ማቴ. 1፡18 የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። 19 እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። 20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። 21 ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።

ይህ ቃል ስለ እግዚአብሔር ምሪት ይነግረናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰዎች ከለመዱት ስርዓት ውጪ በሆነ መንገድ ነበር። ድንግል ጸነሰች፣ ይህ ደግሞ ተሰምቶ አይታወቅም። ነገር ግን የጸነሰችው ከመንፈስ ቅዱስ ስለነበረ ዮሴፍ እንደ አንድ ሰው ሊቀበለውና ሊረዳው የሚችል አልነበረም።

እግዚአብሔር ይህ አሳቡ ይፈጸም ዘንድ ለዮሴፍ ምሪትን ሰጠው። እግዚአብሔር የመራው ግን ዮሴፍ በሚያውቀውና እንዳሰበው አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ምሪት ከእኛ ሁኔታ በላይ ነው። ነገር ግን ምሪቱ ከእግዚአብሔር ስለሆነ በመታዘዝ በረከቱን እናገኛለን። የእግዚአብሔር ምሪቶች ከእኛ ልምድ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ አመክንዮት በላይ ነቸው፤ እግዚአብሔር ግን መታዘዝን እየሰጠ ወደ ራሱ አሳብ ይወስደናል። 

ትንቢተ ኤርምያስ 29፥11 ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።

ወደ ዕብራውያን 13፥21 በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።