ወደ ሮሜ ሰዎች  5:1 "እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤" የላይኛው ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉሙ በክርስቶስ ስለ ጸደቅን ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን የሚል ነው።

ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን የሰጠን በእምነት ያገኘነው የክርስቶስ ጽድቅ ነው። ጽድቅ ማለት ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ያለምንም ክስ የመቅረብ ብቃት ማለት ነው። በክርስቶስ ስራ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅን፣ በዚህ እርቅ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ደግሞ ሰላም አለን። በልጁ በማመን ያገኘነው ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን ሊሰጠን በቂ ነው። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሰላም የተገኘው በእርሱ ስራ ነው እንጂ በእኛ አይደለም። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለህ። የማይናወጥና ለዘላለም የሆነ የእግዚአብሔር ሰላም አለህ። 

ወደ ኤፌሶን ሰዎች  2:13 "አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። 14-15 እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ 16 ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። 17 መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ 18 በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።

ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቃችን፣ ጽድቅንም ያገኘንበት ብቸኛው መንገድ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። በእርሱ ስራ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም ሰላም አለን፤ ይኽም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእኛ ሥራ ወይም ጽድቅ የተነሳ አይደለም።