yegizewkal
ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። ትንቢተ ኤርምያስ 15፥16

  • Home/መነሻ ገጽ
  • Gospel Thoughts/የወንጌል አስተምህሮ
    • ነገረ ድነት/Salvation
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
    • Literature/ስነ-ጽሑፍ
    • ከመጽሐፍት ዓለም
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን
    • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Testimony/ምስክርነት
  • ማስታወቂያ/Advertisement
  1. You are here:  
  2. Home
  3. The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
  4. ከመጽሐፍት ዓለም

ከመጽሐፍት ዓለም

የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ከመጽሐፍት ዓለም

የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት 

ዮሐንስ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የሚደረግ ኅብረት በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል። ክርስትና በባህሪው ሁሉን አቀፍ ባለመሆኑ፥ በዓለም ላይ ያሉት ሰዎች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። ስለ እግዚአብሔርና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነቱን የሚያውቁ፥ ከእግዚአብሔር የተወለዱና እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሚመላለሱና የቅድስና፥ የጽድቅና የፍቅር ባህሪውን የሚያንጸባርቁ ሰዎች ብቻ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኛሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑት ግን ድነትን አያገኙም። ይህ በዛሬው ዓለም ውስጥ ወሳኝ እውነት ነው። ሰዎች ሀ) ከሌላ ሃይማኖት ተከታዮች፥ ለ) በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ከሚገኙ ኑፋቄዎችና ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በአእምሮአቸው እያመኑ ተግባራዊ ከሚያደርጉት ሰዎች ጋር በመቻቻል አብረው ለመኖር ይፈልጋሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች፥ «እንዴት አልዳኑም፥ ማለት ይቻላል? ይሄ ሃይማኖታዊ አምባገነናዊነት አይመስልምን? ይህ ሃይማኖታዊ ትዕቢት አይደለምን?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ዮሐንስና ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክርስትና የተለየ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራሉ። እኛ የእግዚአብሔር እውነት አለን ሌሎች ሃይማኖቶች ግን ሰውን የሚያድን እውነት የላቸውም። ሰውን የሚያድነው ሃይማኖታዊ ቅንአት ሳይሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። በሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የትዕቢት ስሜት ሊሰማን አይገባም። ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ልናስገድዳቸውም አይገባም። ነገር ግን ክርስቶስ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት መሆኑን በእርጋታ ልናብራራላቸው ይገባል ( ዮሐ. 14፡6)። ጴጥሮስ እንዳለው «እንድንበት ዘንድ የሚገባ፥ ለሰዎች፥ ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።» (የሐዋ. 4፡12)። እኛ ትክክል የሆነውና እነርሱ የተሳሳቱት ታላላቆች ወይም ከእነርሱ የተሻለ እውቀት ያለን ሰዎች በመሆናችን አይደለም። እግዚአብሔር ብቸኛውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠቅሶታል። እኛም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመናችን ይህንኑ እውነት እናውጃለን። 

Read more: የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት

የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ከመጽሐፍት ዓለም

የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት 

ዮሐንስ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የሚደረግ ኅብረት በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል። ክርስትና በባህሪው ሁሉን አቀፍ ባለመሆኑ፥ በዓለም ላይ ያሉት ሰዎች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። ስለ እግዚአብሔርና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነቱን የሚያውቁ፥ ከእግዚአብሔር የተወለዱና እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሚመላለሱና የቅድስና፥ የጽድቅና የፍቅር ባህሪውን የሚያንጸባርቁ ሰዎች ብቻ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኛሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑት ግን ድነትን አያገኙም።

Read more: የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት

የመጽሐፈ መሳፍንት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ከመጽሐፍት ዓለም

የመጽሐፈ መሳፍንት

መግቢያ

የመጽሐፈ ኢያሱ ታሪክ የደስታና የድል ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች በእርሱ ርዳታ በቃል ኪዳኑ ተስፋ መሠረት ጠላቶቻቸውን አሸንፈው የከነዓንን ምድር ወርሰዋል። እስራኤላውያን በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ለተገባው ቃል ኪዳን ለመታዘዝ የሰጡትን ቃል እንደገና አደሱ። የሚገርመው ግን የዚህ ሕዝብ ታሪክ በድል አልተደመደመም። ታሪኩ በመጽሐፈ መሳፍንት ይቀጥላል።

የመጽሐፈ መሳፍንት ታሪክ የኃዘንና የሽንፈት ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእርሱ ለመታዘዝ እምቢ አሉ። ቃል ኪዳኑንም አላከበሩም፤ ስለዚህ ለቃል ኪዳኑ መታዘዝ እንዳለባቸው ለማስተማር እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እንዲሸነፉ ፈቀደ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስተማርና ለማስጠንቀቅ ችግርንና ሽንፈትን በመሣሪያነት ተጠቀመ። ይህም ሆኖ ግን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መታዘዝን አልተማሩም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለእርሱም ለመታዘዝ የገቡትን ቃል ለመጠበቅ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ያላቸውን የመጀመሪያ ፍቅራቸውን የሚተዉትና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እየቀዘቀዙ የሚሄዱት ለምንድን ነው? ) ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅርና መታዘዝ ሕያውና ጠንካራ አድርገው እንዲጠብቁ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ መሳፍንት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ለ) የመጽሐፉ ዓላማ ምንድን ነው? ሐ) የመጽሐፉ አስተዋጽኦስ ምንድን ነው?

የመጽሐፈ መሳፍንት ርእስ

የዚህ መጽሐፍ ርእስ የተገኘው ከኢያሱ ሞት ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ እስከ ሳኦል ድረስ የነበሩ ጊዜያዊ የአገሪቱ መሪዎች በነበሩ ሰዎች የሥልጣን ስም ነው። እነዚህ መሪዎች መሳፍንት (ፈራጆች) ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፥ ከአስተዳዳሪነት ወይም ከፈራጅነት ይልቅ ሥራቸው ወደ ጦር መሪነት ያደላ ነበር። ለእስራኤላውያን ነፃነትን ለማምጣት እግዚአብሔር በግል የሚመርጣቸውና ኃይልን የሚያስታጥቃቸው ሰዎች ነበሩ። መሳፍንት የእስራኤልን ሕዝብ ከሚያስጨንቁአቸው ጠላቶቻቸው ነፃ ካወጡዋቸው በኋላ በነገዶቻቸው ላይ መጠነኛ የሆነ ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ መሳፍንት ወይም ነፃ አውጪዎች በበርካታ ነገዶች ላይ ሥልጣን የነበራቸው ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን በተወሰኑ ነዶች ላይ ብቻ ሥልጣን የነበራቸው የአካባቢ መሪዎች ነበሩ።

እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ ገዥ የሚሆን መሪን ያላስነሣው ሆን ብሎ ነበር፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ንጉሣቸው ነበርና ነው (መሳ. 8፡23)። የተለያዩት ነገዶች በእግዚአብሔር የሚገዙና በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚገኙ ሕግጋትን በመታዘዝ ሊኖሩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ንጉሣቸው ስለነበር ንጉሥ አያስፈልጋቸውም ነበር። በኋላ በመጽሐፈ ሳሙኤል ውስጥ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን እንደ አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው በጠየቁ ጊዜ ድርጊታቸው በእግዚአብሔር ላይ እንደሚፈጸም ዓመፅ ተቆጥሮባቸው ነበር (1ኛ ሳሙ. 8፡5-8)።

የውይይት ጥያቄ፥

1.   ይህ ከእግዚአብሔርና ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ከሚኖረን ግንኙነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

2.   የሚለየውስ እንዴት ነው?

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ማን እንደሆነና እነዚህ የተለያዩ ተግባራትን አሰባስቦ በአንድ ላይ ያቀናበራቸው ማን እንደሆነ የሚያመለክት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ዓለማውያን ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በማዘግየት በዚህ መልክ የጻፈው ኦሪት ዘዳግምን የጻፈውና ከኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያለውን የታሪክ ዘገባ ያቀናበረው ሰው ነው ይላሉ። ሆኖም ለዚህ ሁሉ አንዳችም ማረጋገጫ የለም።

አይሁድ ጸሐፊው ሳሙኤል ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ይህን በሚመለከት ማረጋገጫ የለንም። በዘመነ መሳፍንት የተለያዩ መሳፍንትን በሚመለከት አጫጭር ታሪኮች ሳይጻፉ አልቀሩም። በኋላ አንድ ጸሐፊ፥ ምናልባትም ሳሙኤል እነዚህን ታሪኮች ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ አቀነባብሮአቸው ይሆናል። 1ኛ ዜና 29፡29 እንደሚናገረው ሳሙኤል፥ ናታንና ጋድ የተባሉት ነቢያት የተለያዩ ታሪኮችን ዘግበዋል። ከብሉይ ኪዳን ጥናት እንደምንረዳው በዚሁ ጊዜ የተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትም ነበሩ። ለምሳሌ፥ የያሻር መጽሐፍ (ኢያሱ 10፡13)፥ የእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (2ኛ ነገ. 15፡31) እና የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (2ኛ ነገ. 16፡19) ይገኛሉ። እንደዚሁም በመሳፍንት መጻሕፍት ውስጥ ንጉሥ አልነበረም የሚለው ቃል ተደጋግሞ መጠቀስ የሚያመለክተን መጽሐፈ መሳፍንት ተቀናብሮ በተጻፈበት ጊዜ በእርግጥም በእስራኤል ላይ የነገሡ ነገሥታት መኖራቸው ነው።

መጽሐፈ መሳፍንትን ማን እንደጻፈው ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም የተጻፈው ግን በ1000 ዓ.ዓ. ገደማ በዳዊት ዘመን እንደነበር መገመት ይቻላል። የመጽሐፈ መሳፍንት ታሪካዊ ሥረ - መሠረት ባለፈው ሳምነት የጸለስጢና ምድር የተለያዩ ትላልቅ መንግሥታት የጦርነት ሜዳ እንደነበረች ተመልክተናል። የከነዓን ምድር ከእነዚህ ትላልቅ መንግሥታት ጋር ከሚተባበሩ ከተለያዩ የከተማ መንግሥታት የተዋቀረች ነበረች። በደቡብ በኩል የሚገኘው ትልቁ መንግሥት ግብፅ ነበር። በሰሜን በኩል በኢያሱና በመሳፍንት ዘመን የነበረው ትልቅ መንግሥት የኬጢያውያን መንግሥት ነበር። እነዚህ ትላልቅ መንግሥታት በጳለስጢና ውስጥ ብዙ ጊዜ ጦርነት ይገጥሙ የነበሩ ቢሆንም፥ ይህ ጦርነት እስራኤላውያንን በከፍተኛ ሁኔታ መንካቱ አጠራጣሪ ነው። እስራኤላውያን የሚኖሩት በተራራማዎቹ ስፍራዎች ነበር እንጂ ከዋናዎቹ የንግድ መተላለፊያዎች አጠገብ አልነበረም። በአብዛኛው መሳፍንት ግብፃውያንም ሆኑ ኬጢያውያን አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ አልቻሉም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓን በየትኛውም መንግሥት ቀጥተኛ በበላይ ተቆጣጣሪነት ሥር አልነበረችም። በዚህም ምክንያት ብዙ ትናንሽ መንግሥታት ከነዓንን ለመቆጣጠር ወይም ለመውረርና አደጋ ለመጣል ይሞክሩ ነበር። ይህ በከነዓን ምድር ላይ የተደረገ ጦርነት በውጤቱ የተለያዩ ሕዝቦች እስራኤላውያንን ለመቆጣጠርና ለመግዛት እንደቻሉ በሚያንፀባርቅ መንገድ በመጽሐፈ መሳፍንት ተገልጧል። ከኢያሱ ሞት ጀምሮ ሳኦል እስከ ነገሠበት ጊዜ ድረስ የነበረው ሁኔታ የተለያዩ መንግሥታት እስራኤልን ያጠቁበትና የጨቆኑበት ዘመን ነበር። በእነዚህ ዓመታት ነበር የባሕር ሕዝቦች ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ፍልስጥኤማውያን በመባል የሚታወቁ አዲስ ነገዶች ወደ ከነዓን የባሕር ዳርቻ ተሰደው የመጡት። ወዲያውኑ አብዛኛውን የከነዓንን ምድር ተቆጣጠሩና ለብዙ ዓመታት የአይሁድ ሕዝብ ዋና ጠላት ሆኑ።

የእስራኤል ሕዝብ የተለያዩ ነገዶች በየራሳቸው ክልል መኖር ከጀመሩ ወዲህ የሕዝቡ አንድነት እየቀነሰ መጣ። በአንድነት እንዲቆዩ የሚያደርግ እንደ ሙሴ ወይም እንደ ኢያሱ ያለ ጠንካራ መሪ አልተገኘም፤ ስለዚህ ጎሰኝነት ወይም የዘር ልዩነት እየጠነከረ መጣና ነገዶቹ በየራሳቸው ሽማግሌዎች ወይም የነገድ አለቆች መተዳደር ጀመሩ። 12ቱን ነገዶች እጅግ በላላ መንገድ (ፈዴራላዊ አስተዳደር) እንዲቆዩ ያደረጉ ሁለት ነገሮች ነበሩ። የመጀመሪያው፥ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የጋራ የሆነ አምልኮአቸው ነበር። የከነዓናውያንን አማልክት ሳይሆን እግዚአብሔርን እስካመለኩ ድረስ የተባበሩ ነበሩ። የእውነተኛውን አምላክ አምልኮ በሚተዉበት ጊዜ የጋራ የሆነ ሃይማኖት አይኖራቸውም ነበር። ሁለተኛው፥ ሁሉም የያዕቆብ ልጆች መሆናቸውና ይኸውም የጋራ ውርስ መያዛቸው ነበር፤ ስለሆነም አንድ ነገድ በውጫዊ ጠላት

በሚጠቃበት ጊዜ ሌሎቹ ነገዶች ለእርዳታ መድረሳቸው የተለመደ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይህንን አንድነት በሚረሱበት ጊዜ በ12ቱ ነገዶች መካከል የሚደረግ ጦርነትም የተለመደ ነበር።

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ስለ ዘመነ መሳፍንት ዝርዝር የሆነ መግለጫ የመስጠት አሳብ አልነበረውም። ለምሳሌ፡- በግብፃውያንና በኬጢያውያን መካከል ስለተደረገ ጦርነት የሚጠቅሰው አንዳችም ነገር የለም። የጸሐፊው ዋና አሳብ በዚህ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ችግር የሥነ - መለኮታዊ ትምህርት ትንተና መስጠት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትኩረት በቀድሞ ዘመናት ሁኔታ ላይ ሰፊ ገለጻ መስጠት ሳይሆን የአይሁድ መጨቆን ለምን እንደሆነ መናገር ነበር።

የዘመነ መሳፍንት የጊዜ ቅደም ተከተል

የመጽሐፈ መሳፍትን የጊዜ ቅደም ተከተልን በተመለከተ ብዙ ክርክርና ጥርጣሬ አለ። ይህም በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው፥ የእስራኤል ሕዝብ ነፃ የወጡበትና ከነዓንን የወረሱበት ጊዜ ጉዳይ በሊቃውንቱ ዘንድ አከራካሪ መሆኑ ነው። ይህ ነገር የሆነው በ15ኛው ክፍለ ዘመን (1400 ዓ.ዓ.)? ነው ወይስ በ13ኛው ክፍል ዘመን (በ1280 ዓ.ዓ.)? ወግ አጥባቂ የሆኑ ምሁራን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መረጃ የሚስማማው ለ15ኛው ክፍለ ዘመን ቀረብ ላለው ጊዜ ነው ወደ ማለት ያዘነብላሉ።

ሁለተኛው ጥያቄ፥ መሳፍንት የገዙት በአንድ ጊዜ ነው ወይስ በተከታታይ? የሚለው ነው። እያንዳንዱ መስፍን የገዛበትን ጊዜ በተናጠል ወስደን ከደመርነው አጠቃላዩ 410 ዓመታት ይመጣል። ሁሉም ምሁራን እንደሚስማሙበት ከሆነ ይህ ጊዜ ለዘመነ መሳፍንት እጅግ ብዙ ነው፤ ስለዚህ እነዚህ የመሳፍንትን ዘመን የምናይባቸው ሁለት አማራጮች አሉን። የመጀመሪያው፥ የእስራኤል ሕዝብ የወጡበትና ሰዎች ማስታወስ ይችሉ ዘንድ ቀላል ለማድረግ የተሰጠ አጠቃላይ ጊዜ ተደርጎ የተሰጠ ነው የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው ግን፥ አንዳንዶቹ መሳፍንት ሌሎቹ መሳፍንት በሌላ ስፍራ በገዙበት ጊዜ የነበሩ የአንድ የተወሰነ ክልል ገዥዎች ነበሩ የሚል ነው። ለምሳሌ፡- ሶሜጋር፥ ቶላ፥ ኦጢር፥ ኢብሃን፥ ኤሉንና አብዶን ሌሎች መሳፍንት በሚገዙበት ጊዜ የተነሡ የአንድ ክልል መሪዎች ነበሩ፤ ስለዚህ የመሳፍንት የጊዜ ቅደም ተከተል በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካለው የጊዜ ቅደም ተከተል ጋር የሚስማማ ነው።

ዘመነ መሳፍንት ከ (1380-1050) ዓ.ዓ. ድረስ 300 ዓመታት ያህል የፈጀ ሳይሆን አይቀርም።

ቀጥሎ ለዘመነ መሳፍንት የተሰጠ የጊዜ ቅደም ተከተል እናገኛለን፡፡

1.   ኢያሱ 1406-1376 ዓ.ዓ.

2.   የሽማግሌዎች አገዛዝ 1376-1366 ዓ.ዓ

3.   የመስጴጦምያ የጭቆና ዘመን 1366-1358 ዓ.ዓ.

4.   የጎቶንያል አገዛዝ የ40 ዓመት ሰላም 1358-1318 ዓ.ዓ.

5.   በሞዓብ የመጨቆን ዘመን 1318-1301 ዓ.ዓ.

6.   የናዖድ አገዛዝና የ80 ዓመት ሰላም 1301-1221 ዓ.ዓ.

7.   በከነዓናውያን የመጨቆን ዘመን 1221-1201 ዓ.ዓ.

8.   የዲቦራና የባርቅ አገዛዝ የ40 ዓመት ሰላም 1201-1161 ዓ.ዓ.

9.   በምድያን የመጨቆን ዘመን 1161-1154 ዓ.ዓ.

10. የጌዴዎን አገዛዝና የ40 ዓመት ሰላም 1154-1114 ዓ.ዓ.

11. የአቤሜሌክ- የ3 ዓመታት ንጉሥ 1114-1111 ዓ.ዓ.

12. የዮፍታሔ አገዛዝ -6 ዓመት 1111-1105 ዓ.ዓ.

13. የሶምሶን አገዛዝ - 20 ዓመት

14. የዔሊ አገዛዝ 1066-1046 ዓ.ዓ.

15. የሳሙኤል አገዛዝ 1046-1026 ዓ.ዓ.

16. የሳኦል አገዛዝ 1026-1011 ዓ.ዓ.

** እነዚህ ጊዜያት በጣም ያልተረጋገጡ እንደሆኑና የተለያዩ ምሁራን መሳፍንት የገዙበት ዘመን ብለው የሚሰጡት ጊዜ የተለያየ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

የመጽሐፈ መሳፍንት አወቃቀርና አስተዋጽኦ

መጽሐፈ መሳፍንት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡-

1.   የዘመነ መሳፍንት መግቢያ (1፡1-3፡6)

2.   የገዙ የተለያዩ መሳፍንት (3፡7-16፡31)

3.   የዘመነ መሳፍንት አጠቃላይ የሥነ - ምግባር ባሕርያት (17-21)

የሚከተለው ጠለቅ ተደርጎ የተዘረዘረ የመጽሐፈ መሳፍንት አስተዋጽኦ ነው፡-

1.   የመጽሐፈ መሳፍንት መግቢያ(1፡1-3፡6)

ሀ. የእስራኤላውያን ከነዓናውያንን የማስወጣት ተግባራቸውን በሚገባ አለማከናወን (1፡1-2፡5)

ለ. የእስራኤል የክሕደት ዑደት መግቢያ (2፡6-3፡6)

2.   ስድስቱ የእስራኤላውያን የክሕደት ዑደቶች «የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ» (3፡7-16፡31)።

2.1.     ጎቶንያል (3፡7-11)

2.2.     ናዖድ (3፡12-31)

2.3.     ዲቦራና ባርቅ (4-5)

2.4.     ጌዴዎን (6-8)

2.5.     አቤሜሌክ (9)

2) ቶላዕና ኢያዕር (10፡1-5)

ሠ. ዮፍታሔ (10፡6-12፡7)

1.   ኢብጻን (12፡8-10)

2.   ኤሎም (12፡11-12)

3.   ዓብዶን (12፡13-15)

4.   ሶምሶን (13-16)

3.   እስራኤላውያን በዘመነ መሳፍንት ያሳዩት የሥዓ-ምግባር ብልሹነት፡- «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (17-21)።

ሀ. የዳን ነገድ ታሪክ (17-18)

ለ. የብንያም ነገድ ታሪክ (19-21)

 

የመጽሐፈ መሳፍንት ዓላማ

እስራኤል በጠላቶችዋ ለምን ተሸነፈች? ያለማቋረጥ በባርነት ውስጥ የሆነችውስ ለምንድን ነው? እስራኤላውያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን የተስፋ ቃል ኪዳን በረከት ያልተለማመዱት ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ሊያድናቸው ስላልቻለ ነውን? የከነዓናውያንና የአሕዛብ አማልክት ብርቱ ስለሆኑ ነውን?

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ለመመለስ የሚሞከራቸው ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው። የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ እስራኤላውያን ያ ሁሉ ሥቃይ የደረሰባቸው ለምን እንደሆነ ሊገልጥላቸው ይፈልግ ነበር። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ እስራኤላውያን ለምን እንደተሸነፉና በመከራ ውስጥ እንደተዘፈቁ የሚያሳዩ ሁለት ምክንያቶች ተሰውረው እናገኛለን፡

1. እስራኤላውያን ብዙ መከራና ችግር የደረሰባቸው ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በታዛዥነት ስላልኖሩ ነው። እግዚአብሔር እንዳልተጠነቀቀላቸው በማሰብ እርሱን ከመውቀስ ይልቅ፥ እስራኤላውያን ለወደቁበት አስጊ ሁኔታ ራሳቸውን ብቻ መውቀስ ነበረባቸው። እውነተኛ ንጉሣቸውን እግዚአብሔርን ትተው፥ የከነዓናውያንን አማልክት፥ ሥነ-ምግባራት፥ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና የአኗኗር ዘይቤዎች ስለተከተሉ እግዚአብሔር እየቀጣቸው ነበር። በኦሪት ዘዳግም እንደተጠቀሰው፥ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን አስከተለባቸው። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደምናነበው «የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረጉ» (መሳ. 2፡11፤ 3፡7፥ 12፤ 4፡1 ወዘተ.)። በመጽሐፈ መሳፍንት የሚገኙት የመጨረሻዎቹ ሁለት ታሪኮች የሚያሳዩት የእግዚአብሔር ሰዎች ምን ያህል ከፍተው እንደነበር ነው።

የሚያሳዝነው የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ ሁሉ በፊቱ የተቀደሰ ኑሮ ከመኖር ወደኋላ ማለታቸው ነው። በዚህ ፈንታ ዓለምን መሰሉ። ውጤቱም በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ማስከተል ሆነ። እግዚአብሔር በረከቱን ከእነርሱ ወሰደ። ወደ እግዚአብሔር መመለስን እምቢ ሲሉ፥ እግዚአብሔር ለምርኮ አሳልፎ ይሰጣቸውና በዓለም እንዲሸነፉ ያደርግ ነበር። ይህም ሆኖ ሳይመለሱ ሲቀሩ፥ እግዚአብሔር ይተዋቸው ነበር። በትንቢተ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ክብር ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን እንዴት እንደተወ እናነባለን (ሕዝ. 10፡ 11፡23)። በአዲስ ኪዳን በጳውሎስ ከተጀመሩት አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስናቸውን ስላጡ በመጨረሻ ተደመሰሱ ወይም ወደ መስጊድነት ተለወጡ፤ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ያለማቋረጥ እርሱን ከተውንና እንደ ዓለም መኖር ከጀመርን እግዚአብሔር እኛንም ይተወናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም ቢሆን ዓለምን የመምሰል አዝማሚያ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው? ለ) በዘመነ መሳፍንት ከነበረው የእስራኤላውያን ታሪክ እንደ ማስጠንቀቂያ ልንወስደው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? ሐ) እኛ ክርስቲያኖች ዓለምን መምሰል እንደሌለብን ለማስተማር መጽሐፈ መሳፍንትን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?

2. እስራኤላውያን ከፍተኛ መከራና ችግር የደረሰባቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን ይጠብቁ ዘንድ የሚያስችላቸው ብቁ መሪ ስላላገኙ ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ኋለኛ ክፍል እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡- «በዚያም ዘመን ከእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳ. 21፡25)። እንደ ጸሐፊው አመለካከት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተሸነፉበትና በኃጢአት የወደቁበት አንዱ ምክንያት ጠንካራ መሪ ወይም የሚመራቸው ንጉሥ ስላልነበራቸው ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ለመጠበቅ የነገድ አመራር በቂ አልነበረም።

መጽሐፈ መሳፍንት የተጻፈው ምናልባት በዳዊት ጊዜ ስለሆነ ጸሐፊው እግዚአብሔርን የሚፈራ ጠንካራ መሪ፥ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ይኖር ዘንድ የሚጫወተውን ከፍተኛ ሚናና የሚሰጠውን ጥቅም ታላቅነት ተመልክቶ ይሆናል። ከኋለኛው ታሪክ እንደምንገነዘበው፥ ንጉሥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ካልሆነ ሕዝቡ ወዲያውኑ እግዚአብሔርን ይተዋሉ። መጽሐፈ ነገሥት የሚያሳየን እስራኤል ነገሥታትን ማግኘቷ ብቻ ቃል ኪዳንን ለመጠበቅና ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ በቂ እንዳልሆነ ነው።

የእስራኤል ዋና ችግር ለሰማያዊ ንጉሥዋ አለመታዘዝዋ ነው። ምድራዊው ንጉሥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሆነ፥ ሕዝቡ ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ ሆኖ እንዲኖር ይረዳል። ንጉሡ ታዛዥ ባይሆንም እንኳ፥ እስራኤላውያን ለሰማያዊ ንጉሣቸው መታዘዛቸውን መቀጠል ነበረባቸው፤ ነገር ግን ልክ በመሳፍንት ዘመን እንደ ነበረው ፈጥነው በኃጢአት ይወድቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፦

  1. ሕዝቡ ለእግዚአብሔር እየታዘዙ እንዲኖሩ እግዚአብሔርን ስለሚፈራ መሪ አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?
  2. መሪው ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢመራ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ግን የግል ግንኙነቱን ከእግዚአብሔር ጋር መጠበቅ እንዳለበት ይህ ምን ያስተምረናል?

መጽሐፈ መሳፍንት የሚያስተምረን የእግዚአብሔር ሰዎች በትእዛዙ በማይመላለሱበት ጊዜ፥ ፍርድን ብቻ ሳይሆን፥ ጥፋትንም ጭምር በራሳቸው ላይ እንደሚያመጡ ነው። ከመሳፍንት 17-21 ያለው ክፍል ዋና ትምህርት ለቃል ኪዳኑ አለመታዘዝ በሚኖርበት ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በመተው ሐሰተኛ አማልክትን እንደሚያመልኩ ነው። እግዚአብሔርን በሚተዉበት ጊዜ የቅን ፍርድ ጉድለትና የእርስ በርስ መጠፋፋት ይከሰታል። ፈሪሀ እግዚአብሔር በማይኖርበት ስፍራ፥ ፍትሐዊ ሕግጋት አይኖሩም፤ ውጤቱም የሕዝቡ ሁሉ መሠቃየት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሕጎቻቸው ውስጥ እንዲሠሩ ያልፈቀዱ ሕዝቦች ያጋጠሟቸው መቅሠፍት፥ የፍርድ መዛባት፥ ጉቦኝነት፥ ጦርነትና የመሳሰሉት ነገሮች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ በኢትዮጵያ እውነት መሆኑን እንዴት አየህ?

በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ ሁለት ዋና ዋና የእግዚአብሔር ሥዕላዊ ሁኔታ እናያለን። የመጀመሪያው፥ የእግዚአብሔር የሥነ - ሥርዓት እርምጃ ነው። ሕዝቡ በኃጢአት በሚወድቁበት ጊዜ እግዚአብሔር አስቸጋሪ ነገሮችን ወደ ሕይወታቸው በማምጣት ሥነ ሥርዓትን (ዲስፕሊንን) ያስተምራቸው ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት ሊያጠፋቸው አልነበረም፤ ነገር ግን ሕዝቡ ከኃጢአት እንዲርቁና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለሕዝቡ ሁሉ የሚጠቅም ኑሮ እንዲኖሩ ነበር፤ (ዕብ. 12፡4-11 ተመልከት)።

በሁለተኛ ደረጃ በምሕረት የተሞላውን የታጋሹን የእግዚአብሔር ሥዕላዊ ሁኔታ እናያለን። እግዚአብሔር ሕዝቡ በሚተዉት ጊዜ በጽድቅ በመፍረድ ወዲያውኑ ሊቀጣቸው ይችል ነበር። ይህንንም ቢያደርግ ፍጹም ትክክል ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ለብዙ መቶ ዓመታት በትዕግሥት በመሥራት ይቅርታውንና በሕይወታቸው ላይ የሚደርሰውን ችግር ልባቸውን ወደ እርሱ ለመመለስ ይጠቀሙበት ዘንድ ሞክሮ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡ ታማኝ ባልሆኑበት ጊዜ እንኳ ለእነርሱ ታማኝ ነበር። ወደ እርሱ በጮኹ ጊዜ ጸሎታቸውን በመመለስ፥ እነርሱን ከባርነት ነፃ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ያደርግ ነበር። እግዚአብሔር በምሕረቱ ነቢያትን እየላከ ያስጠነቅቃቸውና ለማውጣት መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር በአሁኑ ዘመንም ምሕረቱንና ትዕግሥቱን እያሳየን ያለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር ምሕረት በሕይወትህ የታየው እንዴት ነው? ሐ) ለአንተ ስላለው ትዕግሥት፥ ምሕረትና ጸጋ እግዚአብሔርን አመስግነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መሳፍንት 1-16

ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ችግር በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ግልጥ ዓመፅ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ አለመታዘዝ ነው። እግዚአብሔርን ሙሉ ለሙሉ አላመልክም ማለት ሳይሆን፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በከፊል ብቻ መታዘዝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ችግር ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በቤተ ክርስቲያን ወይም በራስህ ሕይወት ውስጥ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ያየኸው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ፥ ቆይቶ ወዳለመታዘዝ ያመራል። እግዚአብሔር ልንከተለው የሚገባንን ትእዛዝ ወይም ልናደርገው የሚያስፈልግ ነገር ሲሰጠንና ያንንም በከፊል ብቻ ስንከተል መንፈሳዊ ውድቀት በሕይወታችን ይጀምራል። በቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል። በከፊል መታዘዝ ከዓለም ጋር ጓደኝነት ወደ መፍጠር ነው የሚመራው። ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ክርስቲያን በግሉ ዓለምን መምሰል ይጀምራል፤ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውንና ልዩ መሆናቸውን እያጡ ይሄዳሉ። ይህም ነገር ወዲያውኑ ዓለምንና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቅልቅል አምልኮ ይመራል። በመጨረሻም እግዚአብሔርን ሙሉ ለሙሉ ወደ መካድና ወንጌልን ወደ መቃወም ያደርሳል።

መጽሐፈ መሳፍንት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር እንዴት ሙሉ በሙሉ እንዳልታዘዙና እርሱ እንዳዘዘውም ከነዓናውያንን እንዳላባረሩ ያሳየናል። ስለሆነም እግዚአብሔርን የመቃወም ሂደታቸው ተጀመረ። በመጀመሪያው እንደ ከነዓናውያን ማምለክ ጀመሩ። ይህም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ድቀት መራቸው። ወዲያውኑ ከነዓናውያን ይጨቁኗቸው ጀመር። እግዚአብሔር የእርሱ ወደሆነው ንጹሕ አምልኮ ሊመራቸው ጠላቶቻቸውን ድል ይነሣ ዘንድ ፈቀደ። ይህ ነገር ለጊዜው የሠራ ቢሆንም እንኳ እያንዳንዱ ተከታታይ ትውልድ እግዚአብሔርን በመተዉ እግዚአብሔር የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ይወስድበት ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳ. 1-16 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ያልታዘዙት እንዴት ነው? ለ) ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት የጌታ መልአክ ያዘዘባቸው ፍርድ ምን ነበር፤ ሐ) በመሳ. 2፡10-19 የምታየውን የክሕደትን ዑደት፥ ፍርድና ነጻ መውጣት ግለጥ። መ) ከመሳፍንት 1-16 የእስራኤልን ሕዝብ ያሸንፉ ጠላቶችና በእነዚህ ጠላቶች ላይ ድልን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያስነሣቸውን መሳፍንት ዘርዝር። ሰ) መንፈስ ወረደባቸው ተብሎ የተጻፈላቸውን ሰዎች ዘርዝር።

1. የዘመነ መሳፍንት መግቢያ (መሳ. 1-3፡6)።

ሀ. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በጠላታቸው ሁሉ ላይ ድልን እንዴት እንደሰጣቸው ለማሳየት የቀረቡ ምሳሌዎች (መሳ.

1፡1-18)

አይሁዳውያን ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍና ከምድሪቱ ለማባረር ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው? ኃይል ስላነሳቸው ነውን? ወይስ በጌታ ርዳታ ሊያባርሩአቸው ስላልሞከሩ ነው? ወይስ የጌታን ትእዛዝ በከፊል ብቻ በመታዘዝ ስለበደሉ? ወይስ እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ድልን እንደሚሰጣቸው የገባውን ተስፋ ስላጠፈ ነው?

በዚህ ክፍል የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ሊያሳየን የፈለገው፥ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለ ነበር አይሁድን ለመቋቋቋም የቻለ ማንም ሰው እንዳልነበረ ነው። በይሁዳና በከነዓናውያን መካከል የተደረገውን ጦርነት በምሳሌነት በማቅረብ፥ አይሁድ በቀላሉ እንዴት ሊያጠፏቸው እንደቻሉ ያሳየናል። እንዲሁም አንድ ሰው በእግዚአብሔር እርዳታ አንድን ከተማ እንዴት እንዳሸነፈ አሳይቷል። የካሌብ ልጅ የሆነው የናትናኤል ታሪክ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ሁሉ ያሸንፉ ዘንድ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደ ነበር የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።

ለ. አይሁድ ከነዓናውያንን ለማሸነፍና ለማጥፋት አልቻሉም ነበር (መሳ. 1፡18-36) አይሁድ ከነዓናውያንን ሊያሸንፉ ያልቻሉበትን ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ ከማሳበብ ይልቅ እራሳቸው እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አለመቻላቸው እንደሆነ መገንዘብ ነበረባቸው። ከእስራኤል ነገዶች ማናቸውም ቢሆኑ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አልቻሉም ነበር፤ ስለዚህ በእያንዳንዱ ነገድ አካባቢ ያልተሸነፉና ያልጠፉ የከነዓናውያን ከተሞች ነበሩ።

ሐ. ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እግዚአብሔር ያመጣው ፍርድ (መሳ. 1፡1-5) አንድ ቀን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ለመፍረድ ተነሣ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ የሚታመነው የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ከነዓናውያንን ከእንግዲህ ማሸነፍ እንደማይችሉ ነገራቸው። ከነዓናውያንንና የአምልኮ ስፍራቸውን በሙሉ ስላላጠፉ፥ ከእንግዲህ እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ሙሉ ድልን እንደማይሰጣቸው ነገራቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መታዘዝ እንዳለብን ይህ ነገር ብርቱ ማስጠንቀቂያ እንዴት ይሆነናል?

ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ ሙሉ በሙሉ አለመታዘዝ ነው። ያልታዘዝናቸው አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን እያወቅን፥ ለእግዚአብሔር በታዘዝንባቸው ነገሮች መመካት አንዳችም ረብ የለውም። በከፊል መታዘዝ አለመታዘዝ ስለሆነ፥ በእኛ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣል።

መ. የክሕደት፥ የፍርድና ነፃ የመውጣት ዑደት (መሳ. 2፡6-3፡6)

በመሳፍንት 3፡1-6 ከነዓናውያን ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ እግዚአብሔር ያልፈቀደበትን ሌላ ምክንያት እናገኛለን። እግዚአብሔር የሚቀጥለው የእስራኤል ትውልድ ለቃል ኪዳኑ ይታዘዝና ይከተለው ወይም አይከተለው እንደሆነ ለመፈተን ይህንን ሕዝብ ሊጠቀምበት ፈለገ። የሚያሳዝነው፥ እያንዳንዱ ትውልድ ዓለምን (ከነዓናውያንን) ወደ መምሰል አዘነበለ፤ በአምልኮውና በሥነ ምግባሩም የተበላሸ ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እግዚአብሔር ለእርሱ ያለንን ፍቅር የሚመዝንባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ያ ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ፈተና የሚወድቁት ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል፥ የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ በዚህ ዘመን ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ ያለፈበትን የታሪክ ዑደት ያሳየናል። በመጀመሪያ፥ አይሁድ ሌሎች አማልክትን በማምለክ በእግዚአብሔር ላይ ዓመጹ። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሊቀጣቸውና ለእርሱ ወደሆነ አምልኮ ሊመልሳቸው ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ሦስተኛ፥ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ነፃ ያወጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። አራተኛ ከጠላቶቻቸው የጭቆና አገዛዝ ነፃ የሚያወጡአቸውን መሳፍንት አስነሣላቸው። አምስተኛ፥ እስራኤላውያን በሰላም ጊዜ ደስ እያላቸው ኖሩ። በዚህ የሰላም ጊዜ ነበር እስራኤላውያን እንደገና በእግዚአብሔር ላይ ያመፁትና እርሱም ለጠላቶቻቸው ቀንበር አሳልፎ በመስጠት ይቀጣቸው።

2. ዘመነ መሳፍንት (መሳ. 3፡7-16)

ስማቸው ተጠቅሶ የምናገኘው 12 መሳፍንት ቢሆኑም፥ የተለየ ትኩረት የተሰጣቸው ስድስቱ ብቻ ናቸው።

1. ጎቶንያል፡- የካሌብ ልጅ ሲሆን በቅድሚያ የተጠቀሰ ነው። የሌሎች መሳፍንት ተግባር የተመሠረተው በዚህ ሰው ምሳሌነት ላይ ነው። በጎቶንያል ታሪክ የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ የሚተርከው የኃጢአት፥ የፍርድ፥ የንስሐና ነፃ የመውጣት ዑደትን ነው። ይህ ዑደት በመጽሐፈ መሳፍንት ሌላ ክፍል አምስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል።

2. ናዖድ፡- የዚህ ሰው ታሪክ በዝርዝር ተዘግቧል። እስራኤልን ነፃ ማውጣቱን ልዩ የሚያደርገው ሞዓባውያንን ለማሸነፍ ራሱ የሠራው ሥራ በመኖሩ ነው። ሌላው መለያው እጀ ግራኝ መሆኑ ነው፡፡

3. የዲቦራና የባርቅን ታሪክ ልዩ የሚያደርገው ሴቶች በድሉ ውስጥ በተጫወቱት ልዩ ሚና ነው። ዲቦራ የእስራኤል መንፈሳዊ መሪ የነበረች ነቢይት ናት። ኢያዔል ደግሞ የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በመግደል የዚህ ድል ተሳታፊ ነበረች።

4. በመጽሐፈ መሳፍንት ማዕከላዊ ታሪክ ላይ የጌዴዎንና የልጁን የአቤሜሌክን ታሪክ እናገኛለን። በዚህም ቦታ የጌታ መልአክ የተባለው (ክርስቶስ) ጌዴዎንን በመጥራትና በኃይል በማስታጠቅ ተግባር የተጫወተውን ሚና እንመለከታለን። በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው የእስራኤላውያንን ጦርነት እግዚአብሔር እንዴት እንዳሸነፈላቸው መናገር ነበር። ባደረጉት ነገር እንዳይመኩ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ጦርን ለማሸነፍ 400 ሰዎችን ብቻ ተጠቀመ።

አይሁድ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን ሰው ንጉሥ ለማድረግ እንደሞከሩ እናያለን። ጌዴዎንን ንጉሣቸው እንዲሆን ጠየቁት፤ እርሱ ግን እምቢ አለ። ይህንን ያደረገው የሕዝቡ ንጉሥ መሆን ያለበት እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና እርሱም ሆነ ሕዝቡ፥ ሰብዓዊ ንጉሥ ከመፈለግ ይልቅ ለእግዚአብሔር ሥልጣን መገዛት እንዳለባቸው ያውቅ ስለነበረ ነው (መሳ. 8፡22-23)።

በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ሦስት የሚያሳዝኑ ነገሮች ተፈጽመዋል፡-

ሀ. መጀመሪያ፥ ጌዴዎን ከጠላቶቼ በተዋጋሁ ጊዜ አልረዳችሁኝም ብሉ የሱኮትን ከተማ ሲቀጣ እናያለን።

ለ. ሁለተኛው ጌዴዎን የወርቅ ኤፉድ መሥራቱ ነበር። ኤፉድ ካህናት የሚለብሱት በተለያየ ሕብር ያሸበረቀ ልብስ ነበር። ኤፉድ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የሚያገለግል መሣሪያ ነበር፤ (1ኛ ሳሙ. 23፡6-12)። ጌዴዎን ኤፉድ ለምን እንደሠራ ግልጽ አይደለም። ምናልባት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ተጠቅሞበት ይሆናል። በምንም መንገድ ይሁን ብቻ ወዲያውኑ ወደ አምልኮ ዕቃነት ተለወጠ። የእግዚአብሔር አምሳል ተደርጎ ተመልኳል፤ ወይም አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቡት፥ ኤፉድ በአንድ ጣዖት ላይ ይደረግና ሰዎች ወደዚያ በመምጣት ኤፉዱ የአማልክቶቻቸውን ፈቃድ እንደሚወስንላቸው ያምኑ ነበር።

እግዚአብሔር ጌዴዎንን በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቀመበት ቢሆንም ይህ ነገር ለእርሱና ለቤተሰቡ የማሰናከያ ዓለት ሆነባቸው።

ሐ. የጌዴዎን ልጅ የሆነው አቤሜሌክ ራሱን አነገሠ። ይህም በእስራኤል ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት አስነሣ። አቤሜሌክንም አንዲት ሴት የወፍጮ ድንጋይ በራሱ ላይ ለቃ ገደለችው።

5. ዮፍታሔ፡- በኅብረተሰቡ ተንቆና ተጠልቶ የነበረ ሰው ሲሆን የሚቀጥለው ዋና መስፍን ሆነ። በእርሱም ጊዜ ሁለት የሚያሳዝኑ ነገሮች ሆኑ። በመጀመሪያ፥ ከጦርነት አሸንፎ በሚመጣበት ጊዜ የሚያገኘውን የመጀመሪያውን ነገር ለእግዚአብሔር ለመሠዋት አደገኛ ስእለት ተሳለ። ጦርነቱን አሸንፎ በመጣ ጊዜ ያገኘው የመጀመሪያ ነገር ሴት ልጁ ስለነበረች፥ ስእለቱን መፈጸም ነበረበት። በዮፍታሔ ሴት ልጅ ላይ ስለተፈጸመው ትክክለኛ ነገር ምሁራን ይከራከራሉ። አንዳንዶች ዮፍታሔ ልጁን ለእግዚአብሔር ስለሰጠ፥ ድንግል ሆና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የምታገለግል ሆነች ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ዮፍታሔ ልጁን ለእግዚአብሔር ሠውቶ መሥዋዕት አቅርቧል ይላሉ። ሰውን በመሥዋዕትነት ማቅረብ በብሉይ ኪዳን የተከለከለ ቢሆንም (ዘሌ. 18፡21፤ ዘዳ. 18፡10-12)፥ ዮፍታሔ በልጁ ላይ ያደረገው ይህን ሳይሆን አይቀርም።

ሁለተኛ፡በዮፍታሔና በኤፍሬም ነገዶች መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህም ከኤፍሬም ነገድ 42000 ሰዎች ሞቱ።

6. በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የምናገኘው የመጨረሻው ትልቅ መስፍን ሶምሶን ነው። ሶምሶን ናዝራዊ ሆኖ እንደሚወለድ እግዚአብሔር ለወላጆቹ ስለነገራቸው ልደቱ ልዩ ነበር። ናዝራዊ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ለእግዚአብሔር አገልግሉት የለየ ሰው መሆኑን ታስታውሳለህ። የሶምሶን ናዝራዊነት ልዩ የሆነው የዕድሜ ልክ በመሆኑ ነው። ናዝራዊ በመሆኑም የወይን ፍሬ ውጤት የሆነ ማንኛውንም ነገር የማይበላ፥ ምንም ዓይነት ሬሳ የማይነካና ጠጉሩን የማይቆረጥ ነበር፤ (ዘኁ. 6፡1-21 ተመልከት)። የሚያሳዝነው ግን ሶምሶን እነዚህን ትእዛዝት ሁሉ አፍርሷል። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ወይንን ሳይጠጣ አልቀረም፤ የሞተ አንበሳ ሬሳ ነክቷል።ጠጉሩን በተቆረጠ ጊዜ ግን እግዚአብሔር የሰጠው ኃይል ከእርሱ ተወሰደ። ሶምሶን መንፈስ ቅዱስና ታላቅ ኃይል የነበረው ቢሆንም፥ የሥነ ምግባር ሕይወቱ ግን በጣም የተበላሸ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ለማዳን በሶምሶን ለመጠቀም ያሰበውን ያህል አልተጠቀመበትም። ለዚህ ነው ሶምሶን በእስራኤል ሕዝብ ላይ የነበረው መሪነት ፍልስጥኤማውያንን ማሸነፍና እንደገና በእነርሱ እጅ መውደቅና መገዛት የተደጋገመበት። ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ የነበራቸው የበላይነት እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ ቀጥሎአል።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ መሪዎች ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና መጠበቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ የሶምሶን ታሪክ እንዴት ያስጠነቅቀናል?

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከተለያዩ መሳፍንት የምናገኛቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) በእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?

መሳፍንት 17-21

የውይይት ጥያቄ፥ የሰው ልጅ ልብ በመሠረቱ መልካም ነው ወይስ ክፉ? ለምሳሌ፥ ሕግ እንዲሁም ሕግን የሚያስፈጽም የፖሊስ ኃይል ባይኖር ኖሮ የሰዎች ዝንባሌ መልካም ይሆን ነበር ወይስ ክፉ? መልስህን አብራራ።

የመጽሐፈ መሳፍንት የመጀመሪያ ዋና ክፍል (ከምዕ. 1-16 ያለው) በእነዚያ ዓመታት የነበሩ የአይሁዳውያን ዋና የፖለቲካ ችግሮችን ግልጽ በሆነ መንገድ ያሳየናል። ትኩረታቸውም ሕዝቡን ከውጭ ኃይል ወይም ከጠላት ቀንበር ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር ባስነሣቸው መሳፍንትነት አመራር ላይ ነው።

የመጽሐፈ መሳፍንት የመጨረሻው ክፍል (መሳፍንት 17-21) በመሳፍንት ዘመን የነበረውን ሃይማኖታዊና የሥነ-ምግባር ጉድለት የሚያንጸባርቅ ነው። የሰው ልብ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እስካልሆነ ድረስ ሊኖር የሚችለውን ግልጽ ሥዕል ያሳያል። ሰው «በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን» (መሳ. 21፡25) ማድረግ ሲጀምር፥ ክፉ መሆኑ ወዲያውኑ ይረጋገጣል። ሕግ ወይም ሕግ አስፈጻሚ አካል በሌለበት ለሕገወጥነት መከሰት ጊዜ አይወስድበትም። ሕግና ሕግን የሚያስፈጽሙ የሕዝብ መሪዎች የሰው ኃጢአት በተወሰነ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ያደርጋሉ። እነዚህ ተከላካዮች ሲነሡ፥ የሰው ኃጢአተኝነት ወዲያውኑ ገሐድ ይወጣል።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) አንተስ ይህ ነገር ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ ስለ ሰው ክፉ ባሕርይ የሚያስተምርህ ምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡ መሳ. 17-21 አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች የሰው ልጅ ክፋት የታየው እንዴት ነው?

በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ. 17-21 የሚገኙት ታሪኮች የተፈጸሙበትን ጊዜ ማወቅ የማይቻል ነው። የዳን ነገዶች ገና ርስት በመፈለግ ላይ ስለሚገኙና የአሮን ልጅ ፊንሐስ ሊቀ ካህን በመሆኑ፥ ታሪኮቹ የተፈጸሙት በመጀመሪያዎቹ የመጽሐፈ መሳፍንት ዘመን ሳይሆን አይቀርም (መሳ. 18፡1፤ 20፡27-28)። የእነዚህ ታሪኮች ዓላማ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን አጠቃላይ የሥነ-ምግባር መመሪያ መጥፋት ለማሳየት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሊያውቁና ሌሎችን ማስተማር ይገባቸው ለነበሩ ሌዋውያን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ በላይ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እንዲኖሩ የሚጠበቅባቸው ሌዋውያን ነበሩ። እነርሱም እንደቀረው ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ። በኃጢአታቸውም ምክንያት የቀሩት ሕዝብ ወደ ክሕደትና ጣዖት አምልኮ ሄዱ። የእነርሱም ተግባር ሕዝቡን ወደ እርስ በርስ ጦርነት መራው።

1. የሌዋውያን ካህናትና የዳን ነገድ ታሪክ (መሳ. 17-18)

የእግዚአብሔር ሕዝብን ኃጢአተኝነት የሚያመለክተው የመጀመሪያው ታሪክ፥ ስለ አይሁድ ሃይማኖት መበላሸት ይናገራል። ይህ ብልሽት የተጀመረው ከኤፍሬም ነገድ የሆነች አንዲት ሴትና ልጇ ከብር የተሠራ ምስል ሠርተው በቤታቸው ባስቀመጡ ጊዜ ነው።

ወደ ደቡብ ብዙ ኪሎ ሜትር ራቅ ብሉ አንድ ሌዋዊ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ ሌዋውያን የእስራኤላውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲሆኑ በእግዚአብሔር የተመረጡ ነበሩ። ደግሞም ይኖሩባቸውም ዘንድ እግዚአብሔር 48 ከተሞችን ሰጥቷቸው እንደነበረ ታስታውሳለህ። ቤተልሔም ከእነዚህ አንዷ አልነበረችም። ይህም የሚያሳየው በሙሴና በኢያሱ ዘመን ተጀምሮ የነበረው የአኗኗር ዘይቤ እየተጣሰ መሆኑን ነው። ሌዋዊ ቤተልሔምን ትቶ ስለ መሄዱ የተነገረው እውነት፥ ጨርሶ ሊገኝባት የማይገባው ከተማ ስለነበረች፥ ሥራ አግኝቶ ወደሌላ ስፍራ መሄዱ ሊሆን ይችላል። ይህም እግዚአብሔር ያዋቀረው የአኗኗር ስልት እየተጣሰ መሆኑን ያሳያል። ሌዋውያን እስራኤላውያን ለጌታ ከሚሰጡት አሥራት በሚገኘው ገቢ ኑሮአቸውን መምራት ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝቦች አሥራታቸውን በማይሰጡበት ጊዜ ይህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዴት ይጎዳል? ለ) ይህ የአንተ ቤተ ክርስቲያንም ችግር ነውን? ከሆነስ ለምን?

ሌዋዊው ሥራ ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጓዘና ወደ ሚካ ቤት መጣ። ሚካም ላሠራው ጣዖት ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ቀጠረው። ሚካ ቤቱን የአምልኮ ስፍራ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ይህንን ያደረገው ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ በኃላፊነት ማገልገል የነበረበትን አንዱን ሌዋዊ በመቅጠር ነበር። ሌዋዊው ስለ ግል ሕይወቱ እንጂ ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ አምልኮ ግድ ስላልነበረው የተሳሳተውን አምልኮ ለመምራት ፈቃደኛ ሆነ። እውነተኛ አምልኮን ሳይሆን ገንዘብን ብቻ ፈለገ።

ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የዳን ነገድ አባሎች የሚኖሩበትን ስፍራ እየፈለጉ ወደዚህ ስፍራ ደረሱ። የዳን ነገዶች በሜዲትራኒያን ባሕረሠላጤ አጠገብ መሬት ተሰጥቶአቸው ነበር። መሬቱ በዚያ ስፍራ እጅግ ለም ቢሆንም፥ በከነዓናውያን ተይዞ ነበር፤ ስለዚህ የዳን ነገዶች ሌላ ስፍራ ይፈልጉ ዘንድ አምስት ወታደሮችን ላኩ። ወደ ሚካ ቤት በደረሱ ጊዜ ሌዋዊው ከደቡብ የእስራኤል ክፍል እንደመጣ ተገነዘቡ። በዚያ ስፍራ የሚካሄድ የጣዖት አምልኮ አለቃ መሆኑንም አወቁ። ከዚያ በኋላ አምስቱ ሰዎች ወደ ሰሜን 240 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሌሳ ወደምትባል ስፍራ ደረሱ። የወደፊት ቤታቸውም በዚያ እንዲሆን ወሰኑ። የቀሩት የዳን ነገዶች ወደ ሌሳ መጥተው ምድሪቱን ሲወሩ፥ አምስቱ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት በመሄድ ሌዋዊውንና የሚካን ጣዖት ወደ ሌሳ ይዘው ሄዱ። ለብዙ ዓመታት ይህ ሌዋዊና ቤተሰቡ የዚህ ጣዖት ካህናት ሆነው ቀሩ። ሌሳ በኋላ «ዳን» ተብላ የተጠራች የእስራኤል የሩቅ ሰሜን ድንበር ናት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ስለ እግዚአብሔር የነበራቸውን ደካማ አስተሳሰብ በሚመለከት ምን እንማራለን? ለ) የአይሁዳውያን ሃይማኖት በከነዓናውያን ሃይማኖት በፍጥነት የተበከለው ለምንድን ነው? ሐ) ሃይማኖታችን በዓለማዊ ልምምድ ስለመበከሉ አደገኛነት ምን እንማራለን?

ከዚህ ትምህርት የምናገኛቸው በርካታ እውነቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የከነዓናውያንን ባሕልና ሃይማኖት እንዴት በፍጥነት እንደለመዱ ማየት እንችላለን። ሁለተኛ፥ ሕዝቡ የእግዚአብሔር አምልኮ ከጣዖት አምልኮ ጋር ሊቀላቀል እንደሚችል እንዴት እንዳሰበ ማየት እንችላለን። እግዚአብሔር ወደ ጣዖት ሊለወጥና ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ አሰቡ። ሦስተኛ፥ የጣዖት አምልኮን ዋጋ ቢስነት እናያለን። ጣዖት ራሱን ከመሰረቅ ለማዳን አለመቻሉና፥ ኃይል እንደሌለው ያሳየናል።

2. ሌዋዊውና ቁባቱ (መሳ. 19-21)

ከዘመነ መሳፍንት የምናገኘው ሁለተኛው ታሪክ የሕዝቡን የሥነ ምግባር ብልሹነት ያሳየናል። እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቹ ድካምና ኃጢአት እንዳየለባቸው ለሁለተኛ ጊዜ እንመለከታለን። የመጀመሪያው ሌዋዊ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ ኤፍሬም እንደሄደ፥ ሁለተኛው ሌዋዊ ደግሞ ወደ ቤተሰቦችዋ የተመለሰችውን ቁባቱን ፍለጋ ከኤፍሬም ወደ ቤተልሔም መጣ። ከቤተልሔም ቁባቱን ይዞ ወደ ኤፍሬም በሚመለስበት ጊዜ እግረ መንገዱን ጊብዓ በምትባል በብንያማውያን ከተማ መሸበትና አደረ። ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች፥ እስራኤላውያን እጅግ አስጸያፊ ተግባር ፈጸሙ። ለራሳቸው ሰዎች መስተንግዶ ማድረግ አልቻሉም። ግብረ ሰዶም ለመፈጸም ፈልገው ሰውዩውን ካደረበት ቤት ለማስወጣት ሞከሩ። ሌዋዊውን ያሳደረው ሰው ግን የገዛ ሴት ልጁንና የሌዋዊውን ቁባት አውጥቶ ሰጣቸው። ቁባቱም እስክትሞት ድረስ በመፈራረቅ ሌሊቱን ሙሉ አመነዘሩባት።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ታሪክ የሌዋዊንና የእስራኤልን ሕዝብ ሃይማኖታዊና ሥነ- ምግባራዊ ክፋት እንዴት ያሳየናል?

ሌዋዊው የቁባቱን ሬሳ 12 ቦታ ቆራረጠና ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንዱን ቁራጭ ላከ። ይህም ነገር የ12ቱን ነገዶች ቁጣ ቀሰቀሰና ምን እንደተፈጸመ ለማየት መጡ። ታሪኩን በሰሙ ጊዜ፥ ይህንን ኃጢአት የፈጸሙትን ሰዎች አሳልፈው እንዲሰጧቸው የብንያም ነገዶችን ጠየቁ። ብንያማውያን ግን ስለተቃወሙ፥ የእርስ በእርስ ጦርነት ተነሣ። በጦርነቱም 40000 እስራኤላውያንና 25100 ብንያማውያን ሞቱ። የብንያማውያን ሴቶችና ልጆች በሙሉ ተገደሉ። ከብንያም ነገድ በሙሉ የተረፉት 600 ሰዎች ብቻ ነበሩ።

ሌሎች እስራኤላውያን፥ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው የብንያም ነገድ ሊጠፉ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ ለእነዚህ 600 ብንያማውያን 600 ሚስቶች የሚገኙበትን ዘዴ ፈጠሩ። በዚህም የብንያምን ነገድ ጨርሶ ከመጥፋት አዳኑት።

ሰዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ሲያደርጉ፥ ኃጢአታቸው አድጎ በርካታ ሰዎችን እንደሚነካና እንደሚያጠፋ አይገነዘቡም። የጊብዓ ሰዎች ኃጢአት በሺህ የሚቆጠሩ የበርካታ እስራኤላውያንን ሞትና የብንያም ነገድን ወደ ውድመት የሚያደርስ ጥፋት አስከትሉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ቁጥሮች ኃጢአት ስለሚስፋፋበት መንገድና በምድሪቱ ስለ ሕግና ሥርዓት አስፈላጊነት ምን ያስተምሩናል? ለ) ከዚህ ታሪክ ለቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚጠቅሙና ልናዛምዳቸው የምንችል አንዳንድ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና ዋና ትምህርቶች

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት እንዳነበብነው በውስጡ የሚገኙ፥ ከሕይወትህና ከቤተ ክርስቲያንህ ጋር ልታዛምጻቸው የምትችለውን ዋና ዋና እውነቶች ናቸው ብለህ የምታስባቸውን ዘርዝር።

1. መጽሐፈ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በከፊል የመታዘዝ ውጤት ምን እንደሆነ ያሳየናል። እግዚአብሔር ከነዓናውያንን በሙሉ እንዲያጠፉ የሰጠውን ትእዛዝ አይሁድ በከፊል ብቻ ስለታዘዙት፥ ወደ ባሰ ኃጢአት የመውደቅን ሂደት ጀመሩ። ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ ብዙም ሳይቆይ፥ ለእርሱ በግልጽ ወዳለመታዘዝ ተለውጧል። የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያን ሕይወትም ይፈጸማል። ማንም ሰው በድንገት በኃጢአት ፈጥኖ አይወድቅም። ይልቁንም ይህ በሂደት የሚፈጸም ነው። በመጀመሪያ መጠነኛ ጅማሬ ይኖረዋል። ይህ ጅማሬ በከፊል መታዘዝ ነው። በአብዛኛው የሕይወት ክፍላችን ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን፤ ነገር ግን ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች በሕይወታችን እንዲቆዩ እንፈቅዳለን። እነዚህ ኃጢአቶች፥ ኩራት፥ ትዕቢት፥ ቁጣ፥ ወይም ቅንዓት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ብዙ ሳይቆዩ እነዚህ ኃጢአቶች አድገው ሕይወታችንን በመቆጣጠር ለእግዚአብሔር በግልጽ ወዳለመታዘዝ ያደርሱናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህንን እውነት በራስህ ወይም በሌላው ክርስቲያን ሕይወት እንዴት አየኸው?

2. መጽሐፈ መሳፍንት ዓለም በክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ያላትን ኃይልና እንዴት ወደ ኃጢአት እንደምትመራ ያሳየናል። በኢያሱ መሪነት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለመከተልና እርሱን ብቻ ለማምለክ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጠላቶች የሆኑት ከነዓናውያን በመካከላቸው እንዲኖሩ ስለፈቀዱ፥ የከነዓናውያን ልምምድ ብዙም ሳይቆይ ችግር ያመጣባቸው ጀመር። ወዲያውኑ እንደከነዓናውያን ማሰብና ማምለክ ጀመሩ፤ በመጨረሻም እንደ ከነዓናውያን መኖር ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከዓለምና ከልምምዷ እንድንለይ፥ እርሷንም ከመምሰል እንድንጠነቀቅ ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ቆሮ. 6፡14-18 እና 1ኛ ዮሐ. 2፡15-17 አንብብ። ከዓለም ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት በዚህ ክፍል የተሰጠን ትእዛዝ ምንድን ነው?

ክርስቲያኖች ሁሉ ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንድናቋርጥ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም። ኢየሱስም የጸለየው፥ በዓለም እንድንኖር እንጂ፥ ከዓለም እንድንወጣ አይደለም (ዮሐ. 17፡14-19)። እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችን ጓደኛ እንድናደርግ፥ ወንጌልን እንድናካፍላቸው፥ በሚያስፈልጋቸው ነገር እንድንረዳቸው፥ ከጎናቸው ሆነን እንድንሠራ፥ ወዘተ. ይፈልጋል። ኢየሱስ ራሱ «የኃጢአተኞች ወዳጅ» ተብሉአል (ማቴ. 11፡19)። ከማያምኑ ጋር ያለንን ማንኛውንም ኅብረት ማቆም አለብን የሚሉ ሰዎች ተሳስተዋል። ከእነርሱ ጋር ካልኖርን፣ ካላወቅናቸውና ፍቅርን ካላሳየናቸው በቀር፥ የዓለም ብርሃንና ጨው እንዴት መሆን እንችላለን? እንድንጠነቀቅ የተነገረን ነገር ቢኖር፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ዓለማዊ ተጽዕኖ እንዳይኖር ነው። እንደ እግዚአብሔር ልጆች የዓለም ፍልስፍና በሕይወታችን ላይ የማያስፈልግ ተጽዕኖ እንዳያደርግ መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ፡ የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር፥ ለራሳችን፥ ለቤተሰባችን ወይም ለጎሣችን በራስ ወዳድነት የተለየ ጥንቃቄ ለማድረግ መመኘት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ ሊደረግበት የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር እየኖረ በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ የማይደረግበት እንዴት ነው?

3. እግዚአብሔር አማኞች ዓለምን እየመሰሉ ሲሄዱ፥ ያነጻቸው ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይጠቀማል። ይህ ማለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ስለ ኃጢአት ፍርድ ናቸው ማለት አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ናቸው። አንዳንዶች በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ናቸው በማለት እንዳንፈርድ መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔር ሕዝብ በኃጢአት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ የሚያደርግበት መንፈሳዊ መመሪያ አለ። ይህም በሽታ፥ የወዳጅ ሞት፥ ወይም በአገር ላይ የሚመጣ ችግር ሊሆን ይችላል። በዚህ ዓይነት ጊዜ የሚመጣው ችግር ዓላማ ሕዝቡ ንስሐ ገብተው ከክፉ መንገዳቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። እውነተኛ ንስሐ ሰውን ጠባዩን እንዲለውጥ ያደርገዋል። እስራኤላውያን ግን በእውነት ንስሐ ገብተው እንደሆነ የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም። ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደወጡ ብዙም ሳይቆዩ፥ ወደ ቀድሞ ክፉ ተግባራቸው ይመለሱ ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት ግን ንስሐ እንድንገባና መንገዳችንን እንድንለውጥ ነው። ወደ በረከት ስፍራ የሚመልሰን በዚያን ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በግል ሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሔር ከኃጢአት ያነጻችሁ ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደተጠቀመ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ስጥ።

4. የእግዚአብሔር ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ታላቅ መሪን በማስነሣት በእርሱ አማካይነት ነጻነትን ይሰጣቸዋል። እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው በሚጨቆኑበት ጊዜ፥ የሕዝቡን ጸሎት በመስማት መሳፍንትን አስነሣላቸው። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የምናያቸው መሳፍንት ተቀዳሚ ተግባራቸው ወታደራዊ መሪነት ሆኖ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ አውጥተዋል። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች የመረጠው በመንፈሳዊነታቸው ለመሆኑ ምንም መረጃ የለንም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ መሳፍንት በጣም መንፈሳዊ አልነበሩም። ሶምሶን ዘማዊ ነበር። ዮፍታሔ ልጁን ሠውቷል። ጌዴዎን ሕዝቡን ወደ ኤፉድ አምልኮ መርቷል። አብዛኛዎቹ መሳፍንት ልንከተለው የሚገባ መንፈሳዊ ምሳሌነት አልተዉልንም። ቢሆንም እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ሰውን ከመንፈሳዊነቱ ውጭ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል የእነርሱ ታሪክ ያሳየናል።

ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር የሚሠራው በተመሳሳይ መንገድ ነው። እግዚአሔር ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ለማውጣት መሠረታዊ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ሰው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃውን ሳይመለከት ሊጠቀምበት ይችላል። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፥ አማኝ ያልሆነን የፖለቲካ መሪን በማስነሣት፥ ለአማኞች እንዲራራና ከችግሮቻቸው ነፃ እንዲያወጣቸው ሊያደርግ ይችላል።

ነገር ግን እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ መሪዎች የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። የእስራኤል ልጆች በተደጋጋሚ በኃጢአት የወደቁበት ምክንያት፥ ምናልባት እነዚህ መሳፍንት ለሕዝቡ መልካም መንፈሳዊ ምሳሌ ስላልሆኑ ይሆናል። የሰዎች ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ብዙ ጊዜ የሚወሰነው በመሪዎቻቸው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ መሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መመሪያዎች አንዱ ነው። መሪዎች እግዚአብሔርን ሲወዱና በቅድስና ሲያገለግሉት፥ ሕዝቡም እንዲሁ ያደርጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ እውነት ሲሆን ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምርጫ መመሥረት ያለበት፥ በትምህርት፥ በዘር፥ ወይም በቤተሰብ ውርስ፥ ወዘተ. ሳይሆን በመንፈሳዊ መመዘኛ መሆን እንዳለበት ይህ ምን ያስተምረናል?

5. መጽሐፈ መሳፍንት የሚያተኩረው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፡- መሳ. 3፡10፤ 6፡34፤ 11፡29፤ 14፡6፥ 19፤ 15፡14፤ 16፡20። ይህ በዚያን ዘመን ስለነበረው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን ያስተምረናል?

ከመጽሐፈ መሳፍንት ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተደረገ ትኩረት ነው። ከዚህ መጽሐፍ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተነገረው በጣም ጥቂት ነገር ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ግን የጌታ መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ከላይ የተሰጡትን ጥቅሶች በሚገባ ካጠናን የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፡-

ሀ. አንድ የተለየ ተግባር ለመፈጸም በተጠሩ ውሱን መሪዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ነበር። የመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ መውረድ የተለመደ ነገር አልነበረም፤ ሆኖም እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመምራት ወይም ነፃ ለማውጣት ይችሉ ዘንድ ለመረጣቸው ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው ነበር። በዚህ ዓይነት እነዚህ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከባርነ ያወጡት በራሳቸው ኃይል ሳይሆን፥ እግዚአብሔር መንፈሱን ስለ ሰጣቸው እንደሆነ ግልጥ መሆን ነበረበት። እውነተኛው የእስራኤል ነፃ አውጭ እግዚአብሔር እንጂ መስፍኑ አልነበረም።

ለ. መንፈስ ቅዱስ ሰዎች የእርሱን ልዩ ኃይል በሚፈልጉበት ጊዜ በተደጋጋሚ ይመጣ ነበር። በመጀመሪያ አካባቢ ሶምሶን ከጠላቶቹ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በላዩ ላይ ይወርድ ነበር።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ በሰው ደስ በማይሰኝበት ጊዜ ከዚያ ሰው ተለይቶ ይሄድ ነበር። ይህን እውነት እግዚአብሔር ከሶምሶን ተለየ ከሚለው ቃል መመልከት እንችላለን። በንጉሥ ሳኦል ታሪክ መንፈስ ቅዱስ ተወው የሚል ቃል ስናነብ (1ኛ ሳሙ. 16፡14)፥ ይህ ነገር ግልጽ ይሆንልናል። ለጸሎቱ መልስን በመስጠት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሶምሶን እንደተመለሰ ደግሞ የዳጎንን ቤተመቅደስ በመደርመሱ እንረዳለን፤ (መሳ. 16፡28-30)።

ልናስታውሰው የሚገባን አንድ በጣም አስፈላጊ እውነት አለ። እግዚአብሔር እውነቱን ሁሉ በአንድ ጊዜ አልገለጠም። ነገር ግን ስለ እርሱ የሚናገር ተጨማሪ እውነትን በየጊዜው በዘመናት ሁሉ በዝግታ ይገልጥ ነበር። ይህ «እየጨመረ የሚሄድ መገለጥ» በመባል ይታወቃል። አይሁድ እግዚአብሔር አምላክ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ማለት ሥላሴ መሆኑን አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንፈስ የእግዚአብሔር ተቀጥያ፥ ወይም የእግዚአብሔር ኃይልና ሥልጣን፥ የመኖሩ ማረጋገጫ አድርገው ያስቡት ነበር። መንፈስ ቅዱስን ከሥላሴ አንዱ አድርገን የምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ብቻ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ነው፥ ሆኖም ከእግዚአብሔር የተለየ ነው።

ይህም ማለት ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለንን መረዳት በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ ከመመሥረት መጠንቀቅ አለብን ማለት ነው። በኢዩኤል 2፡28 እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን መንፈሱን በሰዎች ሁሉ ላይ እንደሚያፈስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የጀመረው በጰንጠቆስጤ ቀን ነው፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ በላይኛው ክፍል ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ላይ ወርዶባቸው ነበር (የሐዋ. 2)። በአዲስ ኪዳን በሚገኙ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች የሚከተሉት እውነቶች ግልጽ ናቸው።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በጸጋው በሚያምኑበት ጊዜ ለልጆቹ በሙሉ የሚሰጠው እንጂ ለተወሰኑ የተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ ብቻ አይደለም። በሮሜ 8፡9 ጳውሎስ ማንም መንፈስ ቅዱስ የሌለው የክርስቶስ አይደለም ይላል። በሌላ አነጋገር፥ ይህ ማለት አማኝ አይደለም ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ የመጣው ባመንበትና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በሆንበት ጊዜ ስለሆነ አሁን ወደ እኛ እንዲመጣ መጸለይ ስሕተት ነው፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ያለማቋረጥ እንድንሞላ መጸለይ ግን ተገቢ ነው፤ (ኤፌ. 5፡18)። መንፈስ ቅዱስን እንዳናጠፋው ኃጢአታችንን መናዘዝ አለብን (1ኛ ተሰ. 5፡19)።

ለ. እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና ከልጆቹ ላይ አይወስድም። ክርስቲያኖች ኃጢአት በሚያደርጉበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሊወሰድባቸውና ደግሞ ተመልሶ ሊመጣ አይችልም። ኃጢአት የሚያደርግ ክርስቲያን እንኳ መንፈስ ቅዱስ አለው። እርስ በርሳቸው ይጋጩ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያኖች እንኳ መንፈስ ቅዱስ እንደነበራቸው ከ1ኛ ቆሮ. 1፡7 በግልጽ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ በእኛ ውስጥ የሚሠራውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እናጣለን።

ሐ. የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉበት ዘንድ እግዚአብሔር እንደፈለገ ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥተዋል (1ኛ ቆሮ. 12፡11)። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዓላማቸው ለግል ጥቅም፥ መንፈሳዊነታችንን ለመግለጥ አይደለም፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ብስለትና እግዚአብሔርን በማገልገል እንድታድግ እርስ በርሳችን ማገልገል እንድንችል ለማድረግ ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡26)።

መ. የአንድ ሰው መንፈሳዊነት የሚመዘነው፥ በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች እንጂ (ገላ. 3፡22-23)፥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በመቀበል አይደለም።

ይህ ትምህርት ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ከሚያስተምሩት የተለየ ቢሆንም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን ነገር ማወቅ አስፈላጊ ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ወይም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሚገኝ አንድ ክስተት ላይ የሥነ-መለኮት ትምህርት መሥርተን፥ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት መንገድ ምን ጊዜም ይኸው ነው ልንል አንችልም። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተገኘ እውነት እንጂ በእነዚህ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ በተገኘ እውነት ላይ መመሥረት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከላይ የተመለከትናቸው ጥቅሶች አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር እንዴት ይጋጫሉ? ለ) ሕይወትህን መርምር። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕይወትህ እንዳይሠራ የከለከሉህ ኃጢአቶች አሉን?

ሐ) የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወትህ እንዳሉ ማረጋገጫ የሚሆኑ ነገሮችን በምሳሌነት ጥቀስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ አስቴር

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ከመጽሐፍት ዓለም

የመጽሐፈ አስቴር

መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ባለፉት 20 ዓመታት ስለ ተፈጸመው የኢትዮጵያ ታሪክ አስብ። መንግሥትን፥ ቤተ ክርስቲያንንና የግል ሕይወትህን በመቆጣጠር ረገድ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እንዴት አየህ? ምሳሌዎችን ስጥ።

መጽሐፈ አስቴር እግዚአብሔር በማይታይ መንገድ በሉዓላዊነቱ ሕዝቡን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔር እጅ በሥራ ላይ ሆኖ ባያዩም እንኳ እግዚአብሔር በብዙ በማይታዩ መንገዶች ለራሳቸው ጥቅምና ለመንግሥቱ መስፋፋት በመሥራት ላይ ነው። ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንደ ዕድል የሚያየውን ነገር እኛ ክርስቲያኖች ዕድል እንዳይደለ እናውቃለን። ይልቁንም እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችንም ሆነ እጅግ ጥቃቅን የምንላቸውን ድርጊቶች ሁሉ ፈቃዱን ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል።

መጽሐፈ አስቴር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልዩ መጻሕፍት ከምንላቸው አንዱ ነው። ምሁራን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥሩ ከሚባሉ ሥነ ጽሑፎች አንዱ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ወይም በማንኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ተመሳሳይ የሆነ ሥነ-ጽሑፍ አለመገኘቱ በጣም ያልተለመደ ነገር ነው። መጽሐፈ አስቴር እጅግ አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢሆንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን እንደተካተተ ምሁራን ብዙ ጊዜ በመደነቅ ይጠይቃሉ። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ የእግዚአብሔር ስምም ሆነ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ ወዘተ ጨርሶ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ መጽሐፉን ለማይረዱት ሰዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ አይታያቸውም። ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጽሐፉ ስለ ሌሉች ዓለማዊ ታሪኮች የሚጠቅሰው አንዳችም ነገር ስለሌለ የታሪኩን እውነተኛነት ይጠራጠራሉ። ስለሆነም ይህ ነገር አጭር ልብ ወለድ ወይም ሰዎችን ለማስተማር የተሰጠ ምሳሌ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን መጽሐፈ አስቴርን ከማንበብ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው ታሪኩን በእውነተኛነቱ እንደተመለከተው ነው (ለምሳሌ፣ አስቴር 10፡2)።

የመጽሐፈ አስቴር ርእስ

መጽሐፈ አስቴር ከዋና ዋናዎቹ ባሕርያት አንዷ በሆነችው በአስቴር ስም የተሰየመ ነው። አስቴር አባትና እናቷ የሞቱባት በኋላም የፋርስ ንግሥት የሆነችና የአይሁድን ሕዝብ ሁሉ ያዳነች ሴት ናት። ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሴቶች ስም ተሰይመዋል፤ አንደኛው መጽሐፈ ሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፈ አስቴር ነው። መጽሐፈ አስቴር ወደ ግሪክ ቋንቋ በተተረጎመበት ጊዜ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ያክሉበት ጀመር። እነዚህ ታሪኮች መርዶክዮስ ስላየው ሕልም፣ መርዶክዮስ ለአርጤክስስ ስለጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎችና አስቴርና መርዶክዮስ ስላደረጉዋቸው የተለያዩ ጸሎቶች የሚናገሩ ናቸው። እነዚህ ታሪኮች በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የታከሉ ቢሆኑም፥ በመጀመሪያው መጽሐፈ አስቴር ውስጥ ያልነበሩ ታሪኮች ወይም ጥቅሶች ናቸው።

የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ

መጽሐፈ አስቴርን ማን እንደጻፈው መጽሐፉ ራሱ የሚናገረው ነገር የለም። በአይሁድ አፈ ታሪክ መሠረት መጽሐፈ አስቴር የተጻፈው በመርዶክዮስ ነው ቢባልም ይህን በሚመለከት አንዳችም መረጃ የለንም፡፡ ሆኖም መጽሐፉን በምናጠናበት ጊዜ በግልጥ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው አንድ አይሁዳዊ፥ የተማረና የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ያለው፥ የፋርስ ቤተ መንግሥትን መዛግብትና የቤተ መንግሥት ባህልንም ሊያገኝ የሚችል ሰው እንደ ነበረ ነው (አስቴር 10፡2)። እንዲሁም ጸሐፊው በአስቴርና በመርዶክዮስ መካከል የተደረጉትን ውይይቶች ያውቅ ነበር። መርዶክዮስ እነዚህን ሁሉ መመዘኛዎች ስለሚያሟላ መጽሐፉን እርሱ ጽፎት ሊሆን ይችላል።

መጽሐፈ አስቴር የተጻፈበት ጊዜ

ጸሐፊው ማን እንደሆነ ስለማይታወቅ፣ መቼ እንደተጻፈ አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ከ200 ዓ.ዓ. በፊት መጻፉን ነው። መጽሐፉ ከ400-350 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ሳይጻፍ አልቀረም። ከዚያ በኋላ የፉሪም በዓል የአይሁድ ብሔራዊ በዓል ሆነ።

የመጽሐፉ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ አጋማሽ ላይ ነው። የተፈጸመውም በዕዝራ 6 ና በዕዝራ 7 መካከል ነው። እንደ መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በይሁዳ ሳይሆን በፋርስ ምድር ነው። እግዚአብሔር በሥራ ላይ የነበረው በይሁዳ ብቻ ሳይሆን፥ በምርኮ በነበሩ አይሁድ መካከልም ነበር።

የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ ንጉሥ የነበረው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ አሕሻዊሮስ በመባል የሚታወቀው ቀዳማዊ አርጤክስስ ነበር። የዚህ ሰው አባት ታላቅ ጦረኛ የነበረውና የፋርስን መንግሥት ክልል በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ያስፋፋው ታላቁ ዳርዮስ ነበር።

አርጤክስስ አዳዲስ ምድርን በወረራ ከመያዝ ይልቅ፥ ትኩረቱ ዋና ከተማ የነበረችውን ሱሳንና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞችን በመሥራት ላይ ነበር። አማካሪዎቹ ግን ግዛቱን እስከ አውሮጳ ድረስ ለማስፋፋት ይችል ዘንድ ግሪክን እንዲወጋ መከሩት፤ ነገር ግን በዚህ ጦርነት አልተሳካለትም። ግሪኮች በጦርነቱ አሸነፉትና አብዛኛውን ጦሩንና የባሕር ኃይሉን ደመሰሱበት።

የዓለም ታሪክ ስለ አርጤክስስ የሚናገረው በርካታ ነገር ቢኖርም አስቴርን ግን የሚጠቅስ ታሪክ የለም። አስጢን የምትባል አንዲት ሚስት እንደ ነበረችውና በኋላም እርሷን በማስወገድ አስቴርን በንግሥትነት እንዳገባ የሚናገር ታሪክም የለም። የዓለም ታሪክ የሚናገረው አሚስቲሪስ ስለተባለች አንዲት ንግሥት ብቻ ነው። ይህ ስም የአስጢን ወይም የአስቴር ሌላ ስም እንደሆነም የምናውቀው ነገር የለም።

የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው ንጉሡ አርጤክስስ ከግሪኮች ጋር ለመዋጋት ወደ ጦር ሜዳ ከመሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ምሁራን የግብዣው ዓላማ በግሪክ ላይ ስለሚደረገው ወረራ ለመነጋገር ነበር ብለው ያስባሉ። አስጢን እንደተወገደች አስቴር ወዲያውኑ ንግሥት ያልሆነችበት ምክንያትም ይህ ሊሆን ይችላል። አስጢን የተወገደችው አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ሲሆን፥ አስቴር ንግሥት የሆነችው ደግሞ በ7ኛው ዓመት ነው። በመካከሉ የ4 ዓመታት ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህም ማለት የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው ከ483-471 ዓ.ዓ. ነበር ማለት ነው።

የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች እና አስተዋጽኦ

የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች

1. መጽሐፈ አስቴር የእግዚአብሔርን ታላቅነትና በዓለም ሕዝብ ሁሉ ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለአይሁድ ለማስተማር የተጻፈ ታሪክ ነው። ጸሐፊው አይሁድን ለማስተማር የፈለገው ነገር፥ ሕዝቡ የሚኖሩት በተስፋይቱ ምድር ሳይሆን በምርኮ ምድር ቢሆንም እንኳ፥ እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ አሁንም ቢሆን ታማኝ መሆኑን ነው፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለማስተማር ጸሐፊው የተጠቀመው የመጽሐፍ ቅዱስን የተለመደ መንገድ አይደለም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ በአጠቃላይ ግልጽ ተአምራትን በማድረግ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያስተማራቸውን እውነቶች እናያለን። እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን የተሻገሩበትንና ፈረዖን ከነሠራዊቱ የሰጠመበትን፥ ሕዝቅያስ ባደረገው ጦርነት እግዚአብሔር 180000 የአሦር ወታደሮችን የደመሰሰበትን ታሪክ እናነባለን። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለማመልከት ጸሓፊው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ስልት ሲጠቀም እናያለን። ጸሐፊው ሆን ብሎ የእግዚአብሔርን ስም አልጠቀሰም። ይልቁንም እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከጥፋት ለማዳን በጣም ጥቃቅንና ኢምንት ናቸው የሚባሉ ድርጊቶችን እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው በተደጋጋሚ ትኩረት ሰጥቶት እናያለን።

ለምሳሌ፡- አስቴር ንግሥት ሆና ለመመረጥና ሕዝቧን ከጥፋት ለማዳን ቻለች። መርዶክዮስ እንደአጋጣሚ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ ለመስማትና ንጉሡን ለማስጠንቀቅ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሰ። ንጉሡ አንድ ለሊት እንቅልፍ ርቆት ስለ መርዶክዮስ እንዲያነብብና የሚያሸልመው ድርጊት እንዲጋለጥ ሆኖ መርዶክዮስ ተሸለመ። አንድ የማያምን ሰው ይህንን ተመልክቶ አይሁድ ከጥፋት ለመዳን ዕድለኞች ሆኑ ቢልም፥ እንደ ጸሐፊው አስተሳሰብ ዕድል የሚባል ነገር የለም። ይልቁንም እግዚአብሔር ጥቃቅን ድርጊቶችን እንኳ በመቆጣጠር ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም ይጠቀምበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች የሆኑት በዕድል ነው ብለው የሚያስቧቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙት በዕድል እንደሆነ የሚያስቡ ክርስቲያኖች አሉን? አብራራ። ሐ) ለዓለም ዕድል ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚመለከቱአቸው እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር አሠራር በማያምኑ ሰዎች ወይም በሥጋዊ ክርስቲያኖች ዘንድ የማይታዩና ለመረዳት የሚያስቸግሩ ቢሆኑም እንኳ በክርስቲያኖች ዘንድ ግን ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡ ናቸው። ለእኛ በሚያደርገው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን እጅ በመሥራት ላይ መሆኑን ማየት መቻል አለብን። የብሉይ ኪዳን ተአምራት በማይፈጸሙበት ጊዜና አይሁድ በዓለም ሁሉ ተሠራጭተው በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር የጥንቱን ዓይነት ተአምራት ባይሠራም አይሁዳውያንን ግን አሁንም እንደደገፋቸው ነበር። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማድረግ ሕዝቡን ይጠብቅ ነበር (ለምሳሌ፡- ዘካ. 1፡2)። እግዚአብሔር የክፉዎችን ዕቅድ ፍሬ ቢስ ለማድረግ ይሠራ ነበር (መዝ. (140)፤ መጽሐፈ ምሳሌ 10፡24-25 አንብብ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአሁኑ ዘመን ክርስቲያኖችስ ይህንን እውነት መረዳት ያለባቸው ለምንድን ነው?

2. አይሁድ ፉሪም የሚባል ዓመታዊ በዓል ነበራቸው። ይህ ቀን ለአይሁድ እጅግ ከተወደዱ በዓላት አንዱ ሆነ። መጽሐፈ አስቴርን በማንበብ፥ በመብላትና በመጠጣት፥ ደግሞም ስጦታን በመለዋወጥ ያከብሩታል። የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ ለአይሁድ የፉሪምን በዓል አጀማመር ለመግለጥ ፈልጓል።

3. እኛ በቀላሉ የምንገነዘበው ባይሆንም፥ ጸሐፊው በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል ስለሚደረገው የማያቋርጥ ጦርነት መናገሩ እንደሆነ አይሁድ ይገነዘቡት ነበር። ከብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ጠላቶቻቸው አማሌቃውያን ነበሩ (ዘጸ. 17፡8-16 ተመልከት)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸው አይሁድን አዘዘ፤ (ዘዳ. 25፡17-19)። አይሁድ ግን ይህንን በማድረግ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፥ በብሉይ ኪዳን ታሪክ በአጠቃላይ በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል የተደረገውን የማያቋርጥ ጦርነት እንመለከታለን (ለምሳሌ. 1ኛ ሳሙ. 15፤ 1ኛ ዜና 4፡43)። በእስራኤላውያን አእምሮ አማሌቃውያን እነርሱንና እግዚአብሔርን ለሚቃወሙ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ሁሉ ተምሳሌት ናቸው። ሐማ ከአማሌቃውያን ወገን እንደመጣ ተገልጦአል (መጽሐፈ አስቴር 3፡1-6፤ 9፡5-10)። የሐማ ዕቅድ እንደ ከሸፈና እርሱም እንደተደመሰሰ በማሳየት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ሁሉ አንድ ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚጠፉ ጸሐፊው አስተምሮአል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ዛሬ እኛን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

የመጽሐፈ አስቴር አስተዋጽኦ

  1. አስጢን ከንግሥትነትዋ ተሻረች (1)
  2. አስቴር ንግሥት ሆነች (2፡1-18)
  3. መርዶክዮስ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ አጋለጠ (2፡19-23)
  4. ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ያወጣው ዕቅድ (3)
  5. መርዶክዮስ የአይሁድን ሕዝብ እንድትረዳ አስቴርን አሳመናት (4)
  6. የአስቴር የመጀመሪያ ግብዣ (5፡1-8)
  7. መርዶክዮስ ተሸለመ (5፡9-6፡14)
  8. የአስቴር ሁለተኛ ግብዣና የሐማ መሰቀል (7)
  9. የአይሁድ ሕዝብ ሕይወት መትረፍና የመርዶክዮስ መሾም (8-10)

5ኛ ጥያቄ፥ ስለ አስቴር ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ፤ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችንም ዘርዝር።

አስቴር 1-6

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም የሚሠራው እንዴት ነው? ብዙ ጊዜ ቀይ ባሕርን እንደመክፈል ያሉ ታላላቅ ተአምራትን ይሠራልን? ብዙ ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ይህንን የመሳሰሉ ታላላቅ ተአምራትን እንዲሠራ እንፈልጋለን። በመሆኑም በልሳን መናገርና ፈውስን ወደ መሳሰሉ አስደናቂ ተግባራት እንሳባለን። አዎን እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን በመካከላችን በታላላቅ መንገዶች ይሠራል፤ ነገር ግን ለአስደናቂ ነገሮች ብቻ ትኩረት በመስጠታችን፥ እግዚአብሒር በተለመዱ ጥቃቅን ነገሮችም ውስጥ እንደሚሠራ እንዘነጋለን። እግዚአብሔር የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውሳኔ በመቆጣጠር ይሠራል። እግዚአብሔር ለወንጌል ሥራ ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጡ በሚችሉበት ትክክለኛ ስፍራ ልጆቹን በማስቀመጥ ይሠራል። እግዚአብሔር ልናስባቸው በማንችል በሕይወታችን በሚፈጸሙ ጥቃቅን ነገሮች ውስጥ እንኳ ሲሠራ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፥ በየቀኑ ሊጎበኙን የሚመጡ ሰዎችን የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። በመንገድም ሆነ በቢሮ የሚመጡትንና የሚገናኙንን ሰዎች የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በአስደናቂ ነገሮች ላይ ብቻ የምናተኩር መሆን የለብንም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በሚያደርጋቸው ዕለታዊ የተለመዱ ነገሮችም ላይ ማተኮር ያስፈልገናል። በሕይወታችን የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሔር መሪነት የሚከናወኑ ናቸው። እነዚህ ለእኛ በጣም ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ልናስተውላቸው እስከማንችል ድረስ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥

  1. ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩባቸውን የእግዚአብሔርን ኃይል የሚያሳዩ አስደናቂ ሁኔታዎች የሚገልጹ ነገሮችን ዘርዝር
  2. እግዚአብሔር በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች የማይገነዘቡአቸውን ተራና የተለምዶ የሚመስሉ ነገሮችን ዘርዝር።
  3. ተአምራታዊ ከሆኑ መንገዶች ይልቅ በእነዚህ የተለመዱ ነገሮች ላይ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ሌሎች የበለጠ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ልብ ልትላቸው የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

የውይይት ጥያቄ፥ አስቴር 1-6 አንብብ።

  1. በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተገለጹትን ዋና ዋና ድርጊቶች ዘርዝር።
  2. ለአይሁድ ሕዝብ ጥቅም ሲል እግዚአብሔር እንዴት በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ጥቃቅን ነገሮችን ዘርዝር።

አስቴር 1-6 የአስቴርን ታሪክ የተለያዩ ደረጃዎች ያሳያል። በፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተፈጸሙ ጨርሶ የማይገናኙ የሚመስሉ ነገሮችን ይዟል። እነዚህ ታሪኮች ሲነገሩንም ለዋናው ታሪክ ያላቸው አስፈላጊነት አልተጠቀሰም። ለታሪኩ መሠረት የሆነው ዋናው ነገር በሓማ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤላዊያን ጠላትና በአስቴርና በመርዶክዮስ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ያለውን ትግል ነው። ቀጥሎ ይህንን ትግልና በባዕድ ምድር ሕዝቡን ለመታደግ በመሥራት ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን እጅ የሚያሳዩትን ነገሮች አስተውል።

1. ንግሥት አስጢን: ከንግሥትነት ሥልጣንዋ ተወግዳ አንዲት የማትታወቅ አስቴር የተባለች ሴት የምትቀጥለዋ የፋርስ ንግሥት ሆና ተመረጠች። ይህ በጣም አስፈላጊ የነበረው በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግና የአይሁድን ሕዝብ ከጠቅላላ ጥፋት ለማዳን የቻለች ንግሥት አስቴር ስለነበረች ነው። እግዚአብሔር በአንድ የአሕዛብ ግብዣ ተጠቅሞ አንዲት ንግሥት እንድትወገድና ሕዝቧን ለማዳን እንድትችል አስቴር ንግሥት እንድትሆን አደረገ።

2. የአስቴር አጎት: የነበረው መርዶክዮስ ንጉሡን ለመግደል የተደረገውን ሴራ ሰማና ይህንን ለንጉሡ ነገረ። መርዶክዮስ ይህን ሴራ በማክሸፉ ረገድ ያበረከተው በቤተ መንግሥቱ መዛግብት ውስጥ ተጻፈ። ይህ መረጃ የአይሁድ ሕዝብ ጠላት የነበረው ሐማ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር በተገደደበት ጊዜ አስፈላጊ ሆነ። የንጉሡ የግል አማካሪ የነበረውን የሐማ ስፍራ የወሰደም መርዶክዮስ ነበር። በዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ እናያለን። እግዚአብሔር ንጉሡ እንዳይገደል አደረገ፤ ቢገደልም ኖሮ አስቴር በአዲሱ ንጉሥ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ አትችልም ነበር። እግዚአብሔር ሴራውን ሊያከሽፍ በሚችልበት ትክክለኛ ስፍራ ላይ መርዶክዮስን አስቀመጠው። በኋላም የመርዶክዮስን ሥራ እግዚአብሔር ለንጉሥ አስታወሰና በፋርስ መንግሥት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ስፍራ በማስቀመጥ እንዲያከብረው አደረገ።

3. አጋጋዊው ሐማ: ያለ ምንም ምክንያት የጠላቸውን የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ሴራ አሴረ። እንደምታስታውሰው፥ አጋግ ከአማሌቃውያን ነገሥታት አንዱ ነበር (1ኛ ሳሙ. 15፡20)፤ ስለዚህ ሐማም አማሌቃዊ መሆኑን መገመት ትክክል ነው። ሐማ በምድሪቱ ያሉትን አይሁድ በሙሉ ለማጥፋት ከአርጤክስስ ፈቃድ አገኘ።

4. መርዶክዮስ አይሁድን: ለማዳን የምትችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባት አስቴርን አሳመናት፡ አስቴር 4፣14 በመጽሐፉ ውስጥ ያለ ቁልፍ ጥቅስ ነው። ስለ ሕይወቷ ለፈራችው ለአስቴር መርዶክዮስ እንዲህ አላት፡- «አንቺ፡- በንጉሥ ቤት ሰለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?» በዚህ ንግግር ውስጥ ሁለት እውነቶችን እናያለን። የመጀመሪያው፥ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ያደረገው እግዚአብሔር የአይሁድ ሕዝብ እንዳሉ እንዲጠፉ እንደማይፈቅድ መርዶክዮስ ያውቅ እንደ ነበር ነው። ብዙ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ፥ እግዚአብሔር አይሁድን ሙሉ ለሙሉ ከመጥፋት ሁልጊዜ ይጠብቃቸዋል።

ሁለተኛው ነገር እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም ግለሰቦችን በልዩ የኃላፊነት ስፍራ በማስቀመጥ እንደሚጠቀምባቸው መርዶክዮስ ተገንዝቦ ነበር። መርዶክዮስ አስቴር ንግሥት የሆነችው በዕድል እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። አስቴርን የፋርስ ንግሥት በማድረግ አይሁድን ለማዳን ሊጠቀምባት የወደደው እግዚአብሔር እንደሆነ መረዳት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ጠቃሚ የሆኑ ክርስቲያኖችን ትክክለኛ በሆነ የአመራር ስፍራ በማስቀመጥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንዴት እንደተጠቀመባቸው የሚያሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ተመሳሳይ ሁኔታ ስጥ።

5. አስቴር ወደ ንጉሡ በመሄድ: ወደ አዘጋጀችው ግብዣ እንዲመጣ ጠየቀችው። በፋርስ ባሕል ማንም ሰው ንግሥቲቱም ብትሆን እንኳ ያለ ንጉሡ ጥሪ እርሱ ወዳለበት መግባት አይችልም ነበር። አስቴር ወደ ንጉሡ በመግባቷ በትረ መንግሥቱን የምታመለክተውን በትር ወደ እርሷ ካልዘረጋላት ሕይወቷን እንኳ ልታጣ እንደምትችል ታውቅ ነበር፤ ነገር ግን የእርሷ ሕይወት ከወገኖች ሁሉ ሕይወት እንደማይበልጥ ተገነዘበች። ስለዚህ በፈቃዴ ወደ ንጉሡ ገባች። ይህንን ከማድረጓ በፊት ግን እግዚአብሔር በሥራዋ የተዋጣለት ያደርጋት ዘንድ አይሁድ ሁሉ እንዲጾሙና እንዲጸልዩ ጠይቃ ነበር። አስቴር፥ በንጉሡ ፊት ሞገስ እንድታገኝ ሊያደርግ የሚችል እግዚአብሔር እንደሆነ ታውቅ ነበር! ስለዚህ አይሁድ ሁሉ እንዲጸልዩላት ጠየቀች። እግዚአብሔር ጸሎቷን አከበረ። እንዲሁም በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ የነበራትን እምነት ሕይወቷን እንኳ ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆኗን በንጉሡ ፊት ሞገስ በመስጠት አከበረላት።

6. ለእርሱ ክብር ለመስጠት: መርዶክዮስ ባለመስገዱ ሐማ ተቆጣ። ስለዚህ ለመርዶክዮስ የመስቀያ ግንድ አዘጋጀ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን ለመስቀል ከንጉሥ ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት፥ እግዚአብሔር ለንጉሡ እንቅልፍ በመከልከል መርዶክዮስ ሕይወቱን ማዳኑን እንዲያስታውስ አደረገው። በዚያን ጊዜ ሐማ፥ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር ተገደደ፤ ስለዚህ ጸሐፊው የማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቢጠሉም እንኳ አንድ ቀን ሊያከብሯቸው እንደሚገደዱ ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ፊልጵ. 2፡9-11 አንብብ። የኢየሱስ ጠላቶች አንድ ቀን እርሱን እንዲያከብሩት የሚገደዱት እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፥

  1. ከዚህ የመጽሐፈ አስቴር ክፍል የምንማራቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር።
  2. እነዚህ እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች በሚመለከት ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አስቴር 7-12

የውይይት ጥያቄ፡ ምሳሌ 21፡1 አንብብ።

  1. እግዚአብሔር በምድር መሪዎች ላይ ስላለው ቁጥጥር ይህ ጥቅስ ምን ያስተምረናል?
  2. ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር በሚሠሩበት ጊዜ ይህ ነገር እንዴት ማበረታቻ ይሆናቸዋል?
  3. ይህ ነገር ሲፈጸም እንዴት እንዳየህ ምሳሌዎችን ስጥ።

እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ብሎ ሁልጊዜ የሚሠራ መሆኑን አይተናል። ተአምራትን ባናይም እንኳ እግዚአብሔር በሥራ ላይ አይደለም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ የሚሠራው ሕዝቡ እንኳ በማያውቁት መንገድ ነው። ክርስቲያኖች ግን ዕድል ወይም አጋጣሚ የሚባል ነገር እንደሌለ መገንዘብ አለባቸው። ይልቁንም ጸጋን የተሞላው ሰማያዊ አባታችን ለክብሩ፥ ለመንግሥቱና ለሕዝቡ ሲል ነገሮችን ሁሉ እየተቆጣጠረ ይሠራል።

መጽሐፈ አስቴር፥ እግዚአብሔር በአስቴር ዘመን ይህንን ለአይሁድ እንዴት እንዳደረገላቸው የሚገልጥ ሥዕላዊ ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ጠላቶች፥ የእርሱን ሕዝብ አይሁድን ለማጥፋት ቢወስኑም እንኳ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን በአንዲት ሴት በመጠቀም በጸጥታ ሠራ።

የውይይት ጥያቄ፥ አስቴር 7-12 አንብብ።

  1. አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት ያዳነችው እንዴት ነው?
  2. በዚህኛው የአስቴር ታሪክ ክፍል የእግዚአብሔር እጅ የታየው እንዴት ነው?
  3. ከዚህ ታሪክ የምንማረው መንፈሳዊ ትምህርት ምንድን ነው?

አስቴር 1-6 እስራኤላውያን ራሳቸውን ያገኙበትን አደገኛ ሁኔታ የሚገልጥ ሲሆን፥ አስቴር 7-12 ግን እግዚአብሔር የሐማና የጠላቶቹን ዕቅድ ለማፈራረስ እንዴት እንደሠራና ሕዝቡን እንደጠበቀ ይገልጣል። የሚከተሉትን ትምህርቶች ተመልከት፡-

1. አስቴር፥ እርስዋንና ሕዝቧን ያለ ምንም ምክንያት ሊገድል ማሰቡን በመናገር ሐማን ከሰሰችው። በውጤቱም ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው ግንድ ላይ ተሰቀለ (መዝ. (28)፡1-5 ተመልከት)።

2. ንጉሥ አርጤክስስ በመንግሥቱ ሁሉ አይሁድን ለመዋጋት በሚያስቡ (ወይም በሚሞክሩ) ጠላቶቻቸው ሁሉ ላይ የመስቀል ሥልጣን ለአይሁድ እንደተሰጣቸው የሚገልጥ ትእዛዝ አስተላለፈ። ንጉሡም መርዶክዮስን የቅርብ አማካሪው አደረገው። በአንድ ወቅት በቤተ መንግሥት የሐማ የነበረውን የክብር ስፍራ መርዶክዮስ ወሰደ።

3. አይሁድ በጠላታቸው በሐማ ላይ ስላገኙት ድል የፉሪምን በዓል አከበሩ። ፉሪም የሚለው ቃል «ፉር» ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን፥ ትርጉሙም ዕጣ ማለት ነው። ይህም የሚያመለክተው ሐማና ንጉሡ አይሁድን ስለሚያጠፉበት ቀን ለመወሰን ያወጡትን ዕጣ ነው (አስቴር 3፡7)። እስራኤላውያንን ለማጥፋት ሐማ ዕጣ ቢጠቀምም እግዚአብሔር ግን ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ዕጣው በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ወደቀና ብዙ ሺህ አሕዛብ ተገደሉ። አይሁድ ዛሬም ይህንን በዓል በታላቅ ደስታ ያከብሩታል። በዚህ በዓል ዕለት መጽሐፈ አስቴር ለቤተሰቡ አባላት በሙሉ ይነበባል።

የመጽሐፈ አስቴር ዋና ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የግለሰቦች ታሪክ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል የሚካሄድ ጦርነት ታሪክ ነው። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የዚህን ጦርነት ፍንጮች እናያለን። ሰይጣን በጦርነቱ ለመዋጋት የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀምም ዓላማው ሁልጊዜ አንድ ነው። የእግዚአብሔርን ዕቅድና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ይፈልጋል።

በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ሁሉ ሰይጣን የደኅንነት መስመር እንዲቋረጥ ለማድረግ በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማበላሸት ታግሏል። ከዘፍ. 3፡15 እንደምታስታውሰው፥ ከሴቲቱ ዘር ሰይጣንን የሚያጠፋ ሰው እንደሚመጣ እግዚአሔር ተስፋ ሰጥቷል። ሰይጣን የሴቲቱ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ስለሚያውቅ የሚመጣበትን የዘር ግንድ ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ የግብፅ ንጉሥ ሣራን በሚስትነት እንዲወስድ በማድረግ የአብርሃምን የዘር ግንድ ለማቋረጥ ሞክሮ ነበር። ርብቃንም መኻን በማድረግ የዘር ሐረጉ እንዲያበቃ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። በኋላም ሰይጣን የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በራብ ለመጨረስ የሞከረ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን በዮሴፍ በኩል እነርሱን ታድጎአቸዋል። በኋላም መሢሑ የሚመጣው በእርሱ በኩል መሆኑን እግዚአብሔር ለዳዊት ነግሮታል (2ኛ ሳሙ. 7፡14)። ሰይጣን ግን የዳዊትንም ዘር ለማጥፋት በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሊያበላሽ ጥሮ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ እግዚአብሔር ካዳነው ከአንድ ትውልድ በቀር ጎተልያ የዳዊትን ዘር በሙሉ አጥፍታ ነበር፤ (2ኛ ነገ. 11፡1-3)። አሁን ደግሞ በአስቴር ታሪክ ሰይጣን ሐማ የተባለውን የአንድ ሰው ጥላቻ በመጠቀም አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። አይሁድ ተደምስሰው ቢሆን ኖሮ መሢሑ ባልተወለደና ዓለምም አዳኝን ባላገኘ ነበር። እግዚአብሔር ግን የሰይጣንን ዕቅድ አከሸፈ።

ይህ እውነት ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን አንዳንድ የአይሁድ ታሪክ ለመረዳት ይጠቅመናል። በየትኛውም ስፍራ ይሁኑ አይሁድ ሁልጊዜ የሚሰደዱ ሰዎች ነበሩ። ይህም በተለይ የታየው በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሂትለርና ጀርመኖች ከ6 ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያንን ቢገድሉም፥ እግዚአብሔር ግን አሁንም ቢሆን ለአይሁድ ሕዝብ ዕቅድ ስላለው ሙሉ በሙሉ ሊያጠፏቸው ባለመቻሉ ነው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ በታሪክ ሁሉ ቅሬታዎችን በመጠበቅ አንድ ቀን ሊጎበኛቸውና በመካከላቸው ታላቅ ሥራን ሊያደርግ ዕቅድ አለው (ሮሜ 11 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥

  1. የማያምኑ ሰዎች ከክርስቲያኖች ጋር የሚታገሉትና ሊያጠፏቸው የሚሹት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይህ እውነት እንዴት ይረዳናል?
  2. ይህ እውነት በተጨማሪ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ እግዚአብሔር እንደማይፈቅድ ምን ያስተምረናል?

የታሪክ መጻሕፍት ክለሳ

እስካሁን ድረስ ባካሄድነው ጥናታችን ሁለት ዋና ዋና የብሉይ ኪዳን ክፍሎችን ተመልክተናል። በመጀመሪያ ፔንታቱክ በሚል ስም የታወቁትን በሙሴ የተጻፉትን አምስቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ተመልክተናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አሥራ ሁለቱን የታሪክ መጻሕፍትን ተመልክተናል። እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉት በተለያዩ ያልታወቁ ጸሐፊዎች ነበር። የሚናገሩትም በብሉይ ኪዳን ያሉትን የቀሩትን የእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ነው። ታሪኩም ከ1400 እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። እነዚህ 12 መጻሕፍት የ1000 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናሉ። ታዲያ ሁሉም የታሪክ መጻሕፍት ቢሆንም በትምህርት ቤት እንደምንማራቸው የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉ አይደሉም። ይልቁንም እያንዳንዱ መጽሐፍ የተጻፈው መንፈሳዊ እውነትን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለማስተማር ነው። ከእነዚህ መጻሕፍት በምናነብበት፥ በምናጠናበትና በምንሰብክበት ጊዜ በውስጣቸው ያለው መንፈሳዊ እውነት ምን እንደሆነ ልንረዳና ለቤተ ክርስቲያን አባሎቻችን ልናስተምር ይገባናል።

የውይይት ጥያቄ፥

  1. 12ቱን የታሪክ መጻሕፍት ዘርዝር።
  2. እያንዳንዱን መጽሐፍ በሚመለከት መጽሐፉ የሚናገራቸውን ዋና ዋና የታሪክ ወቅቶች ዘርዝር። 
  3. በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ገጸ ባሕርያትን ግለጥ፡
  4. በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር።

የሚከተሉትን መጻሕፍት ዝርዝር ተመልከት

1. ኢያሱ፡- እንደምታስታውሰው ኢያሱ ሙሴ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ መሪ ነበር። ሕዝቡን ወደ ከነዓን ለመምራትና በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማሸነፍ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር። ኢያሱ በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። በኢያሱ ዘመን የተገኘው ድል አብዛኛው በምድራዊ ጠላቶች ላይ ነበር፤ ለእኛ ግን በመንፈሳዊ ጠላቶቻችን ላይ ስለሚገኝ ድል የሚያስተምረን ነው።

2. መሳፍንትና ሩት፡- ዘመነ መሳፍንት ኢያሱ ከሞተ አንሥቶ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ እስከ ሳኦል ዘመን ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን ወደ 400 ዓመታት ይጠጋል። የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና አሳብ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳ. 17፡6፤ 21፡25) በሚለው ጥቅስ ውስጥ ይገኛል። አይሁድ እግዚአብሔርን በመካድ የሐሰት አማልክትን (ጣዖታትን) የተከተሉበት የክሕደት ጊዜ ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት አይሁድ ያለፉበትን የውድቀት ሂደት ይናገራል። በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው በከነዓናውያን እጅ አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። ሦስተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ በባርነት ቀንበር ሥር ቆዩ። አራተኛ፥ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ እንዲያወጣቸው ወደ እርሱ ጮኹ። አምስተኛ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ የሆነ መስፍንን ወይም የጦር መሪን በማስነሣት ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና እንደገና ኃጢአት ሠርተው እስኪፈረድባቸው ድረስ የነፃነት ዘመን ሰጣቸው። በዚህ ዘመን የተነሡ ዋና ዋና መሳፍንት ናትናኤል፥ ናዖድ፥ ዲቦራና ባርቅ፥ ጌዴዎን፥ ዮፍታሔና ሶምሶን ነበሩ። የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመው በዘመነ መሳፍንት ሲሆን፥ አብዛኛው ሕዝብ እንዴት እግዚአብሔርን እንዳላከበረና በዚህ ዓይነት ጨለማ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ጥቂት ሰዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ነው።

3. 1ኛ ሳሙኤል፡- 1ኛ ሳሙኤል እስራኤል ከዘመነ መሳፍንት በአንድ ንጉሥ ሥር አንድ መንግሥት ሆና ትተዳደር ወደነበረችበት ወደ ነገሥታት ዘመን ስላደረገችው የሽግግር ጊዜ የሚናገር መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የእስራኤል የመጨረሻ መሳፍንት ስለሆኑት ስለ ዔሊና ስለ ሳሙኤል ይገልጣል። በተጨማሪ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ስለሆነው ስለ ሳኦልም ይናገራል። ስለ ሳኦል ውድቀትና ተከታዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እግዚአብሔር ዳዊትን እንዴት እንደመረጠው ይናገራል። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የሚናገረው ስለ ዳዊት ዝና አጀማመርና ሳኦልም ዳዊትን ለመግደል ስላደረጋቸው የተለያዩ ሙከራዎች ነው።

4. 2ኛ ሳሙኤልና 1ኛ ዜና መዋዕል፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የሚሸፍኑት ተመሳሳይ ጊዜያትን ነው። የሚናገሩትም በእስራኤል ተወዳዳሪ ስላልተገኘለት ስለ ታላቁ ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ለዳዊት የዘላለም ቃል ኪዳንን በመግባት በእስራኤል ሁሉ ላይ ገዥ የመሆን መብትን ለዘሩ እንደ ሰጠ እንመለከታለን። ይህንን ቃል ኪዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚፈጽመው አይተናል። እነዚህ መጻሕፍት በዳዊት ሕይወት ስለታየው መንፈሳዊ ታላቅነትና ወታደራዊ ኃይል ይናገራሉ። 2ኛ ሳሙኤል በዳዊት ወታደራዊ ታላቅነትና ኃጢአት ላይ ሲያተኩር፥ 1ኛ ዜና የሚያተኩረው ደግሞ በዳዊት መንፈሳዊ ሕይወትና ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድና ለቤተ መቅደሱ ሥራ ዝግጅት በማድረግ እግዚአብሔርን እንዴት እንዳከበረ በመናገር ላይ ነው።

5. 1ኛ ነገሥትና 2ኛ ዜና መዋዕል 1-18፡- እነዚህ መጻሕፍት ከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ወደ ተከፋፈለው መንግሥት የተደረገውን የሽግግር ዘመን የሚናገሩ ናቸው። የሁለቱም መጻሕፍት የመጀመሪያ ክፍሎች የሚናገሩት ጠቢብ ስለነበረው ስለ ዳዊት ልጅ ስለ ሰሎሞን ነው። 1ኛ ነገሥት እስራኤልን ወደ ክሕደት በመምራት የእስራኤልን መንግሥት በሁለት ስለከፈለው ስለ ሰሎሞን ኃጢአት ይናገራል። 2ኛ ዜና መዋዕል ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንዴት እንደሠራ ይናገራል። ቀጥሉ እነዚህ መጻሕፍት የሚናገሩት አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት እንዴት ለሁለት እንደተከፈለ ነው። በስተ ሰሜን የሚገኙት አሥሩ ነገዶች እስራኤል ተብለው የተጠሩ ሲሆን፥ ዋና ከተማቸውም ሰማርያ ነበረች። የብንያምና የይሁዳን ነገዶች የያዙት ሁለቱ ነገዶች ዋና ከተማቸውን ኢየሩሳሌም በማድረግ የይሁዳን መንግሥት መሠረቱ። 1ኛ ነገሥት የሰሜኑንና የደቡቡን መንግሥታት የተለያዩ ነገሥታት በአጭር በአጭሩ ሲያቀርብ፥ 2ኛ ዜና ደግሞ ያተኮረው በደቡብ መንግሥት ነገሥታት ላይ ነው። እንደዚሁም 1ኛ ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ 2ኛ ዜና የሚያተኩረው ግን በሌዋውያን ሥራ ላይ ነው።

6. 2ኛ ነገሥትና 2ኛ ዜና መዋዕል 19-36፡- እነዚህ መጻሕፍት የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል በ722 ዓ.ዓ. በአሦር መንግሥት መደምሰሱንና የይሁዳ መንግሥት የሚባለው የደቡብ መንግሥት ደግሞ በ586 በባቢሎናውያን መማረኩን ይናገራሉ። 2ኛ ነገሥት የሚናገረው ስለ ሰሜኑና ላለ ደቡቡ መንግሥት ሲሆን 2ኛ ዜና የሚያተኩረው ግን በደቡቡ መንግሥት ላይ ሆኖ በተለይ ደግሞ በይሁዳ እውነተኛ አምልኮን ለመመለስ የተሐድሶ ሥራ በሠሩ እግዚአብሔርን በሚፈሩ መሪዎች ታሪክ ላይ ነው። 2ኛ ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ማተኮሩን ሲቀጥል፥ 2ኛ ዜና ግን ስለ ሌዋውያን ሥራ ይናገራል።

7. መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር፡- እነዚህ ሦስት መጻሕፍት የሚናገሩት ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በኋላና አይሁድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ ስላለው ጊዜ ነው። ዕዝራና ነህምያ የሚያተኩሩት ከምርኮ ወደ ይሁዳ በተመለሱት አይሁድ ላይ ነው። መጽሐፈ ዕዝራ በዕዝራና በዘሩባቤል መሪነት የተመለሱትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት የእስራኤል ቡድኖች የሚገልጽ ሲሆን፥ በተጨማሪ ስለ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ መሠራትና ዕዝራ በይሁዳ ስለመራው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ ነህምያ ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራትና ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሰሙ ጊዜ በመካከላቸው ስለተፈጸመው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር የሚያተኩረው በምርኮ ምድር በነበሩ አይሁድ::

ላይ ነው። መጽሐፉ እዚአብሔር ሕዝቡን በቸርነቱ የፋርስ ንግሥት አድርጎ ባስቀመጣት በአስቴር አማካይነት ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸውና የሐማን ዕቅድ እንዳከሸፈ ይናገራል። የብሉይ ኪዳን ጥናት የመጀመሪያ ክፍል የሆነውን የዚህን መጽሐፍ ጥናት የመጨረሻውን ፈተና ለመውሰድ ተዘጋጅ። የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሚቀጥለው ጥናት እንመለከታለን።

 

መጽሐፈ ሩት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ከመጽሐፍት ዓለም

መጽሐፈ ሩት 

መግቢያ
በየትኛውም ዘመን፥ ምንም ያህል ጊዜው ጨለማ ቢሆን፥ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ የተመረጡ ሕዝቦች አሉት። አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረውን ኑሮ እየተቃወሙ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሕይወት የሚኖሩ ጥቂት ታማኞች አሉ፤ በመጽሐፈ ሩት ውስጥ የምናየው ነገር ይህ ነው። ዘመነ መሳፍንት በአጠቃላይ ሲታይ እጅግ የከፋ ቢሆንም፥ በእስራኤል ውስጥ እግዚአብሔርን ያከበሩ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። መጽሐፈ ሩት የእነዚህን ጥቂት ሰዎች እምነትና እግዚአብሔር እንዴት ለእነርሱ መልካም እንዳደረገላቸው የሚያሳይ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር የሆኑ ቅሬታዎች ወይም ጥቂት ታማኞች የመኖራቸውን እውነትነት በሕይወትህ እንዴት አየኸው?
የውይይት ጥያቄ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ መጽሐፈ ሩትን ተመልከት፤ ስለዚህ መጽሐፍ የሚናገራቸውን ዋና ዋና ነገሮች ዘርዝር።


የመጽሐፈ ሩት ስያሜ
መጽሐፈ ሩት የተሰየመው በመጽሐፉ ታሪክ ዋና ገጸ ባሕርይ በሆነችው በሩት ነው። አስቴርን ጨምሮ በሴት ስም ከተሰየሙ ሁለት መጻሕፍት መካከል መጽሐፈ ሩት አንዱ ነው።


የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ
የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ ማን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ምንም መረጃ የለም። የአይሁድ ትውፊት መጽሐፉን የጻፈው ሳሙኤል ነው ይላል። የመጽሐፉ የመጨረሻ ትኩረት በዳዊት ላይ ስለሆነ፣ ጸሐፊው ሳሙኤል አይመስልም። ስለዚህ በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ ወይም ከዚያ ጥቂት ራቅ ብሎ፥ እግዚአብሔር የዳዊትን የዘር ግንድ ለመጠበቅ እንዴት እንደሠራ ለመግለጽ የሚፈልግ አንድ ሰው እንደጻፈው ይገመታል። ሩት 1፡1 የዘመነ መሳፍንት ፍጻሜን የሚያሳይ ይመስላል። የዳዊት ስም በመጽሐፉ መጨረሻ መጠቀሱ ሕዝቡ ዳዊትን ያውቁት እንደነበር ያሳያል።


የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመበት ጊዜ
የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመው በዘመነ መሳፍንት ነው። በዘመነ መሳፍንት በየትኛው ጊዜ እንደተፈጸመ የምናውቀው ነገር የለም። አንዳንድ ምሁራን ዮፍታሔ በነበረበት ዘመን አካባቢ የተፈጸመ ነው ብለው ይገምታሉ።


የመጽሐፈ ሩት አስተዋጽኦ

  1. በአቤሜሌክ ቤተሰብ ላይ የደረሰው መከራና ኃዘን (1፡1-5)
  2. ኑኃሚንና ሩት ወደ ቤተልሔም ተመለሱ (1፡6-22)
  3. ሩት ቦዔዝን በመከር መሰብሰቢያ ስፍራ አገኘችው (2)
  4. ሩት ወደ ቦዔዝ የአውድማ ስፍራ በመሄድ እንዲያገባት ጠየቀችው (3)
  5. ቦዔዝ ሩትን አገባ፤ ወንድ ልጅም ወለዱ (4፡1-17)
  6. የዳዊት የዘር ሐረግ (4፡18-22)።

የመጽሐፈ ሩት ዓላማ
የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር መጽሐፈ ሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን ይመስልሃል? መጽሐፈ ሩት ለምን እንደተጻፈና በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንደተካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይከራከራሉ። ስለዚህ ጉዳይ ሦስት ዋና ዋና አመለካከቶች አሉ፡- 

  1. መጽሐፈ ሩት የተጻፈው የዳዊትን አያቶችና ቅድመ አያቶች በመናገር፥ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ የዳዊትን የዘር ግንድ እንዴት እንደጠበቀ ለማሳየት ነው። አንዳንዶች የሩትና የቦዔዝ ታሪክ ዳዊት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳየት የተጻፈ ነው ይላሉ። ኑኃሚን ከባዶነት ወደ ሙላት (1፡2)። ከከፍተኛ ራብና ችግር (1፡1-5)፥ ወደ ደኅንነትና ተስፋ (4፡13-17) እንደተመለሰች ሁሉ፥ ራስ ወዳድ ባልሆነው በዳዊት አመራር የእስራኤል ሕዝብ ከብሔራዊ አደጋ ወደ ሰላምና ብልጥግና ተመልሰዋል። በዚህ ዓይነት ዳዊት እውነተኛው የሩትና የቦዔዝ ልጅ መሆኑ ታየ። ይህ የመጽሐፉ ዓላማ ሊሆን የሚችል ነው ቢባልም ዋናው የመጽሐፉ ዓላማ ግን አይደለም።
  2. መጽሐፈ ሩት የተጻፈው አይሁድ አሕዛብን ወደ ይሁዲነት እምነት ለመለወጥ መሞከር እንዳለባቸው ለማስተማርና አሕዛብም እግዚአብሔርን በእውነተኛ እምነት ሊያመልኩ እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር። ይህም ቢሆን የመጽሐፉ ዋና ዓላማ መሆን የሚያጠራጥር ነው።
  3. መጽሐፈ ሩት የሚያስተምረው፥ አጠቃላይ የሆነ ክሕደት ባለበት ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው። ብዙ ክፋት ባለበት ስፍራ እምነት ሊኖር ይችላል። እግዚአብሔር የእነዚህን ጥቂት ሰዎች እምነት ስለሚያከብር፥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታም ውስጥ ጠበቃቸው። ከሦስቱ አመለካከቶች መካከል የመጽሐፈ ሩት ዋና ዓላማ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
    መጽሐፈ ሩትን ለመረዳት፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት ቀጥሎ መምጣቱንና ዘመነ መሳፍንት ደግሞ ከፍተኛ ክፋትና የሥነ - ምግባር ብልሽት የታየበት ዘመን መሆኑን ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ መጽሐፍ ንጉሥ ያልነበረበትን የዚህ ዘመን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳይ ነው።
    መጽሐፈ ሩት፥ አብዛኛው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከነበረበት አሳዛኝ ክሕደት ጋር በተነጻጻሪነት የቀረበ ታሪክ ነው። የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ በታላቅ ክፋት መካከል ጨርሶ ባልተጠበቀ ስፍራ፣ ባልታሰቡ ሰዎች ልብ ውስጥ እምነት ሊኖር እንደሚችል በብዙ ንጽጽር ያሳየናል። ጸሐፊው በርካታ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም እውነተኛ እምነት በጥቂት ታማኝ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያመጣውን ለውጥ ያሳያል። የሚከተሉትን ተመልከት፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁድ የእግዚአብሐርን ንጉሥነት እምቢ ብለው ጣዖታትን አመለኩ። (ዘመነ መሳፍንት)
    1. የተናቀችው የአሕዛብ ወገን እውነተኛውን እግዚአብሔርን ለመከተል የጣዖት አምልኮን ተወች፡፡ (መጽሐፈ ሩት)
    2. ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በሕዝቡ ሕይወት በሚታየው ታላቅ ክፋት ላይ ነው።
    2. መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ እንደ ሩትና ቦዔዝ ባሉት ጥቂት ግለሰቦች እምነት ላይ ነው።
    3. ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በወንዶችና በኃጢአተኛነታቸው ላይ ነው፡፡
    3. መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ በሴቶችና በእግዚአብሔር ባላቸው እምነት ላይ ነው።
    4. ዘመነ መሳፍንት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣ ያሳያል፡፡
    4. መጽሐፈ ሩት እግዚአብሔር፥ እምነታቸውን በእርሱ ላይ ለሚያደርጉ ሰዎች ታማኝ መሆኑን ያሳያል።
    መጽሐፈ ሩት የሚመደበው «አጭር ታሪክ» ተብሎ ከሚጠራ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ነው። የታሪኩ ዓላማ ትልቅ የሃይማኖት መሠረታዊ ትምህርት ለማስተማር አይደለም፤ ነገር ግን በክፋት መካከል ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን እምነትና በመታዘዝ ለሚከተሉት እግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ለማሳየት ነው። ታሪኩ፥ እውነተኛ እምነት ተራ በሆኑ በታማኝ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እንደሚመስል ይገልጣል።
    የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 1፡18-31 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ተራ ሰዎችን በመጠቀም ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ምንድን ነው ይላሉ? ለ) እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል? ሐ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሲፈጸም የምታየው እንዴት ነው? መ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሀብታሞች ወይም በተማሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ስለማድረግ ይህ ምን ያስተምረናል? ሠ) ብዙ ጊዜ ተራ ሰዎች እውነተኛ እምነትና ታላቅ መንፈሳዊነት ለጥቂት የተማሩ ሰዎች ብቻ ነው ብለው የሚያስቡት በምን መንገድ ነው? ረ) እግዚአብሔር የተራ ሰዎችን እምነት እንደሚያከብር መጽሐፈ ሩት ምን ያስተምረናል?
    የውይይት ጥያቄ፥ ሩት 1-4 አንብብ። ሀ) የአቤሜሌክ ቤተሰብ ወደ ሞዓብ የሄደው ለምን ነበር? ለ) የሩትን እምነት ከዖርፋ እምነት ጋር አወዳድር። የሩት እምነት ታላቅ የሆነው እንዴት ነው? ሐ) ሩት ለኑኃሚን ታማኝ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነበር? መ) እግዚአብሔር ሩት ለኑኃሚን ያሳየችውን ታማኝነት ያከበረውና ዋጋ የሰጠው እንዴት ነበር? ሠ) ከዚህ ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ ሊኖረን ስለሚገባ ታማኝነትና እግዚአብሔር ለልጆቹ ስላለው ታማኝነት ልንማር የምንችለው ነገር ምንድን ነው?

    መጽሐፈ ሩት (1-4)
    1. የሩት ታሪክ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ (ሩት 1)
    መጽሐፈ ሩት የሚጀምረው ታሪኩ በዘመነ መሳፍንት ወቅት የተፈጸመ መሆኑን በመናገር ነው። በይሁዳ ግዛት ራብ እንደተነሣ ይናገራል። የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ራብን የተጠቀመበት በአቤሜሌክ ቤተሰብ ላይ ስለመጣው ችግር ለመናገር ብቻ ሳይሆን፥ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ስለመሆናቸውም ለማጋለጥ ነበር። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው የራብን መርገም ጭምር እንደሚያመጣባቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ ተናግሮአል (ዘዳ. 28፡23-24)።
    የአቤሜሌክ ቤተሰብ ራቡን በመሸሽ ወደ ሞዓብ ሄደ። በዚያም ለብዙ ዓመታት ስለኖሩ፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ሞዓባውያን የሆኑ ሴቶችን አገቡ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ አቤሜሌክና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ።
    የታሪኩ ዋና ትኩረት ኑኃሚን እንዴት ባዶና ድሀ እንደሆነች ለማሳየት ነው። ባልዋን እና ልጆችዋን አጣች። በእርጅናዋ ወራት እንክብካቤ የሚያደርግላት አንዳችም ወራሽ፥ ወይም ራሷን የምትደግፍበት መሬት አልነበራትም፤ ስለሆነም እጅግ ተማርራ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ወሰነች። አንደኛዋ ምራቷ በሞዓብ ስትቀር፥ ሌላኛዋ ግን ማለትም ሩት አማትዋን ለመከተል አማልክትዋን፥ ቤተሰብዋንና አገሯን ሁሉ ተወች። ሩት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገለጥ የታማኝ ፍቅር ምሳሌ ናት። ወደ እስራኤል ምድር እንደ እንግዳ ከመሄድ ይልቅ በአገሯ መቅረት፥ ከገዛ ሕዝቧ ጋር መኖር በቀለላትም ነበር።
    2. ለኑኃሚንና ለሩት እንክብካቤ ለማድረግ እግዚአብሔር የሠራው ሥራ (ሩት 2-3)
    በዚህ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር የተጠቀሰበት ቦታ ብዙ ባይሆንም፥ በታሪኩ ሁሉ የእግዚአብሔርን እጅ እንድናይ ለማድረግ ጽሐፊው እንደሞከረ ግልጥ ነው። ሩት እንዴት ወደ አማቷ ዘመድ የእርሻ ቦታ እንደሄደች ተመልከት። የኑኃሚን ዘመድ የሆነው ቦዔዝ ለሩት ልዩ የሆነ ትኩረትና ጥንቃቄ እንዴት እንዳደረገ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ቦዔዝ የቤተሰብ ግዴታውን ለመፈጸም ብሎ አሕዛብ የሆነች ሴት እንዲያገባ እንዴት እንደገፋፋው ተመልከት።
    ታሪኩ የሚያተኩረው በሁለት ዋና ዋና ገጸ-ባሕርያት ታማኝነት በተሞላ ፍቅር ላይ ነው። በመጀመሪያ፥ ሩት ለኑኃሚን የነበራት በታማኝት የተሞላ ፍቅር ነው። በሁለተኛው ደግሞ፥ ቦዔዝ ለሩትና ለኑኃሚን ያሳየው በታማኝነት የተሞላ ፍቅር ነው።
    ነገር ግን ከሰው የታማኝነት ፍቅር ምሳሌነት ሁሉ በላይ እግዚአብሔር ለሁለት ድሀና ምስኪን ሴቶች የነበረውን ፍቅርና እንክብካቤ እናያለን።
    3. እግዚአብሔር የሩትንና የቦዔዝን ታማኝነት በማክበርና ለእርሱ ዋጋ በመስጠት ለኑኃሚን በረከቱን መለሰላት (ሩት 4)
    ከሩት ታሪክ በስተጀርባ የአይሁድ ባሕል የሆነ «የመዋጀት» ተግባር እናያለን። መመሪያው በዘዳግ. 25፡5-10 ይገኛል። በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር ሕግ የሚለው አንድ ሰው ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ ወንድሙ የሞተውን ሰው ሚስት በመውሰድ ከሴቲቱ ልጅ መውለድ እንደነበረበት ነው። በዚህ መንገድ የሚገኘው ልጅ የሟች ወንድሙ ወራሽ ይሆን ነበር፤ ደግሞም በዘሌ. 25፡25-31፥ 41-55 ሕጉ በተጨማሪ ድሀ የሆነ ሰው በድህነት ምክንያት መሬቱን ቢሸጠው፥ የዚህ ድሀ ሰው ዘመድ ገንዘቡን በመክፈል መሬቱን ሊያስመልስና በባዕድ እጅ እንዳይገባ ሊከላከል ይገባ ነበር። የእነዚህ ሁለት ሕግጋት ዓላማ የአንድን ሰው የቤተሰብና የመሬት ወራሽነት ለመጠበቅ ነበር።
    በመጽሐፈ ሩት፥ ይህ ሕግ በቅርብ ዘመድ ብቻ ሳይወሰን፥ በሩቅ ዘመድም ላይ የሚሠራ ሆነ። የመዋጀት ግዴታ የወደቀው በቅርብ ዘመድ ላይ ነበር። ይህ የቅርብ ዘመድ ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም የማይችል ከሆነ ብቻ ኃላፊነቱ ወደ ሌላ ዘመድ ይተላለፍ ነበር። በዚሁ መሠረት ቦዔዝ ሩትን አገባና የአቤሜሌክና የልጆቹ ወራሽ የሚሆን ልጅ አስገኘ። ልጁ የአቤሜሌክ ምድር ወራሽ ሆነ፥ ቦዔዝ ደግሞ የአቤሜሌክ ምድር የተያዘበትን ዕዳ ሁሉ የመክፈል ግዴታ ነበረበት።
    ይህ ከሩት ምዕራፍ 4 ታሪክ በስተኋላ የሚገኝ ባሕላዊ ልማድ ክፍል ነው። ቦዔዝ የኑኃሚን የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው ይፋ ፍርድ ወደሚሰጥበት ስፍራ አመጣው። በጥንት ዘመን የጎሣ ሽማግሌዎች በከተማይቱ በር ላይ ይገናኙና በጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ይፈርዱ ነበር። ወደዚህ የፍርድ ስፍራ የመጣው የቅርብ ዘመድ ለሩት ያለበትን ግዴታ ለመወጣት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጠ። ይህንን ለማድረግ ያልፈለገው፥ የራሱ ልጆች ቢሞቱ ቀሪው ወራሽ ከሩት የሚወለደው ልጁ ስለሚሆን፥ የራሱንም ንብረት ለመቆጠብ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ዘመድ ከቦዔዝ የሚለይበት ነገር ቢኖር ስለራሱ ብቻ የሚያስብ ስስታም ስለ ነበር ነው።
    ቦዔዝ ሩትን የማግባት ግዴታውን ተወጣ። በዚህም ኢዮቤድ የተባለ ልጅ አገኙ። በኃዘኗ ምክንያት በብቸኝነት ተቆራምዳ የነበረችው ኑኃሚን፥ የተባረከች ኑኃሚን ሆነች። የልጅ ልጅ ማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ምድሪቱ ለእርሷ ተመለሰችላት፤ በእርጅናዋ ወራት የሚጦራትንም አገኘች።
    በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጥበብ፥ የሩትና የቦዔዝ ልጅ የእስራኤል ታላቅ ንጉሥ የሆነው የዳዊት አያት ሆነ።
    የውይይት ጥያቄ፥ ስለ እግዚአብሔርና ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ከዚህ ታሪክ የተማርካቸው ዋና ዋና ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

    የመጽሐፈ ሩት ዋና ዋና ትምህርቶች
    በመጽሐፈ ሩት ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ሁለት ቁልፍ ቃላት ይገኛሉ። እነርሱም የመጽሐፉን ዋና ዋና ትምህርቶች የያዙ ናቸው።
    1. መዋጀት፡- በዚህ ታሪክ መዋጀት የሚለውን ትርጉም የሚሰጠውን የዕብራይስጥ ቃል በተለያየ መልኩ 23 ጊዜ እናገኘዋለን። በመጽሐፈ ሩት «መዋጀት» የሚለው ቃል በተለይ ያገለገለው የአይሁድን የመቤዥት ባሕል ለመግለጥ ነው። ተቤዢው ለሟች ዘመዱ ወራሽ የሆነ ልጅ ለማሳደግ፥ ወይም ለችግረኛ ዘመዱ በችግር ምክንያት የሸጠውን መሬቱን ከፍሉ ለማስመለስ፥ ወይም በባርነት ሊወድቅ ላለ ዘመዱ ዋጋ ከፍሉ ከባርነቱ ለማስቀረት ወዘተ ፈቃደኛ የሆነ ነው። ቦዔዝ ለሩትና ለኑኃሚን ተቤዢ ሆነ።
    ቦዔዝ የእግዚአብሔርና የሕዝቡ የእስራኤል ግንኙነት ተምሳሌት ነበር። ቦዔዝ ኑኃሚንና ሩትን በድህነት ምክንያት ከነበረባቸው ባርነት ዋጃቸው (ተቤዣቸው)። ፍላጎታቸውን አሟላ። ልክ እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዳደረገ ዓይነት ማለት ነው። እርሱ የእስራኤላውያንን ፍላጎት ሁሉ ያሟላ አምላክ ነው።
    ቦዔዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ተምሳሌት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፥ በመሆኑም የእኛ ዘመድ ሆነ። እንደ ዘውድነቱ በመስቀል ላይ በመሞቱ፥ እያንዳንዳችንን ከኃጢአት ባርነት ዋጀን፤ (የሐዋ. 20፡28)፤ በዚህም የተቤዢነቱን ዓላማ አሟላ። ተቤዢያችን ክርስቶስን እኛን ከባርነት፥ ከመንፈሳዊ ጉስቁልና ለመዋጀት የሚከፈለውን ዋጋ ከፈለ። በዚህም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት አደረገን።
    የትኩረት ነጥብ፥ የተቤዠህን ክርስቶስን ለማመስገን ጊዜ ይኑርህ።
    2. በፍቅር የተሞላ ቸርነት፡- አይሁድ «ሂሴድ» የሚል ልዩ ቃል ነበራቸው። ይህ ቃል በብዙ ልዩ ልዩ መንገዶች ሊተረጎም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ለቃል ኪዳኑ ታማኝነት፥ አንዳንድ ጊዜ ርኅራኄ፥ ሌላ ጊዜ ፍቅር መሆን ይችላል።
    የሩት ታሪክ እንዲህ ዓይነቱን በፍቅር የተሞላ ርኅራኄ ይገልጣል። ሩት እውነተኛ ተስፋ ባይኖርም እንኳ በፍቅር የተሞላ ርኅራኄና ቸርነት ለኑኃሚን ገለጠች። የኑኃሚንን ጉስቁልና በመካፈል በታማኝነት ለኑኃሚን የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ከእርሷ ላለመለየት መቁረጧን ገለጠች (2፡11-12)። ቦዔዝ ሩትን በእርሻ ስፍራው በመርዳት፥ ወራሾቹን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ፥ እርሷን ለማግባት በመፍቀድ እንዲህ ዓይነቱን በፍቅር የተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ ለሩትና ለኑኃሚን ገለጠ።
    ከሁሉም በላይ ግን በታሪኩ ውስጥ የእግዚአብሔርን በፍቅር የተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ እንመለከታለን (2፡20)። ከዚህ ታሪክ የምንመለከተው፥ እግዚአብሔር በእርሱ የሚታመኑትን ፍቅርን በተሞላ ቸርነትና ርኅራኄ እንደሚመለከታቸው ነው። በመጽሐፈ ሩት ውስጥ እግዚአብሔር በተለያዩ ስውር መንገዶች ለሕዝቡ ጥቅም ሲሠራ እንመለከታለን። ሩትን ወደ ቦዔዝ እርሻ መራት፤ ቦዔዝም እንዲራራላት አደረገ፤ ቦዔዝና ሩት እንዲጋቡም አደረገ። ቦዔዝ፥ ሩትንና ኑኃሚንን የታላቁ የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት አያት በሆነ ልጅ ባረካቸው።
    ምንም እንኳ የእግዚአብሔርን እጅ ሁልጊዜ በሥራ ላይ ባናየውም፥ እግዚአብሔር በማይታይ መንገድ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ሕዝቦችን ሁልጊዜ እንደሚረዳ እንመለከታለን። የሩት ታሪክ ሮሜ 8፡28ን ይገልጣል። «እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።»
    የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ መከራን በምትቀበልበት ጊዜ፥ ይህ እውነት እንዴት ያጽናናሃል? ለ) ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ባለህ ግንኙነት ታማኝ ስለመሆን አስፈላጊነት ይህ ታሪክ ምን ያስተምርሃል?
    (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • ጊዜ
  • ትጋት
  • ሐሰት፣ ሐሰተኛ፣ ሐሰተኝነት እና መገለጫቸው

Article Categories

  • Literature/ስነ-ጽሑፍ
  • Gospel Thoughts / የወንጌል አስተምህሮ
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
  • Testimony/ምስክርነት
  • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን

Login Form

  • Forgot your password?
  • Forgot your username?
Copyright © 2025 yegizewkal. All Rights Reserved.