ከስምህ እና ከተጠራህበት አቅም በላይ እግዚአብሔር እንድትኖር ይፈልጋል። ይህም ደግሞ የሚሆነው እግዚአብሔር በክርስቶስ የሰራልንን ስራ በማመን ብቻ ነው።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 4
9፤ ያቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ፤ እናቱም። በጣር ወልጄዋለሁና ብላ ስሙን። ያቤጽ ብላ ጠራችው።
10፤ ያቤጽም። እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን፤ እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው።
ያቤጽ ስሙ ምንም እንኳን ጣርን ወይም መከራን የሚያስታውስ ቢሆንም፤ አስተዳደጉም በዚህ ስም ተጽእኖ ቢሆንም፤ እግዚአብሔር ግን ከስሙ በላይ የሚገለጥ እንደሆነ ስላወቀና ስላመነ ይባርከው ዘንድ ለመነው። እግዚአብሔርም ደግሞ የለመነውን ሰጠው።
ያቤጽ ከስሙ አቅም በላይ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቅም እንደገባ ሁሉ እኛም ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰራልን ስራ ውጤቶች ነን እንጂ የስማችን፥ የኑሮአችን፥ የቀናችን ውጤቶች አይደለንም። እግዚአብሔር እንድናምን እና እንድናይ የሚፈልገው በክርስቶስ የተሰራልንን ስራ ብቻ ነው።