የሰው ማንነቱ በምልልሱ ይታወቃል። የምንመላለስበት አካሄድ ደግሞ የመሆናችንና የሆነውን የመረዳታችን ውጤት ነው። ወደ ፊልሞና
1፥6 "የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤" ወደ ኤፌሶን ሰዎች
1፥17 "የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ።"
የእግዚአብሔር ልጆች ትልቁና ዋናው መለያቸው የአባታቸውን ባህሪ መካፈላቸው ነው። 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፥2-3 "የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።" ይህ ባህሪ ደግሞ በራሳቸው ጥረትና ስራ የሚያመጡት ሳይሆን በክርስቶስ ስራ የተቀበሉት ነው። የዮሐንስ ወንጌል 15 "1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።" ከአባታችን ከተካፈልናቸው ባህሪያት ውስጥ አንዱ ፍቅር ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር ተሰጥቶናል። ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥5 "በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።" በመንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህ ፍቅር ፈሶልናል።
ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ፍቅርን ለመቀበል ፍለጋ የሚወጡ ሳይሆን የተሰጣቸውንና የተካፈሉትን ፍቅር ለማወቅ የሚተጉ ናቸው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፥18-19 "ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ።" ይህንን የተሰጠንን ፍቅር ባወቅነው መጠን ደግሞ እንመላለስበታለን።
ስለዚህም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን የምናውቅበት አንዱ መንገድ እንዴት እንደተወደድን ማወቅ ነው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5 1 "እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ 2 ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።" ክርስቶስ የወደደን ራሱን የመአዛ ሽታ የሚሆንን መባና መስዋዕት አድርጎ ነው። ራሱን በመስጠት ወዶናል። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህንን የእግዚአብሔርን ፍቅር በልባችን አፍስሶታል።
ስለዚህም ለክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፍቅር መኖር ባህሪውን መኖር ነው። ፍቅር ባህሪያችን ነው፤ ማንነታችን ነው። ከዚህም የተነሳ በፍቅር መመላለስ እንችላለን። በፍቅር መመላለስ ማለት የምናየውን፣ የምንሰማውን፣ የምንዳስሰውን ሁሉ ከፍቅር የተነሳ ማድረግ ማለት ነው። ፍቅር በእኔ ውስጥ ይራመዳል፣ ፍቅር በእኔ ሆኖ ይሰማል፣ ፍቅር በእኔ ሆኖ ያያል፣ ፍቅር በእኔ ሆኖ ያገለግላል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16፥14 "በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።" በእኔ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ነው። ይህንንም ደግሞ የሚከለክል ህግ የለም። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፥23 እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።