ወደ ዕብራውያን 10
32-33 ነገር ግን ግማሽ በነቀፋና በጭንቅ እንደ መጫወቻ ስለ ሆናችሁ ግማሽም እንዲህ ካሉት ጋር ስለ ተካፈላችሁ፥ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ።34 የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ።
35 እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ።
36 የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።
37 ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤
38 ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።
39 እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።
የዕብራውያን መልዕክት የተጻፈላቸው ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት ነቀፋ፣ በጭንቅ ደግሞ እንደ መጫወቻ ወይም መዘበቻ፣ እርሱም ብቻ ሳይሆን እንዲህ የሆነን የእምነትን ኑሮ ከሚኖሩት ጋር የህይወት ተካፋይነት ነበራቸው። ከዚህም የተነሳ በዚህ እምነታቸው ምክንያት የታሰሩትን እንደ ጳውሎስ ያሉትንም ሰዎች ባላቸው ነገር ሁሉ ያካፍሉና ይረዱ ነበር።
የዕብራዊው ጸሐፊ እየነገራቸው ያለው ነገር ቢኖር እንዲህ ሲያልፉበት የነበረውን ይህን የእምነት ኑሯችሁን እንዲያስቡት ነው። ምክንያቱ እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ከእውነተኛ መረዳት እና ከእምነት የሆነ ድፍረትን ስለ ሰጣቸው ነበር። ይህ ድፍረት ደግሞ ብድራት አለው። ትክክለኛ መረዳት ትክክለኛ ምላሽና ኑሮን ያመጣል።
ከዚህ በፊት ስትሄዱበት የነበረው መልካሙ አካሄዳችሁንና ስታደርጉት የነበረውን እግዚአብሔርን የሚያስደስተውን አኗኗራችሁን አሁንም ቀጥሉት። ምክንያቱም ይህ የምትራመዱት መንገድ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሽ አለው።
ነገር ግን ይህ ድፍረት ጽናትን ይፈልጋል። ይህም ጽናት ደግሞ ወደ ፊት የሚያይ እንጂ የሚያፈገፍግ አይደለም። ወደ ፊት የምናየው ከእግዚአብሔር ቃል በእምነት የሆነን የነፍሳችንን መዳን ነው። ወገንተኝነታችን ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት አይደለም።
ኮንፌሽን፡
- የጻድቅ መንገድ ወደ ፊት እንደሆነ የእኔም መንገድ ወደ ፊትና ወደ ላይ ብቻ ነው።
- እኔ ከሚያፈገፍጉት ወገን አይደለሁም።
- በእኔ ህይወት ጥፋት የለም።
- በእግዚአብሔር ቃል እለት እለት ነፍሴን አድናለሁ፡ ሮሜ. 12፡1-2
- እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠኝም። 2 ጢሞ. 1፡7