በመከራ ውስጥ የሚፀና ማንነት
“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” — ዮሐንስ 16፥33።
በአለም ስላለን ብቻ እኛ ክርስቲያኖች መከራ ይደርስብናል ማለቱ ተላላነት ነው፣ በአለም መኖሩ ሳይሆን ክርስቲያን መከራ የመጣበት በአለም ሳለን በእውነት በክርስቶስ ስላለን ነው። በእርግጥ የክርስቶስ ተከታይ ክርስቲያን መባሉ እንዳለ መከራ ቢያመጣም በእርሱ ካለን፣ እንደ ቃሉ ፈቃድ ስንኖር፣ የቃሉን ፈቃድ ስንፈፅም፣ ቃሉን ስንተገብር፣ የኃጢአትን መንገድ ጠልተን በክርስቶስ መንገድ መሄድ በእነዚህ ምክንያት እጅግ የበዛ መከራ መድረሱ አይቀሬ ነው።
በእርግጥ መከራ ፅናትን፣ ትዕግስትን፣ አቋምን የሚፈታተን ቢሆንም በፈተና ውስጥ መፅናቱ የመጨረሻ ዋጋው እጅግ የከበረ ነው። መከራ በዋናነት ከቆምንበት አቋም መጣል አሊያም ማስጣል፣ ከእግዚአብሔርም ጋር የነበረንን ብርቱ ቁርኝትና ግንኙነት ማበላሸት አሊያም ማቋረጥ ነው።
በተለይ የከበረ የእግዚአብሔር እቅድና አላማ ያለበት የሰይጣን ኢላማ የሆነ ሲሆን ይህንን ብርቱ ጉዳይ አለም፣ ሰይጣን እና ስጋውያን ኢላማ አድርገውት መከራን እና ጫናን በማብዛት ሊያስጥሉት ይተጋሉ። መከራ በባህሪው ግፊቱ ከጨለማው አለም ገዢ በሚመጣ ጫና የሚከሰት ሲሆን የመጀመሪያ አላማ አድርጎ የሚነሳው በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖርን፣ በእግዚአብሔር ህግ፣ትዕዛዝ፣ ሥርዓት የሚሄደውን በማስጨነቅ በእርሱ ላይ ያለውን በማስጣል ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ነገር መነጠል ነው።
1- የቀድሞው መከራ
ቀድሞ የነበረው የመከራው አይነት ፊት ለፊት በአካላዊ ጥቃት መከራ መድረስ ሲሆን ይህንንም መከራ የተወጡት በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ጽናት እና አቋም መከራውንና የመከራውን ዘመን ተሻግረውታል።
በተለይ የመከራውን ዘመን የተሻገሩት አንድ ባዩትና በተረዱት እና በገባቸው ብርቱ ጉዳይ ያን ያዩትን ላለማጣት የመከራን ዘመን ድል አድርገው አልፈዋል። በተለይ በሰማይ ከመከራ ድል በኋላ የሚያገኙት እና የሚጠብቃቸውን ሽልማት፣ በሰማይ ሃገር እንዳለ፣ ሥፍራ እንደተዘጋጀላቸው ጠንቅቀው በማወቃቸው የመከራው አይነት እና መብዛት ከሚያገኙት ዘላለማዊ ነገር ጋር ሊወዳደርና ሊነፃፀር እንደማይችል በማወቅ እንደ ተራ፣ ጉድፍ እና ከንቱ፣ ረብ የሌለው እንደሆነ በማወቅ ንቀው፣ ጠልተው ኖረዋል። “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥” — ዕብራውያን 11፥33። “አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።” — ዕብራውያን 11፥16።
መከራ እንዳለ አምኖ መቀበል
በተለይ ጳውሎስ አንድ የገባው፣ ሌሎችንም ሰዎች በገባው መንገድ አብሮ በመጋራት ከእርሱ ጋር እንዲቀጥሉ ይነግር ነበር። "አብረኸኝ መከራ ተቀበል"። አንድ የገባው ነገር ያለው ጳውሎስ በክርስትና እና በክርስቶስ መኖር ምንኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ መከራ ተነጥሎት እንደማይታይ በዋናነት ገብቶታል። ለዚህም ነው ለመንፈሳዊ ልጁአንድ ብርቱ ነገር ያንንም አምኖ እንዲቀበል ያህል የሚነግረው። “እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥8። “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥3።
ለመከራ ራስን ማዘጋጀት
የጳውሎስን ህይወት ስንመለከት ለክርስቶስ እና ለወንጌል ራሱን ማዘጋጀቱ ምን ያህል እንዳመነበት መገለጫ ሲሆን ለዚህም እራሱን በማሳመን ለመጋደል እና መጋደሉ ምን ያህል እንደ ሚያደክመውም ጠንቅቆ ያውቃል። ይህም ብቻ አይደለም ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስም ይህንን የተረዳውን መጋደል እንዳለበት ይነግረዋል። “ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።” — ቆላስይስ 1፥29። “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ።” — 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥12።
2- ዘመነኛው መከራ
ዘመነኛው መከራ ብዙውን ጊዜ ከቁብ የማናስገባው ግን በእጅጉ የክርስትና ህይወታችንን እየሸረሸረ ያለ ዝምተኛ፣ ለዘብተኛ መከራ ግን ያላስተዋልነው የመከራ አይነት ነው። ይህ መከራ እጅግ ወረራ ያለበት እያስደሰተን ነገራችንን የሚነጥቅ፣ ወሳኝ ለሆነ ጉዳይ ጊዜ እንዳይኖረን የሚያደርግ የሚያዘናጋ መከራ ነው። ብዙውን ጊዜ የምንነቃው የክርስትና ህይወታችንና አገልግሎታችን እንደቀድሞው አልሆን ሲለን ነው። መች እንደጎዳን አንነቃም።
ዘመናዊ ወይም ዘመነኛ የክርስትና ፈተና እና መከራ በዛሬው ዘመን ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸውን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ እና ሥነ-ምግባር በእጅጉ የሚያጠቃና መንፈሳዊ እሴቶቻችንን እየጎዳው ነው። ። እነዚህ ፈተናዎች ከጥንት ዘመን በተለየ መልኩ ይታያሉ፣ ግን መሠረታቸው እምነትን ማፍረስ እና ከእግዚአብሔር በእጅጉ ማራቅ ነው።
በተለይ የሚጎዱብን እና የሚጠቁብን መንፈሳዊ አብይ እሴቶቻችን፦
- የእምነት መደከም (Spiritual Weakness)- ዛሬ ብዙ ሰዎች ከመንፈሳዊ ሕይወት ተለይተው ወደ ዓለማዊ ነገሮች በመሄድ እምነታቸው ይደክማል። በተለይ በአለማዊ እሳቤዎች በመሳብ መንፈሳዊ እሴቶችን በእጅጉ ሲጎዳ ዋነኛ ጉዳዮቻችን፦ መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብጊዜ፣ ጸሎት ጊዜ እና የህብረትና የአንድነት ጊዜ እየቀነሰ ነው። አብዛኛው ክርስቲያን የዚህ ነገር ተጠቂ ከመሆኑ የተነሳ የበረታ በመጥፋቱ የደከመውን የሚያበረታ አለመኖሩ በዘመነኞቹ ዘንድ ክርስትና ከብዶ አይታይም። ከታየም የወረት፣ የመርሃ ግብር ጉዳይ ካልሆነ በቀር የክርስትና መንፈሳዊነት በቅጡ በክብር ሲገለጥና ሲታጀብ ባለመታየቱ ከበሬታን የመነፈግ ያህል እየሆነ መጥቷል።
- የዓለም ፍላጎት (Worldliness)- ያልተጎሰመ ስጋ ፍላጎቱ ባለመገደቡ ቁጥጥር ያልተደረገበት የሀብት ፍላጎት፣ ዝና፣ ቅጥ ያጣ የደስታ ፍላጎት እምነትን ይነካል። ያለኝ ይበቃኛልን የማይፈልግ፣ እግዚአብሔርን መምሰልን እጅግ ማትረፊያ እንደሆነ የማይረዳና የማይገነዘብ፣ በመጠን መኖር መርሁ ያልሆነ፣ ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ እሴቶች ይልቅ ዓለማዊ ነገሮችን ሲያስቀድሙ ይታያሉ። በአለም ያለውን መውደድ ምንም ረብ እንደሌለው አለማወቅ አንዱ መከራና ፈተና መሆኑን አለመረዳት የክርስቲያን ፈተና መሆኑን አለማወቅ እየጎዳ ይገኛል። ብዙዎች በዚህ እሳቤ በመጠመድ እና በመተብተብ ስተዋል፣ ከእግዚአብሔርም መንግስት ርቀዋል።
- የሥነ-ምግባር መቀነስ (Moral Decline)- ዛሬ ዓለም ውስጥ የሚታዩ የሥነ-ምግባር መጥፋት ከእግዚአብሔር ሕግ በመራቅ የሚመጣ፣ የእግዚአብሔርን ህግ ቀንና ለሊት አለማሰላሰል ከማሚያመጣው አንደኛው ለዘብተኛ መከራና ፈተና ሆኖ የማናስተውለው ግን ከመድከምና ከመውደቅ በኋላ የምንነቃበት አይነት ነው። በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ከሚታሙበት፣ በሌሎች አለማውያን ዘንድ እንዲህ ከይነት አይተን አናውቅም እስከሚባል ድረስ ያደረሰ እጅግ ክፉ ጉዳይ ነው። (ሐሰት፣ ዝሙት፣ ስርቆት) እንኳን በክርስቲያኖች መካከል እየተገኙ ናቸው።
- የሐሰት ትምህርት (False Teachings)- የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያዛብ ሐሰተኛ ትምህርቶች በብዙ ቦታ ተስፋፍተዋል። ይህም የግል የክርስትና እምነትን እየጎዳ ያለ ነው። የእውቀት ማነስና በእግዚአብሔር ቃል እውነት ላይ ባለመደገፍ፣ ግን ሌሎች በማጣመም በሚገልጡት ከእውነት አፈንግጥ በመሳብ ብዙዎች ስተዋል። ብዙውን ጊዜ የሐሰት ትምህርት ከውጭ ባሉት ዘንድ ብቻ የሚገኝ አድርገን እንጠብቃለን፣ ይህ ስህተት ነ፣ በቅርብ ያለም እንደሚስት እና ሐሰትን እንደሚዘራ ማወቅ አለብን። ብዙውን ጊዜ ለራሳቸው እና ለትምህርታቸው የማይጠነቀቁ የበዙበት ዘመን ይህ ያለንበት እንደሆነ ብዙዎቻችን አንረዳም። ከእውቀት መብዛት አጉል የሚራቀቁና ባልተማሩት ዘንድ እጅግ የተወሳሰበና የተራቀቀ አስተምሮቶች መብዛት፣ ብዙዎች በመምታታ መገኘታቸው በአቋማቸው ላይ እና በእምነታቸው ላይ እርግጠኝነትን በማጣት፣ በምትኩ ጥርጥርን በማጫር እርግጠኝነት በመተው ሸሽተዋል። ከማን መማር እንዳለባቸው እስከመጠራጠር ተደርሷል። ለራሳቸውና ለትምህርታቸው የማይጠነቀቁ የበዙበት ዘመን ነው፣ ይህም አንደኛው መከራ መሆኑንም አለመረዳት ድካም ነው።
- ቴክኖሎጂ እና ማህበራዊ ሚዲያ ማህበራዊ ሚዲያ (Technology and Social Media)- አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ቢሆንም፣ አስተሳሰብን የሚያስቀይር፣ ጊዜን የሚያጠፋ እና ከእግዚአብሔር የሚያርቅ ሊሆን የሚችል ሲሆን በተለይ ጊዜያችንን በእጅጉ በማዘናጋት የሚሰርቁብንና እጅግ ድካምን በመርጨት ለእግዚአብሔር ጊዜ እንዳንሰጥ፣ በዋናነት የክርስትና እሴቶቻችንን በእጅጉ እየጎዳ ያለ የዘመኑ መከራ፣ ፈተና ነው። በዋናነት በእድሜ ደረጃ ያየነው እንደሆነ በጉብዝና የእድሜ ክልል ያለ የዚህ ነገር ተጠቂ፣ እስረኛ-ምርኮኛ ነው።
- መከራና አስጨናቂ ሁኔታዎች- በተለይ አለም፣ የጨለማው ገዢ በዋናነት እየሠራበት ያለ ነገር ቢኖር በአለም የምጣኔ ሐብት አለመረጋጋት ላይ እየሠራው ያለው ነገር በአለም ላይ ላሉ መንግሥታት የእራስ ምታት ቢሆንም በተለይ ክርስቲያኖችም የዚህ ነገር ተጠቂ ቢሆኑም የኢኮኖሚ ችግር በዋናነት በአማራጭ መንገድ መምጣቱ ክርስቲያኖች በማይመች መንገድ መምጣቱና ባለመምረጡ የዚህ መከራ ተጠቂ ይሆናል። በጨለማውን አለም ዘዴ (system) አለመቀበል ለከፋ ድህነት፣ ስራ አጥነት በዳረጉ ለሌላ ለከፋ ችግር መዳረጉ አይቀሬ ነው። ስለዚህ የሚያስጨንቅ ዘመን እንደሚመጣ ከወዲሁ ማወቁ ተገቢ ነው።
- የአንድነት የህብረት እጥረት የህብረት መጥፋት- በህብረት ውስጥ የሚገኝን የታዘዘ በረከት እንዳናገኝ ካደረጉን ዋነኛው እውነተኛ ህብረት መጥፋቱ ነው። ቢኖር እንኳን ህብረት ለማድረግ የውስጥ ፈቃደኝነት ማነስ ለመከራ ዳርጎናል፣ ይህም አንድ መከራ መሆኑን አለመረዳት የውድቀታችን ሰበብ እና ምክንያት ነው። በተለይ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ያለን አነስተኛ አመለካከት ለከፋ ግጭት እና ክፍፍል ምክንያት ሆኖአል። ሆኖም ብቻ ሳይሆን መለያየትን እና መከፋፈልን ለሚመኘው ትልቁ መግቢያ ነው። በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍል፣ ግጭት እና የአንድነት እጥረት ታላቅ ፈተና ነው። በተለይ መጋመድ አለመቻላችን ጎድቶናል። ብዙዎች መለየትን የሚወዱ ምኞታቸውን የሚከተሉ ናቸው።
መፍትሄ እና መንገዶች
- በጸሎት መትጋትና መጽናት፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።” — ማቴዎስ 26፥41።
- መጽሐፍ ቅዱስን መማርና መከታተል፦ “በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።” — ሐዋርያት 18፥24።
- በመንፈሳዊ አንድነት መኖር፦ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” — ኤፌሶን 4፥3።
- ከዓለማዊ ፍላጎት መራቅ፦ “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” — ቲቶ 2፥12-13።
- እውነተኛ ትምህርትን ማሰላሰል፦ “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።” — ሐዋርያት 2፥42። “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” — ቆላስይስ 2፥8። “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥9። በመጨረሻም ዘመናዊ ፈተናዎች ከብዙ አቅጣጫ ቢመጡም፣ ክርስቲያኖች በእምነት በመጽናት እና በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመቆየት ማሸነፍ ይችላሉ። በተሸነፈ አለም ላይ እንዳለን ማወቅ አለብን። ዮሐንስ 16፡33።
አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ
+251902910126