የያዕቆብ መልእክት117 በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።

እግዚአብሔር የበጎ ስጦታ ሁሉ ደግሞም የፍጹም በረከት ሁሉ መገኛ ነው። የሚሰጠውም ከማንነቱ የተነሳ ነው፤ ይህም ማንነቱ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር የሆነው አምላክ በሚለዋወጥ ነገር የማይለዋወጥ፤ በሚቀያየርም ሁነት የማይቀያየር ፍጹም የሆነ አምላክ ነው።

የእግዚአብሔር ስጦታ በጎ ነው፤ እግዚአብሔር ክፉን አይሰጥም፤ ከእርሱ ዘንድ ክፉ አይወርድም። ነገር ግን በጎ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ በጎን ነገር ማድረግ ይወዳል። ስለዚህም የበጎነት መገለጫው የሆነውን ልጁን ሰጥቶናል። ስለዚህም የእርሱን በጎነት እናወራለት ዘንድ በልጁ በኩል ልጆቹ አድርጎ ባርኮናል። እግዚአብሔር የሰጠው ትልቁ የበጎነቱ ስጦታ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱንም በማመን ያገኘነው ልጅነት የእግዚአብሔር በጎነት ነው። 1 የጴጥሮስ መልእክት 29 

እግዚአብሔር የባረከንም በረከታችን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ሆነን በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል። ይህም በረከታችን እንከን የማይወጣለት፣ የማይጨመርበት ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሳይሰስት፣ ሳያስለምን፣ ሳያጎድል የባረከን እግዚአብሔር ይባረክ።