  3

17 ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥

18 እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።

19 ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ጳውሎስም ሲናገር ጌታ የደስታ ምንጭ እንደሆነ ተረዳ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፥4 "ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።"

ታዲያ ይህንን እግዚአብሔር እንዴት እንደሰትበታለን? 

ዳዊት ለዚህ መልስ ይሰጠናል። መዝሙረ ዳዊት 77፥3 "እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች።" ዳዊት ሲናገር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የደስታው ምንጭ እግዚአብሔርን ማሰብ ነበር። እግዚአብሔርን ማሰብ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ወገኑ መሆኑን ማሰብ ይህ ትልቁ የነፍስ ደስታ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ደስታቸውን የተለያዩ ቦታ ይፈልጉታል፤ ደስታቸው ግን በመንፈስ ቅዱስ መረዳት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ደስታ ሊፈልቅና ሊወርሰን የሚችለው እግዚአብሔርን በማሰብ ነው። ማሰብ ትልቁ ሚስጥር ነው። ምክንያቱ የምናስበው ነገር ስለሚገዛን።

ሁለተኛውን ሚስጥር እንዲሁ ዳዊት ሲነግረን መዝሙረ ዳዊት 126፥3 "እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን።" አለ። እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ታልቅ ነገር፣ በክርስቶስ የሰራውንና የፈጸመውን ታላቅ ነገር ማየት ይህ ደስታችን ነው። የተደረገልንን መቁጠር የደስታን ምስጋና ከውስጣችን ያፈልቀዋል።

ያለኸው የእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ስለሆነ ከአንተ የሚጠበቀው በዚህ መንግስት ውስጥ ያለውን ደስታ ማንጸባረቅ ነው። 

ወደ ሮሜ ሰዎች 14፥17 "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።"

የእግዚአብሔር ደስታ ወደ አንተ ነው!

 

Print

ይፈልጉ

ይግቡ