yegizewkal
ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። ትንቢተ ኤርምያስ 15፥16

  • Home/መነሻ ገጽ
  • Gospel Thoughts/የወንጌል አስተምህሮ
    • ነገረ ድነት/Salvation
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
    • Literature/ስነ-ጽሑፍ
    • ከመጽሐፍት ዓለም
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን
    • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Testimony/ምስክርነት
  • ማስታወቂያ/Advertisement
  1. You are here:  
  2. Home
  3. The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
  4. Literature/ስነ-ጽሑፍ

Literature/ስነ-ጽሑፍ

ጊዜ

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: Literature/ስነ-ጽሑፍ

                          ጊዜ

መግቢያ

 ጊዜ እንደ ምንመገበው ምግብ፣ እንደምንጠጣው ውሃ እና እንደ  ምንተነፍሰው አየር ሁሉ ዋጋ  ያለውና በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ትኩረት የሚያሻው ከእግዚአብሔር የተሠጠን ዕድል ነው። የሰው ልጅ በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴ እና ኑሮ  በሕይወት እስካለ ድረስ እድሜው ተወስኖ እና ተመጥኖ  የተሰጠው የጊዜ ልኬት ገደብ አለ። 

ላወቀ፣ ለተረዳና ለገባው ጊዜ ለሰው ልጅ ውዱ ሀብት ነው። ለሰው ልጅ ጊዜ ሲሰጥም ተመጥኖና ተወስኖ እንጂ እንደ አሸዋ የሚዘገን፣ ተዘግኖም የሚሰጥም የተሰጠም፣ የሚቸር የተቸረም አይደለም፣ ገደብ አለውና። አበው ሲናገሩ እንኳን "እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ ብዙ እናያለን" የማንሠራውና የማናየው የለም የሚሉት በዚህ ምክንያት ነው። የጊዜን ብርታትና ጥንካሬንም ሲገልጹ "ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል"፤ ይህ ማለት ምን ያህል የጊዜን ሃያልነት እንደሚያውቁ መረዳት ሲቻል፣ በተጨማሪም ጉብዝናውን ለመግለፅ "ጊዜ ጎበዙ" በማለትም የውዳሴ ያህል በማሞካሸት ይገልጹታል። በእድሜ ዘመን የዕድሜ ልኬት ለሰው ልጅ የመኖሪያ ጣሪያው ለእያንዳንዱ ሰው የተሰጠው የጊዜ ገደብ ማለቂያ አለው። ልኬቱና መጠኑም የሚታወቀው ሲሰጥ ሳይሆን ሲያበቃና ሲያከትም ሲያልቅ ብቻ ነው። የጊዜ ዋጋንም የምናውቀው የዚያን ጊዜ ብቻ ነው። 

ጊዜ መክረሚያ፣ መሠንበቻ ማለት ሲሆን፣ መቆየት በራሱ ደግሞ የውኑ አለም አስፈላጊ ክፍል ነው። በውኑ አለም በስልጣኔ በካበተና በኋላ ቀር አስተሳሰብ የታጨቀች ብትሆንም በሁለቱ አለማት መካከል ያለው የጊዜ መረዳት፣ በጊዜ ጠቀሜታ እና አስፈላጊነት ላይ ያለው አመለካከት እጅጉን የተለያየ ከመሆኑም ባሻገር በሕይወታቸው ላይ የሚታየው ለውጥና ስልጣኔ ለአብነት ያህል አሰረጂና እማኝ ማስረጃ ነው። 

የጊዜ አጠቃቀም በሰለጠነው ማህበረሰብ ላይ እጅግ ለውጥ የታየበት፣ ለውጥን በየፈርጁ ያመጣ ሲሆን በተቃራኒው፣ በጊዜ አግባብ እና አጠቃቀም ላይ ዝቅተኛ አመለካከት ባላቸው ዘንድ ምንም አይነት የገነነ ለውጥ የሌለ ሲሆን እድገቱም የዛን ያህል እጅግ ዘገምተኛ ነው። 

በጊዜ ላይ ያለን አነስተኛ አመለካከት በአገር እድገት፣ በመንፈሳዊ እድገት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው። በጊዜ ውስጥ ሂደትንና የነገሮች ዑደትን የምናይበት ክስተትንም የምንረዳበት እና የምናይበት  ነው። 

በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ እና ከሚጓዙ ነገሮች በምንም አይነት መንገድ ልናቆመው የማንችለው ነገር ቢኖር ጊዜ ነው። ጊዜን ልንቀጥረው፣ በዚህን ሰዓት እዚህ ቦታ እንገናኝ የማንለው ነገር ነው። 

በአለም ላይ ካሉ አገራት እኛ ኢትዮጵያዊያን በጊዜ ላይ ያለን መረዳትና ግንዛቤ እጅግ በጣም የወረደና ያነሰ ሲሆን በተለይ ቀጠሮን ከምናከብርባቸው ነገሮች መካከል ለእኛ ረብ የሌለው ነገር ላይ እንጂ ቀድመን የቀጠሮ ቦታችን ላይ መገኘት በዚህ የማንታማ ሲሆን ዘላቂና ለሕይወታችን እጅግ ጠቃሚ በሆነ ነገር ላይ ግን እጅጉን ሰነፎችና ዳተኞች ነን። 

ጊዜ በእግዚአብሔር ምህረት እና ቸርነት የተሰጠን ውድ ስጦታ ነው። ጊዜ የእግዚአብሔር የምህረቱና የቸርነቱ በጎ ስጦታና መገለጫ ነው።  “ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።” — ሰቆ. 3፥22 
“ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።”— ሰቆ. 3፥23


ጊዜን የሚሰጥ እና የሚጨምር እግዚአብሔር ብቻ ነው። የጊዜ አጠቃቀምን ማወቅ ግን የሰው ልጅ ግዴታ እና ኃላፊነት ነው። እንደ አዲስ ኪዳን አማኝና በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ተቀብሎ እና በስሙ አምኖ እንደ ዳነ ሰው ለጊዜ ያለን ግምትና ቦታ ከፍ ሊል ይገባል፣ ተገቢም ነው። ጊዜ እንደ ዋዛ የምናየው፣ የምንቀልድበት እና የምንዘናጋበት አይደለም።ጊዜ የምናቃጥለው ማገዶ አይደለም።ጊዜ ይለፍ ብለን የምናሳልፈው ወራጅ ወንዝም አይደለም አሊያም እንደ ኩሬ ውሃ አቁረነው የምናከማቸው አይደለም፣ ሁሌም ፍሰቱንና ጉዞውን እንደቀጠለ የሚኖርና የማንገድበው ነው። 

አግባብ ያለው የጊዜ አጠቃቀምን ለመለማመድ የራስ ቁርጠኛ ውሳኔና በውሳኔ መፅናትን እና መዝለቅን ይጠይቃል።  

ጊዜ እንደ ገንዘብ ነው። ካባከንነው በሚያስፈልገን ጊዜ መልሰን ላናገኘውና ልናጣው እንችላለን። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ደግሞ የሚያስደስቱንን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ ይኖረናል። ጊዜን በአግባቡ ስንጠቀም አስፈላጊ አቅም መሆኑን እንረዳለን። 

ጊዜን የምትጠቀምበት መንገድ ሥራችንን ይዘን እንድንቀጥል አሊያም ከሥራ እንድንባረር ሊያደርገን የሚችል አቅም አለው። በጊዜ ላይ ያለን የወረደና የወደቀ አመለካከት ውጤቱ እጅግ የከፋ አሉታዊ ተጽዕኖን በሕይወታችን ላይ ያመጣል። አበው እንኳን በብሒላቸው ስለጊዜ ሲናገሩ "ላለፈ ክረምት እቤት አይሰራም" ይላሉ። ይህን ሲሉ በነበረህ ጊዜ ውስጥ እድልህን መጠቀም ነበረብህ የሚል ምክር አዘል ወቀሳን ያቀርቡበታል። 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማርታ፣ የማርያም እና አልአዛር ትልቅ ወዳጃቸው ነው። በቤታቸው መገኘቱ ለሁለቱም መረዳታቸው የተለየ ነው። አቀባበላቸውም ለየቅል ነው። የማርታ መባከን፣ የማርያም ከእግሩ ስር መቀመጥ የአቀባበል አይነቱ መለየትን ያመላክታል። ዕድልን መምረጣቸውም የዛን ያህል መለያየቱ ለእንግዳቸው ያላቸውን መረዳትና የእርሱን አስፈላጊነት በሁለቱ መካከል ባለው መስተጋብር መረዳት ይቻላል። ዋናው ጌታችን ሲመጣ ጊዜ ይሰጠዋል፣ ስፍራ ይሰጠዋል፣ እጅግ በቅርበት ተጠግቶ ማውራትን፣ መነጋገርን ይጠይቃል። መጨነቁና መታወኩ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። ጌታችን እኛንና ቤታችንን ይፈልጋል እኛ ግን በብዙ እንባክናለን በዚህ መካከል የሚያመልጠንና የሚነጉድብ፣ የማንይዘውና የማንገድበው ጊዜ አለ። የሚያስፈልገው ጥቂት ሆኖ ሳለ በብዙ መታወክና ጊዜን ማባከን። እንደ ማርያም ከእግሩ ስር መቀመጥ። ማርያም ከእግሩ ስር መቀመጧ ለእርሱ ጊዜን መስጠቷ መሆኑ ልብ ይሏል። ከእግሩ በመቀመጥ ጊዜን መስጠት እጅግ ተገቢና ወሳኝ ነው። “ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥”
  — ሉቃስ 10፥41። “የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።” — ሉቃስ 10፥42።ዋናው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ሳለ ከእግሩ ስር ተቀምጦ እርሱ የሚሰጠንን መብላት፣ መመገብ፣ ጽድቁን መጠቀም ተገቢ ነው፣ የእግዚአብሔር መንግስት ጽድቅ ጌታችን እርሱ እራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” — ማቴዎስ 6፥33። ጊዜ አንድም በብርሃን በቀን፣ አንድም በጨለማ በሌሊት ይገለፃል። 

ስለ ጊዜ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጠንቅቀው የተረዱትና ሊባክንም እንደማይገባ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ጠላታችን ዲያብሎስ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሥራቸውን በጊዜ ውስጥ እንደሚከውኑ በውል ያውቃሉ፣ የሚጠፋ ጊዜ ሊኖር እንደማይገባም ጭምር ያውቃሉ።..0

                                                    መዘርዝር ማብራሪያ

 ጊዜን በሚገባ የተጠቀሙና ለበጎ ዓላማ ያዋሉ ጥቂት የእግዚአብሔር ሰዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለትምህርታችን እና ለእውቀታችን መመልከቱ ተገቢ ሲሆን እነዚህም በህይወታቸው ዘመን ሁሉ ጊዜን እንዴት እንደተጠቀሙና ያገኙትን ትሩፋቶች መመልከት ያሻል።  

ሙሴ፦ የአርባ አመት የቤተመንግሥትን ኑሮ በመናቅ፣ በእንቢተኝነት ንቆ በመውጣት፣ የንጉስ የልጅ ልጅ ላለመባል፣ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር ቀሪውን ዘመን መከራ መቀበልን የመረጠ ጀግና የእምነት አባት ነው። ምቾቱን የተወ፣ ልጅነትን የተወ፣ ወራሽ መባልን የተወ፣ ከምቾት ሰፈርና ቤት የምድረ በዳን፣ የበረሃን መንገድ የመረጠ፣ ሕዝብን ለመምራትና አብሮ መከራ ለመቀበል  ከእግዚአብሔር የተቀበለ፣ ቆራጥና የውሳኔ ሰው። የነበረበትና ያደገበት የኑሮ ዘይቤ ያላማለለው፣ ያላታለለው ትልቅ ነብይ ነው። ጊዜውን፣ ዕድሜውን ሰጠ።ምርጫውን ተከትሎ የተጓዘ አገልጋይ፣ መሪ ነው። “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤” — ዕብራውያን 11፥24። የንጉሡን ቁጣ የማይፈራ፣ ደፋር ሰው፣ የኖረበትን የምቾትና የድሎት ዘመን የተወ ሰው ነው። “የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።” — ዕብራውያን 11፥27። በተለይ ሙሴ በእግዚአብሔር ጥሪና ቀጠሮ በሲና ተራራ ለአርባ ቀናት የቆየ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜን የወሰደ፣ ፊት ለፊት የተነጋገረ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር ጊዜን የወሰደ፣ በመነጋገርም ከራሱ አልፎ ለህዝብ መልእክት ይዞ የመጣ ታላቅ ነብይ ነው። 

ኤልሳዕ፦ ከኤልያስ በኋላ የተነሳ ነብይ፣ በእርሻው ላይ ሳለ ኤልያስ መጎናጸፊያውን የጣለበት፣ በሬዎቹን የተወ፣ ከኤልያስ በኋላ የሮጠ፣ ወላጆቹን የተሰናበተ፣ በሬዎቹን አርዶ ሥጋቸውንም በበሬ ዕቃ ቀቅሎ ለሕዝብ የሰጠ እና ያበላ፣ ኤሊያስን ተከትሎ ያገለገለ ቆራጥ ሰው፣ ሁሉን ነገር ትቶ ጊዜውን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠና ከአባቱ ተረክቦ አገልግሎት ያስቀጠለ የውሳኔ ሰው ነው። ያለውን ትቶ የተከተለ ቆራጥ ሰው፣ የሚበልጠውን የተረዳ ትልቅ አገልጋይ ነው።
        1- መጎናጸፊያ ተጣለበት፦ ጅማሮ
“ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው፦ ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት።” — 1ኛ ነገሥት 19፥19።
        2- የመሰናበቻ ጊዜ፦ ቤተሰቡን ተለይቶ ሊሄድ እንደሆነ ማሳወቂያ
“በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ፦ አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም፦ ሂድና ተመለስ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው።” — 1ኛ ነገሥት 19፥20።
        3- የውሳኔ ጊዜ፦ ላይመለስ የቆረጠበትን ማሳያ
“ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር።” — 1ኛ ነገሥት 19፥21።

ሐዋርያት፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ የአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ፣ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ አስቀድሞ ያደረገው ነገር ቢኖር የራሱ የሆኑትን ለመምረጥ፣ ሥራ ሊያሠራቸውና ተልዕኮን ሊያስቀጥል ካሉበት ስፍራ በመሄድ እንዲከተሉት በመጥራት፣ እነርሱም ወስነው ተከተሉት።“በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤”— ሉቃስ 6፥13። “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።”
  — ማቴዎስ 19፥27። ሐዋርያት ሁሉን ትተው፣ የነበራቸውን መተዳደሪያና መጦርያ ትተው፣ የለመዱትን ነገር ትተው ሳያቅማሙ ሲጠራቸው የያዙትን የጨበጡትን ለማንም አደራ ሳይሰጡ ባለበት አስቀምጠውና ትተው አምነውት ተከተሉት። የጴጥሮስ ንግግር ካስተውከን ምን እናገኝ፣ በምላሹና በምትኩ ምንስ እናተርፍ፣ ይሰጠን ይሆን የሚል ጥያቄን አቀረበ። ኪሳራ እንዳይገጥመው አይነት ፍርሃት ይመስላል። ጌታ ኢየሱስ ግን እርግጠኛ እንዲሆንበት ስለወደፊቱ ዋስትና ያለበት ማረጋገጫን ሰጠው። “ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።”— ማቴዎስ 19፥28። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጨማሪም ለጴጥሮስ ሲመልስለት፣ አዎ ሁሉን ትተህ ተከትለሃል፣ ጊዜህን ሰጥተሀኛል በምላሹ መቶ እጥፍ የምታገኝበትን የዘላለም ሕይወት እንደምትወርስና እንደምትቀበል በማለት ምላሽ ሰጥቶታል። “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።”— ማቴዎስ 19፥29። ሐዋሪያት በሕይወት በነበሩበት ዘመን፣ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የተከተሉትን ጌታ ኢየሱስ ባልተዛነፈ ሁኔታ ጊዜያቸውን ጌታን በማገልገል ፈፅመዋል። 

ጳውሎስ፦ እጅግ ቀናተኛ፣ አክራሪና ወግ አጥባቂ የነበረ አይሁዳዊ፣ ለእግዚአብሔር የቀና መስሎት ክርስቲያኖችን እጅግ በከፋ ሁኔታ ያሳድድ፣ በወህኒ ይጥል የነበረ፣ ይሰድብና ይዘልፍ የነበረ፣ ጊዜውንም እነዚህን ነገሮች በመከወንና በማስፈጸም የደከመና የተጋ እና የተጠመደ ሰው ነበረ። “እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ።”— ሐዋርያት 22፥3።
“ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ።”— ሐዋርያት 22፥4።
ይህንን አሳዳጅ ሰው ነው ጌታችን ኢየሱስ ለሌላ ህቡዕ  ተልዕኮ  ሲሄድ የነበረን ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ አግኝቶት የራሱ ያደረገው።  

ሐዋርያት 22
⁶ ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ ⁷ በምድርም ላይ ወድቄ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።⁸ እኔም መልሼ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ።— ሐዋርያት 22፥4።
ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የተፈራና በሊቃውንትም ዘንድ የተከበረ ነገር ግን ለእግዚአብሔር የቀና መስሎት የጌታን ተከታዮችና አማኞች በማሳደድ የተጠመደ እና ጊዜውንም በዚህ ሥራ በማሳለፍ የሚተጋ ሰው ነበረ። ጳውሎስ ጌታ እስከሚያገኘው የነበረው የህይወት ዘመኑ፣ ረብ በመሰለው ሥራ መባከኑ እጅግ ክብር መስሎት የኖረ ግን ጌታ ሲያገኘው የቀደመው ዘመኑ ምዕራፍ በማብቃቱ ሌላኛውን ምዕራፍ ጌታ ሲያስቀይረውና ለራሱ አላማ ጊዜውን ሲጠቀምበት ፣ ጳውሎስም የቀደመ ጊዜውን ቁጭት ውስጥ በመግባት ሲገልፅ፣ ረብ የነበረውን ለክርስቶስ ተወ፣ ራሱንም አስገዛ። ጳውሎስ ብዙ ጥቅሞቹን እንደ ጉድፍ እና እንደ ጉዳት እቆጥረዋለሁ በማለት ዘመኑን፣ ጊዜውን፣ አቅሙን ለጌታ በመስጠት ጊዜውን በአግባቡ የተጠቀመ የአዲስ ኪዳን ቆራጥና የጨከነ አገልጋይ መሆኑን ዛሬ ላለን አገልጋዮችም ጭምር አብነትና ምሳሌ የሚሆንን ህይወት እና አገልግሎት ኖሮ አገልግሎ አሳይቶናል። ጳውሎስ በሥጋ እንኳን ምን ያህል የሚመካበት እንዳለና ይህም የሚታመንበት ለክርስቶስ ግን የተወ፣ ይህም ቢነሳ እኔ እበልጣለሁ በማለት መመካቱን የሚገልፅ፣ በእምነትም ቢሆን የተገረዝሁ፣ ምርጥ እስራኤላዊ ያውም ብንያማዊ፣ ከዕብራዊም ዕብራዊ የሆንሁ፣ አዋቂም እንደሆነ፣ ነቀፋ የሌለበት እንደሆነ ጫፍ የወጣ ማንነቱን የሚገልፅ፣ ዘመኑንም በዚህ የኖረ እንደነበረ ለተቀናቃኞቹ ጭምር አፍ ማስያዣ እና የሚያስከነዳበትን ንግግሩን ማንነቱን ለመግለፅ ይጠቀም የነበረ ሰው ነበረ።
⁴ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። ⁵ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ⁶ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። — ፊልጵስዩስ 3፥7
ይህ ጳውሎስ ነው እንግዲህ ይህን ሁሉ እንዲህ በማለት የገለፀው፣ ቢቀርብኝም አይጎዳኝም በማለት፦“ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።” — ፊልጵስዩስ 3፥7። “አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤” — ፊልጵስዩስ 3፥8-9።

ዳዊት፦ የተነሳበትን ቦታና ጊዜ እና የደረሰበትን ቦታና ጊዜ የሚያውቅ ትልቅ ንጉስ ነው። መነሻውን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ እድሜውን፣ ዘመኑን የእግዚአብሔርን ሐሳብ በማገልገል ያጠናቀቀ ሰው ነው። እግዚአብሔር የሠጠውን ዘመን ለእግዚአብሔር የሠጠ ብርቱ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔር ስም ትልቅ ቦታ ያለው፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትልቅ ስፍራ ያለው፣ ለእግዚአብሔር ታቦት ትልቅ የከበረ ቦታ ያለው፣ ለቃል ኪዳን ሕዝብና ታቦት እጅግ ከበሬታ ያለው ትልቅ አገልጋይ ነው። ለዚህ ነው ዘመኑን መልሶ ለእግዚአብሔር የሰጠው። “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤”— ሐዋርያት 13፥36።

                  የጊዜ እንቅፋቶች

1- የጊዜን አግባብ አለማወቅ፦ እኛ ኢትዮጵያዊያን በአለም ላይ ካሉ ማህበረሰቦች በጊዜ ላይ ያለን አመለካከትና መረዳት እጅግ የወረደና ጊዜ ምን እንደሆነ፣ ጊዜ ለእኛ ምን እንደሚጠቅም፣ የጊዜን ፋይዳ በውል አናውቅም። ጊዜ ብዙ ትርጉም ያለው ወሳኝ ነገር መሆኑን ጨርሶ አናውቅም። የጊዜን ተገቢነት ያወቁ እንኳን በዙሪያቸው ባሉ የጊዜን አግባብነት ባላወቁ ተውጠውና ተቸግረው እናያለንም እናስተውላለንም። 

ቀለል ያለን ስራ ወዲያው ፈጥነን መስራት ሲገባን ለበኋላ አሊያም ለነገ በይደር በማስቀመጥ ተጠቃሚውን ለአላስፈላጊ ችግር ስንዳርግ እንታያለን።  ኋላ ለቁጭትም የሚዳርገንን ነገር ስንሰራ እንታያለን።


2- የጊዜን ተገቢነት አለማወቅ፦ የጊዜ ዑደት በሕይወት ውስጥ እጅግ ወሳኝ መሆኑን በውል ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢነቱን መረዳት ነው። በምንም አይነት ሥራና ሁኔታ ውስጥ እንገኝ ጊዜን ባከንና መጠቀም ተገቢነቱ እዚህ ጋር ነው።በዋዛ ይሁን በፈዛዛ ጊዜ ተገቢነቱ የሚታወቀው በዚህ ነው። ከጊዜ ስሌት ውጭ የሚሆን ምንም ነገር የለም። ለመልካም ሥራ በምንሰናዳበት የትኛውም ነገር ጊዜን በስርዓት መጠቀሙ የጊዜን ተገቢነት ማወቅ ነው። ጊዜ ገንዘብ ነው፣ ጊዜ ሃብት ነው፣ ጊዜ ንብረት ነው። 

በሕይወት ዘመናችን የትውልድ መተካካት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ተወለደ ሞተ የሚባለው ትርጉም የሚኖረው በመወለድና በሞተ መሃል የተሠራው ሥራ እሱ ወይ እንድሞገስ አሊያም እንድንኮሰስ ምክንያት ይሆናል። ስለዚህ በጊዜአችን ሠርተን የምናልፈውን በውል ጠንቅቆ ማወቁ ተገቢም አግባብም ነው። “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤” — ሐዋርያት 13፥36።

3- ረብ ባልሆኑ ነገሮች ላይ መቆየት፦ ብዙውን ጊዜ ከምናባክናቸው ጊዜያት ውስጥ ጥቅም በሌለው፣ ረብ በሌለው፣ ሕይወታችን ላይ ምንም አይነት ጥቅምና ትርፍ በማያመጣ ጉዳይ ላይ እስከምንደክምና እስከምንዝል ድረስ የምንፈጀውና የምናባክነው የምናጠፋው ሲቆጨን አይሰማንም። ጊዜ ካለፈ በኋላ ወሳኝ ነገር ሲገጥመን ምነው ያኔ እንዲህና እንዲያ ባደረግን ብለን ባለፈ ጊዜ ላይ ቁጭታችንን በስሜታችን እንገልፃለን። 

በሕይወታችን ጊዜን ካባከንንባቸው ነገሮች መሃል በተለይ አቻ ጓደኛን መረጣ ላይ፣ በሕይወታችን ምንም አይነት አስተዋጽኦ በማያመጡ ሰዎች ጋር ያለን አሉታዊ ተግባቦት የምክራቸው አሉታዊነት ጊዜአችንን ማባከኛ ሆነው ታይተዋል፣ እየታዩም ነው፣ ካልተለየናቸውም ነገም ማባከኑ አይቀሬ ነው። “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።”
  — መዝሙር 1፥1። “ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።” — መዝሙር 1፥2።
በሕይወታችንም ፌዘኞችን የተጎዳኘንና የተጣመርን ሰዓት እጅግ በሕይወታችን ጉዳትን ማምጣቱ አይቀሬ ነው። ሞገስንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሳጣናል።“በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።” — ምሳሌ 3፥34።

4- የማይመች ባልንጀራ፦ ብዙውን ጊዜ የወዳጅ ምርጫ ላይ አለመጠንቀቅ የሚያመጣው አሉታዊ ችግር ከረፈደ በኋላ ውጤቱ ላይ እና በደረሰብን ችግር የዚያን ጊዜ እንነቃለን። የጓደኛ ምርጫ ላይ መጠንቀቅ በጣም ተገቢ ነው። በተለይ ውስጡን የማናውቀው እና ግልፅ ያልሆነ ጓደኛ ባልንጀርነቱ በክፉ ሊገለፅ ይችላል፣ አጠገቡ ላለውም ጠንቅ ይሆናል። የማይመቹ ሰዎች ለራሳቸውም የማያስቡ፣ ለሌሎችም ጥቅም የማይሰጡና የማይቆሙ፣ አጠገባቸው ላለ እጅግ ጠንቅ ናቸው። መልካሙን ነገሮቻችንን ያጠፋሉ፣ ያጠለሻሉ፣ ከምንም በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻሉ። “የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል።”— መክብብ 10፥1። “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” — 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥33።
“ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋር አትሂድ፥” — ምሳሌ 22፥24። “መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ።” — ምሳሌ 22፥25።

5- በዕቅድ አለመመራት፦ በዓለም ላይ ካሉ ፍጥረታት ነገሮችን በእቅድ ለመምራት አቅምና ችሎታ ከተሰጠው ፍጥረት አንዱ የሰው ልጅ ነው። ሆኖም ግን በአለም ላይ ካሉ ሰዎች በእቅድና በጊዜ ነገሮችን ከማያከናውኑ ሰዎች መሃል እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። ሥራን ከማቀድ ውጭ፣ በወረቀት ላይ ከማስፈር ውጪ ለእቅዱ መሳካት ምንም አይነት ጥረት ስናደርግ አንገኝም። ምንም እንኳን ማቀድ ተገቢ ቢሆንም እቅዱን በተግባር ለማሳየት አለመጣሩ የእቅድ ማውጣት ልፋት ከመሆኑ ባሻገር ሥራ ላይ ካልዋለ ከንቱነቱ ይብሳል። እግዚአብሔርም ነገሮችን ሲሰራ በጊዜ ሽንሸና እና ድልድል ሁሉን ውብ እና ቆንጆ አድርጎ ሰርቷል። ይህም ምሳሌያችን ሊሆን ይገባል። የጊዜን በዕቅድና በአግባብ ማድረግ ውጤቱ ላይ አስደሳች የሆነና አመርቂ ውጤት እናገኝበታለን። “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው።”— መክብብ 3፥11
6- የዛሬን ሥራ አውሎ ማሳደር፦ የዛሬን ሥራ ለነገን የሥራ ጊዜ መውሰድ፣ በነገው ሥራ ላይ ተደራቢና ተጨማሪ ሥራን እና ጫናን በመፍጠርና በማከል ውጤታማ ያልሆነን ሥራ መከወን ያመጣል። ብዙውን ጊዜ ይህ ባህሪ የሚመጣው በስንፍናና በተለይም በቸልተኝነት የሚመጣ እና የሥራ ልምድ የሌለው የጊዜንና የሥራ ጥቅምን ባለማወቅ የሚመጣ ነው። ይህንንም ባህሪ የእግዚአብሔር ቃል በእጅጉ በመቃወም እንድንለየው ያስተምረናል። “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።”— ማቴዎስ 6፥34።
“አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።”— ያዕቆብ 4፥13።

                           በመጨረሻም

ከላይ ያየናቸው የእግዚአብሔር ሰዎችና አገልጋዮች ፍፁም ሁሉን ትተው የተከተሉ፣ ለሌላ አላማ ጊዜያቸውን ሰጥተው የነበሩ፣ ለእግዚአብሔር ግን ጊዜያቸውን በመስጠት እግዚአብሔር ሊሰራባቸው የወደደውን በዘመናቸው ሠርተውና የእግዚአብሔር  ልጆች መሆናቸውን፣ የእግዚአብሔርን ስም አስከብረው፣ አስጠርተው ያለፉ የእምነት ሰዎችና የእምነት አርበኞች ሰዎች ናቸው። ሁሉን ለሚበልጠውና ለበለጠባቸው እግዚአብሔር ትተው የተከተሉ ጀግኖች ናቸው። የጊዜን ውድነት፣ የማይለወጥና የማይቀየር መሆኑን የተረዱና ያወቁ፣ ዘመናቸውንም የሰጡ የዘመናቸው ጀግኖች ናቸው። ሁሉን ትተው የተከተሉ። ስለዚህ በብዙ የምንባክንባቸው ነገሮችን እጅግ ቀንሰን፣ የሚያስፈልገው ጥቂት መሆኑን ተረድተን ከጌታችን ከኢየሱስ እግር መቀመጡ እጅግ ማትረፊያ ነው። ጌታችን ኢየሱስም የሚመጣው በአንድ በሆነ ጊዜ እኛ  በማናውቃት ጊዜ፣ አብ እግዚአብሔር በሚያውቃት ጊዜ ስለሚመጣ እኛም ጊዜያችንን በእግሩ ስር በመቀመጥ የዘላለምን ሕይወት ልንወርስ ይሁን። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።” — ማቴዎስ 24፥36።  “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”— ማቴዎስ 25፥13።

አገልጋይ መምህር በረከት ሱላሞ ሱጌቦ

ሀዋሳ፣ ሲዳማ፣ ኢትዮጵያ 

+251902910126

 

ትጋት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: Literature/ስነ-ጽሑፍ

 

------------------------------------------------------------------------------------------

 

 

ትጋት

“ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው”

(ምሳ. 12፥27)።

መግቢያ

በዚህ ዓለም ላይ ፍሬያማ ሠራተኛ ወይም ውጤታም ሠራተኛ የምንለው ሰው ለውጤታማነትና ለፍሬያማ ሠራተኝነት ከሚያበቃው ዋነኛ ነገር አንዱ ትጋት እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ የሚተጉ ሰዎች ዋነኛ መገለጫ ባህሪያቸው ለጊዜ ያላቸው የጠለቀ አመለካከት እና ዋጋ ትጋታቸውን ጨምሮላቸው ውጤታማ መሆነቸው ነው፡፡

የሚተጉ ሰዎች ሌላኛው ባህሪያቸው እጅግ ትዕግሰተኛ መሆናቸውና ሁልጊዜ ላለሙት ግብና ስኬት ዘወትር በትዕግስት እና እጅግ ብልሃት በታከለበት መንገድ ሥራን መከወናቸው ሲሆን ጥረታቸውን ለቅፅበት ያህል አለማቋረጣቸው ለትጋታቸው ግብዓት ሆኖ ተጠቅመው ግባቸው ላይ ይደርሳሉ፡፡

ትጋት ብዙ ጥረትን፤ የጊዜ አጠቃቀምነ፤ ትዕግስተኝነትን፤ መቋቋምን፤ ግብን ዓላማን ውጤትን ትኩረት አድርጎ የሚነሳ የሥራ መከወኛ ኃይል እና ብርታት ነው፡፡ ትጋት የጊዜን አጠቃቀም፤ ለጊዜ ዋጋን የሚሰጥ፤ ጊዜ እንዲባክን የማይፈልግ፤ ከሁሉ በላይ ለስንፍና ቦታ የሌለው አንዳች ኃይል ነው፡፡

ትዕግስት ከሌለ ትጋት የለም፤ ትጋት ከሌለ ስኬት የለም፤ ስኬት ከሌለ ቀጣይ ምዕራፍ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ትዕግስትና ትጋት በእጅጉ ተሰናስለው የሚኖሩ ነገሮች ናቸው፡፡

 

ትጋት ማለት በግሪክ SPODAZO (ስፓዳዞ) ሲሆን ትርጉሙም ፍጥነትን መጠቀም፣ ጥረት ማድረግ ሲሆን የማይበርድ ጥረት፣ በጽናት የሚደረግ ሥራ፣ በሙሉ ኃይልና ጥንቃቄ የሚደረግ ሥራ ማለት ነው። እንዲሁም የአንድ ሰው ጽናትና ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ጠንካራ፣ ጽናት እና ቀጣይነት ያለው ስራ እንዲያከናውን ያስችለዋል። ትጉ ሰዎች ሥራን የመፈጸም አቅም አላቸው!

በክርስትና እምነት ውስጥ እጅግ የሚፈለግ እና የሚመከር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም  ተደጋግሞ ከተጠቀሱት ቃላቶች አንዱ ትጋት ነው። ይህም የሚያሳየው ትጋት ለሰው ልጅ ምን ያህል ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ ነው። የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊው ሰለሞን ትጋት ለሰው ልጅ የከበረ ሀበት እንደሆነ ይናገራል። “ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው” (ምሳ. 12፥27)።

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ትጋት የተሰጠንን በረከት የምንወርስበት አቅም እና ጉልበት ነው፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላት መሠረት ትጋት መንቃትን፣ ቸል አለማለትን፣ እንዲሁም ሳይታክቱ ያለ እንቅልፍ እና ድካም መጠበቅ ነው። በክርስትና አስተምህሮ ትጉህ መሆን ማለት ለእግዚአብሔር ባለን ቁርጠኝነት ውስጥ ሀላፊነት፤ ዘላቂነት እና ወጥነት ያለው መሆን ነው። በተጨማሪ ትጋት ማለት ሥራ አለመፍታትና ተግባርን እስከ ፍፃሜው ይዞ መዝለቅ ነው።

 

ትጋት ሁልጊዜ 

  1.  ለዓላማ
  2.  ለግብ
  3. ለውጤት ይጨነቃል

ክርስቲያን፣ አገልጋይና ትጋት

በቤተ ክርስትያን አገልጋይ ሊጠነቀቅና ሊያስብበት ከሚገቡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ትጋቱ ነው፡፡ የማየተጋ አገልጋይ በምንም ተዓምር ፍሬያማና ውጤታማ መሆን አይችልም፡፡ ትጋት የጎደለው አገልጋይ ፍሬያማነቱ አይታይም ቀጣይነቱም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡ አገልጋይ ሁልጊዜ በፍሬ መታየት አለበት፡፡ ውጤታማ ካልሆነ ግን ትጋቱ በጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እራሱ በትጋቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ ለፀሎት ይተጋ ነበር፡፡ የማይተጋ አገልጋይ አገልግሎቱም እራሱም ከአገልግሎት ይቆማሉ፡፡ ወደ ደቀመዛሙርቱም መጣ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፡- እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን ማቴዎስ 26፡40::

ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ራሱ እየተጋ ክርስቲያን፤ አገልጋይ የማይተጋበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ ለክርስትናችንም ይሁን ለአገልግሎታችን ትጋት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ትጋት

1.  ትዕግስትን

2.  ጊዜን

3.  አላማን

4.  ግብን አተኩሮ ይንቀሳቀሳል፡፡

 

የትጋት ባህሪያት

1.  የጊዜ ብክንት የለበትም

2.  አይዘናጋም

3.  ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው

4.  ቸልተኝነት አይታይበትም

5.  ትኩረቱ ግቡ ላይ ነው

6.  ፅናት ይታይበታል

7.  ትዕግስት መለያ ባህሪው ነው

 

በትጋት ምን እናድርግ

1.  ስንገዛ በትጋት እንገዛ

ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ ኤፌሶን 6፡7

2.  የምናደርገውን በትጋት እናድርግ

ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉ ቆላስይስ 3፡23

3.  እስከመጨረሻ መቆየት

…ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን እብራውያን 6፡11-12

4.  እናምልክ

…ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርስ ዘንደ አለኝታ አላቸው የሐዋሪያት ሥራ 26፡7

 

ትጋት ከየት ይመጣል

ትጋ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው፡፡

ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለእናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፡፡ 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡16

 

የትጋት ጥቅም

1.  ራስን/ ለፍስን ለመጠበቅ

ነፍስህን በትጋት ጠብቅ ዘዳግም 4፡9-10

2.  ሥራን ለመሥራት

ያም ሥራ በትጋት ይሠራል ዕዝራ 5፡8

 

ትጋት ለማን ነው

1. ለራስ ነው፡- የሚተጋ ሰው በስንፍና አይታማም፡፡ ምክንያቱም ስንፍና በራሱ ኃጢያት ነው፡፡ የማይተጋ ተቃራኒው ታካች ነው፡፡ ታካችን ስንፍና ይገድለዋል፡፡ እነሆ በባሪያዎቹ አይታመንም መለእክቱንም ስንፍና ይከሳቸዋል፡፡ ኢዮብ 4፡18 ስለዚህ ክስ ካለ ጥፋተኝነት ታይቷል ማለት ነው፡፡ ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም፡፡ ምሳሌ 27፡22::የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል፡፡ መክብብ 10፡1::

2.  ለቤተክርስቲያን ነው፡- ቤተክርስቲያን አደገች ስንል ሥራዋን፣ተልዕኮዋን በትጋት እየፈፀመች መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ የምትተጋ ቤተክርስቲያን ዕድገቷ የሚታይ ነው፡፡ የማትተጋ ቤተ ክርስቲያን ባታድግም ባለበት መሄዷ አሊያም ከሌሎች ካደጉ ቤተክርስቲያናት አንፃር ስትታይ ዘገምተኛ ወይም ወደ ኋላ የቀረች ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አደገች ካልን በፀጋ፣ በቃል ሙላት፣ በወንጌል ስርጭት፣ ቤተክርስቲያን ተከላ፣ የሰዎች መዳን ታየ ካልን በስሯ ያሉ አገልጋዮች በትጋት ስራቸውን እየከወኑ ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፡፡2ኛ ጴጥሮስ 1፡5፡፡

 

3.  ለወንጌል ሥራ፡- እርግጥ ነው ጌታ ኢየሱስ በዋናነት የመጣው ለጠፉት፣ ከጌታም በኃጢያ ምክንያት የተለዩትን ለመፈለግና ለማዳን ስለሆነ ጌታ በሰጠን አደራ ልንተጋ ይገባልም የግድም ነው፡፡ ስለዚህ መትጋት የግድ ነው፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ማርቆስ 16፡15፡፡ እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።ሉቃስ 9፡6፡፡እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።የሐዋሪያት ሥራ 8፡25::

 

ስለዚህ ትጋታችን በምን ላይ ይሁን?

መፅሃፍ ቅዱሰ ሲናገር ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ ለጌታ ተገዙ ሮሜ 12፡11

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትጋት ብቻ ተናግሮ አያበቃም፤ ይልቁንም የምንተጋበትን ጉዳይና በምን መትጋት እንዳለብን ጭምር ይነግረናል። የእግዚአብሔር ቃል በብዙ ቦታ ትጉ ይላል። የምንተጋባቸውን ሲገልፅልን፡-

  1. በቃል እንትጋ፡- እኛ ግን ለፀሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 6፡4
  2. በህብረት እንትጋ፡- በሐዋሪያት ትምርና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየፀሎቱም ይተጉ ነበር፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 2፡42፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማሪያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ የሐዋሪት ሥራ 1፡14::
  3. በሥራ፦ የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። 5 በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል።  ምሳሌ 10፥4፡፡ የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች።ምሳሌ 13፥4
  4. በጸሎት፦ እኛ ግን ለፀሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 6፡4
  5. በአገልግሎት፦ “ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ።” ሮሜ 12፥11፡፡
  6. በመልካም ሥራ፦ “ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።” 1ኛ ተሰ. 5፥15::

መትጋት ያለብን ለምንድነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የትጋትን አስፈላጊነት በግልጽ እና በአንክሮ ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል መትጋት ያለብንን ሲያስተምረን፦

  1. ለክርስቶስ ምፅአት ለመዘጋጀት፡- "ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።" ማር. 13፥32-36
  2. ወደፈተና እንዳንገባ ነው። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።” ማር. 14፥38
  3. ወደፊት ሊመጣ ካለው፣ከሚመጣው ሁሉ ለማምለጥና በሰው ልጅ ፊት ለመቆም ነው። “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” ሉቃ. 21፥36
  4. መጠራታችንንና መመረጣችንን ለማጽናት ነው። “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።” 2ኛ ጴጥ. 1፥10
  5.  ለመግዛት ነው። “የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።” ምሳ. 12፥24
  6. ለባለጠግነት/ ባለጠጋ ለመሆን ነው። “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች።” ምሳሌ 10፥4

የትጋት ጠላት ወይም ፀር

1.  መታከት

የታካች እጅ ጭግረኛ ታደርጋለጭ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች ምስሌ 10፡4

2.  ስንፍና

ከስንፍናዬ የተነሳ ቁስሌ ሸተተ በሰበሰም መዝሙር 38፡5፡፡ የሰው ስንፍና መንገዱን ታጠምምበታለች ልቡም በእግዚአብሄር ላይ ይቆጣል፡፡ ምሳሌ 19፡3

3.  ሥራ ፈትነት

ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣበታለች የታካች ነፍስ ትራባለች፡፡ ምሳሌ 19፡15

4.  ዳተኝነት

በእምነትና በትዕግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እሰኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፡፡ ዕብራውያን 6፡11-12፡፡

5.  ሥጋ

ወደ ፈተና እዳትገቡ ትጉና ፀልዩ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው፡፡ ማቴዎስ 26፡41

 

የሚተጉ ሰዎች ምልክት

1.  ስለ ጊዜ ጠንቅቀው ያውቃሉ

2.  ታጋሾች ናቸው

3.  ስንፍና አይታይባቸውም

4.  ለዓላማቸው ጨከኞች ናቸው

5.  የሚያዘናጉአቸውን አይሰሙም

6.  ከአላማቸው ጋር ከሚግባባና ከሚስማማ ጋር አብረው ይሠራሉ፣ ይዘልቃሉ

7.  ትኩረታቸው ሥራቸው ላይ ነው

8.  ትኩረታቸው ግብ ላይ ነው

9.  ለሚቃረኑዋቸው መልሰ አይሰጡም

 

የሚተጉ ሰዎች ከምንም በላይ ዋጋ የሚሰጡባቸው

1.  ለፀሎት ዋጋ ይሰጣሉ

2.  ለእግዚአብሔር ቃል ዋጋ ይሰጣሉ

3.  ለፀሎት ሰፊ ጊዜ ይሰጣሉ

በመጨረሻም

ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፡፡ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡10::

 

ተባረኩ

አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ

+25102910126/ +251911835440/ +251916276339

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

---------------------------------------------------------------------

የእግዚአብሔር ሞገስ በሕዝቡ ላይ

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: Literature/ስነ-ጽሑፍ

የእግዚአብሔር ሞገስ በሕዝቡ ላይ

የእግዚአብሔር ሞገስ

ሞገስ

ሞገስ ማለት ምን ማለት ነው? “ሞገስ” የሚለው ቃል “ካሪስ” ከሚለው ከግሪክ ቃል የተወሰደ እና የተዛመደ፣ አቻ ትርጉም ያለው ሲሆን የእግዚአብሔር ባለጠግነት ፣ ምህረት ፣ ነፃ ስጦታ ፣ ሽልማት ፣ ያልተገባ ወይም ለማይገባው፣ ሊገባውም ለማይችል ግን የተሰጠ፣ የተቸረ የሚልን ትርጉም ይይዛል፣ ይዟልም፡፡ 

 

ብዙውን እኛ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር እንዲሰጠን ከምንፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ሞገስ ነው። በእርግጥ እግዚአብሔር ቸር ነው፣ ለጋሽም ነው፣ ሰጪም ነው። ሆኖም ግን በመሠረታዊነት የምንስታቸው ወሳኝ ነገሮች፣ ከግንዛቤ የማናስገባቸው፣ ችላም የምንላቸው ናቸው። ግን እጅ ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች እና እውነታዎች ናቸው። እነዚህም መሠረታዊ ነገሮች ከእግዚአብሔር የምንፈልገውን ነገር የሚያሰጡን ናቸው። ቅድመ ሁኔታን አመላካች ናቸው። ስለዚህ አውቀን፣ ተረድተን ልናደርጋቸው፣ ልንተገብራቸው የግድ የሆኑ እና በቅድመ ሁኔታ ከእኛ የሚጠበቁ ናቸው። የሚጠበቅብንን ካደረግን በቀጣይ ከእግዚአብሔር የለመንነውንና የምንጠብቀውን ለመቀበል የምንችልበት ነው።

Read more: የእግዚአብሔር ሞገስ በሕዝቡ ላይ

የእግዚአብሔር ሞገስ

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: Literature/ስነ-ጽሑፍ

             የእግዚአብሔር ሞገስ

ሞገስ

ሞገስ ማለት ምን ማለት ነው? “ሞገስ” የሚለው ቃል “ካሪስ” ከሚለው ከግሪክ ቃል የተወሰደ እና የተዛመደ፣ አቻ ትርጉም ያለው ሲሆን የእግዚአብሔር ባለጠግነት ፣ ምህረት ፣ ነፃ ስጦታ ፣ ሽልማት ፣ ያልተገባ ወይም ለማይገባው፣ ሊገባውም ለማይችል ግን የተሰጠ፣ የተቸረ የሚልን ትርጉም ይይዛል፣ ይዟልም፡፡ 

Read more: የእግዚአብሔር ሞገስ

ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋይ፤ አገልግሎትና አደራ

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: Literature/ስነ-ጽሑፍ

ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋይ፤ አገልግሎትና አደራ

ቤተ ክርስቲያን ባለቤቷ እግዚአብሔር እንደሆነ በሁሉም ዘንድ እሙንነት እና ተአማኒነት  ያለው ሐቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በምድር ላይ ሲተክል የራሱን አላማ፤እቅድና ግብ ኖሮት ሊያሳካ የመሰረታት ናት፡፡ ይህችም ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች እና የተገዛች ነች፡፡

Read more: ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋይ፤...

  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • ጊዜ
  • ትጋት
  • ሐሰት፣ ሐሰተኛ፣ ሐሰተኝነት እና መገለጫቸው

Article Categories

  • Literature/ስነ-ጽሑፍ
  • Gospel Thoughts / የወንጌል አስተምህሮ
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
  • Testimony/ምስክርነት
  • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን

Login Form

  • Forgot your password?
  • Forgot your username?
Copyright © 2025 yegizewkal. All Rights Reserved.