የዮሐንስ ወንጌል 17፥17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።
እግዚአብሔር የሚቀድሰን ወይም የሚለየን በቃሉ እውነት ነው። የእግዚአብሔር ቃል እውነት በሰው ልብ ውስጥ ሲያድር የመለየትና የመቀደስ ብቃት አለው።
መዝሙረ ዳዊት 119፥9 ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።
ሰው በራሱ ብቃት መንገዱን መለየትና መቀደስ አይችልም። የእግዚአብሔር ቃል ግን የሰውን አረማመድ ይቀድሳል።
የዮሐንስ ወንጌል 15
1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው።
2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።
3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤
ገበሬው አባቴ ነው፤ እውነተኛውም ግንድ እኔ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም ደግሞ እናንተ ናችሁ።
ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ አባቴ ያጠራዋል። የግሪኩ ትርጉም አባቴ ድጋፍ ይሰጠዋል፤ ያነሳዋል፤ ከግንዱ ጋር ያጣብቀዋል የሚል ትርጉም አለው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በክርስቶስ ያሉትን ደካሞችን አይጥልም፤ ባህሪውና የክርስቶስ የማዳን ስራ ባህርይ ስላልሆነ። እርሱ ወደ እርሱ የመጡትን ከቶ ወደ ውጪ አይጥላቸውም። የዮሐንስ ወንጌል 6፥37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤
ይህንንም ንጽህናና ማጥራት ደግሞ የሚያደርገው በቃሉ ነው። ስለዚህ ነው ቁጥር 3 ላይ "እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤" ያለው።
የእግዚአብሔር ቃል የሰው ልጅ ንጽህናው፤ ቅድስናው፤ ጽድቁ ... ነው።
መዝሙረ ዳዊት
119፥142 ጽድቅህ የዘላለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው።
119፥160 የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህንም ፍርድ ሁሉ ለዘላለም ነው።