ዳይመንሽን
እንደ ቤተ ክርስቲያን ወይም እንደ ግለሰብ አዳዲስ ዳይሜንሽኖች በታናናሽ ምልክቶች ይጀምራሉ።
አዲስ ምልክት ካየህ አዲስ ዳይሜንሽን እየተጀመረ ነው ማለት ነው።
እግዚአብሔር ሙሴን በምድረ በዳ ውስጥ እያለ የህዝብ መሪ የሚሆንበትን ስበትና ልምምድ የጀመረው በታናሽ ምልክት ነው። የማያቃጥል እሳት አሳየውና ሳበው። ዘጸ. 3፤1-3
ታናሹን ምልክት ታላቅ ያደረገው ላኪው ነው። ከእግዚአብሔር ይሁን እንጂ ታናሹ ምልክት ታላቅ ነገር ከጀርባው አለው። ወደ አዲስ ዳይሜንሽን መግባት ትፈልጋለህ? ታናናሾቹን ምልክቶች እንደ እግዚአብሔር ቃል ተከተላቸው።
የሉቃስ ወንጌል 2
7 የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።
8 በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።
9 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።
10 መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤
11 ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።
12 ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።
መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ.... ምልክቱ .... በግርግም ተኝቶ
የምልክቱ ታናሽነት ላይስብ ይችላል። ነገር ግን ምልክቱን ሰጪው ታላቅ ነው።
ሰዎችን ሁሉ የሚያድነው ወንጌላችን ለዓለም ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፥18 የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
ትንቢተ ዘካርያስ 4
9 የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10 የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? (Small Beginnings) እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው።
የጀማሪው ታላቅነት የጅማሬውን ታናሽነት ታላቅ ያደርገዋል። የጅማሬውን ታናሽነት ሳይሆን የጀማሪውን ታላቅነት አይተህ በታናሹ ነገር ውስጥ ለሚገለጠው ራስህን ስጥ። የታላላቅ ዳይሜንሽኖች ከጅማሬ የመሞት ትልቁ ምክንያት የመጡበት ወይም የጀመሩበት ታናሽ መንገድ አለመቀበል ነው። ስለዚህ የጀመረውን እግዚአብሔር ታመነው። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1፥6 በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤
መጽናት
ወደ ዕብራውያን
3፥6 እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።
3፥14 የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤
6፥11-12 በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።
10፥36 የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።
ወደ ዕብራውያን
12፥1-2 እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
ጌታ ኢየሱስ ነውርን እንዲንቅ ደግሞም በመስቀል እንዲታገስ ብቃትን የሰጠው ከፊቱ ያለው ደስታ ነው። የተሰጠህ ደስታ ለእግዚአብሔር የመኖር ብቃትህ ነው። እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ስናልፍ፣ በመጽናት እንድናልፍ በጸጋው የሚገልጠው ነገር ቢኖር የእርሱን ደስታ ነው።
የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችን ነው።መጽሐፈ ነህምያ 8፥10 እርሱም፦ ሂዱ፥ የሰባውንም ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው ፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ አላቸው።
እዝራ ህጉን እያነበበላቸው እያለ ለቅሶን ያለቅሱ ነበር። ነገር ግን ነህምያ ተነስቶ ሂዱ፤ ዘሬ የኃዘን ቀን ሳይሆን የደስታ ቀን ነው የእግዚአብሔር ቃል ሲለቀቅልህ ለደስታህ ነው።
መዝሙረ ዳዊት 119፥162 ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። እንደ ዳዊት የምርኮን ደስታ የሚያውቅ የለም፤ ስለዚህ በቃሉ እጅግ ደስ አለው።
ሰው በእግዚአብሔር ደስታ ውስጥ ሲኖር በጥንካሬ፤ በጉልበት፤ በኃይል ይኖራል። የእግዚአብሔር ደስታ አኗኗርህን ይቀይረዋል።
ወደ ሮሜ ሰዎች 4፥17 የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።
በመንፈስ የተቀበልነው ደስታ የእግዚአብሔር የራሱን ደስታ ነው።
የማቴዎስ ወንጌል 25፥21 ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
የእግዚአብሔር የራሱ ደስታ በመንፍስ ቅዱስ በልባችን ፈሷል። የማይነገር ደስታ በልባችን አለ። ዝም ብሎ ደስ የሚለው የእግዚአብሔር ደስታ አለን። የእግዚአብሔር ደስታ በነገርህ ወይም በሁኔታህ ላይ የተደገፈ ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሔር ላይ ነው።
ትንቢተ ኢሳይያስ 61
1 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ
ልኮኛል።
2 የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፤
3 እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ
እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል።
4 ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።
5 መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይም ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል።
6 እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፥ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በክብራቸውም ትመካላችሁ።
7 በእፍረታችሁ ፋንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፥ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፈንታችሁ ደስ ይላቸዋል፤ ስለዚህ በምድራቸው ሁሉ እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘላለምም ደስታ ይሆንላቸዋል።
ከእግዚአብሔር መንፈስ የተነሳ የዘላለም ደስታ ሆኖልኃል። የእግዚአብሔር መንፈስ በኃፍረትህ ፈንታ፣ በውርደትህ ፈንታ የደስታን ዘይት ሰጥቶኃል፤ የዘላለም ደስታ ለአንተ ነው።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፥12 ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።
ለመጽናትህና ለመታገስህ ትልቁ ምክንያት ደስታህ ነው። ከደስታ ጋር ትጸናለህ፣ ከደስታ ጋር ትታገሳለህ፣ ከደስታ ጋር ትበረታለህ
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1
3-5 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት
በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።
6-7 በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂ
ት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
8-9 እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
3፥1 በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።
4፥4 ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።
4፥10 ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር።
በጌታ ደስ ይበላችሁ ሲል ለምን እንዳለ ማወቁ በጣም ይረዳናል። ሰዎች የሚደሰቱት "ይህ አለን" ብለውና ይህን ያላቸውን ነገር በማሰብና በማሰላሰል ነው። ነቢዩ እንባቆምን በጽሑፉ ስናየው በህይወቱ ሲያስደስቱት የነበሩ ነገሮች ነበሩ። እነዚህ የሚያስደስቱት ነገሮች ከህይወቱ በጎደሉ ጊዜ የሚደሰትበትን ነገር ሲያስብ ጎድሎበት አየ። በዚህ ጊዜ ነው አንድ ከሁሉ በላይ ሊታሰብ የሚገባውን ነገር የተረዳው፤ ይኸውም እግዚአብሔር። ይህ እግዚአብሔር ወገኑ መሆኑን ሲረዳና ሲያስብ ደስታውም ደስታውም በእርሱ መሆኑን ተረዳው። ይህ እግዚአብሔር ለእንባቆም የመድኃኒቱ አምላክ ነበር።
ትንቢተ ዕንባቆም 3
17 ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥
18 እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።
19 ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።
ጳውሎስም ሲናገር ጌታ የደስታ ምንጭ እንደሆነ ተረዳ።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፥4 "ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።"
ታዲያ ይህንን እግዚአብሔር እንዴት እንደሰትበታለን? ዳዊት ለዚህ መልስ ይሰጠናል።
መዝሙረ ዳዊት 77፥3 እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች።"
ዳዊት ሲናገር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የደስታው ምንጭ እግዚአብሔርን ማሰብ ነበር። እግዚአብሔርን ማሰብ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ወገኑ መሆኑን ማሰብ ይህ ትልቁ የነፍስ ደስታ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ደስታቸውን የተለያዩ ቦታ ይፈልጉታል፤ ደስታቸው ግን በመንፈስ ቅዱስ መረዳት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ደስታ ሊፈልቅና ሊወርሰን የሚችለው እግዚአብሔርን በማሰብ ነው። ማሰብ ትልቁ ሚስጥር ነው። ምክንያቱ ደግሞ የምናስበው ነገር ስለሚገዛን።
ሁለተኛውን ሚስጥር እንዲሁ ዳዊት ሲነግረን መዝሙረ ዳዊት 126፥3 "እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን።" አለ። እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ታልቅ ነገር፣ በክርስቶስ የሰራውንና የፈጸመውን ታላቅ ነገር ማየት ይህ ደስታችን ነው። የተደረገልንን መቁጠር የደስታን ምስጋና ከውስጣችን ያፈልቀዋል። ያለኸው የእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ስለሆነ ከአንተ የሚጠበቀው በዚህ መንግስት ውስጥ ያለው ደስታ ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፥17 "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።"
የእግዚአብሔር ደስታ ወደ አንተ ነው! መዝሙረ ዳዊት 45፥7 ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።
አንተ በክርስቶስ የጽድቅ ስራ የተነሳ እግዚአብሔር በደስታ ዘይት ቀብቶኃል፤ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ የደስታ ዘይታችን ነው።
አፕሊኬሽን
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡8 ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ 9-10 የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤
ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡1 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። 2 የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።