yegizewkal
ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። ትንቢተ ኤርምያስ 15፥16

  • Home/መነሻ ገጽ
  • Gospel Thoughts/የወንጌል አስተምህሮ
    • ነገረ ድነት/Salvation
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
    • Literature/ስነ-ጽሑፍ
    • ከመጽሐፍት ዓለም
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን
    • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Testimony/ምስክርነት
  • ማስታወቂያ/Advertisement
  1. You are here:  
  2. Home
  3. Gospel Thoughts/የወንጌል አስተምህሮ
  4. ነገረ ድነት/Salvation

ነገረ ድነት/Salvation

ሐሰት፣ ሐሰተኛ፣ ሐሰተኝነት እና መገለጫቸው

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ነገረ ድነት/ Salvation

   

 

   መምህር በረከት ሱላሞ ሱጌቦ

      Bereket Sulamo Sugebo

   ሀዋሳ/ ሲዳማ/ ኢትዮጵያ

      Hawassa/ Sidama/ Ethiopia

 

ሐሰት፣ ሐሰተኛ፣ ሐሰተኝነት እና መገለጫቸው

                                                                   “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ ....”

ኤፌሶን 5፥11 

መግቢያ

ስለ ሐሰተኞች አስተማሪዎች፣ አገልጋዮች እና ነቢያት ሲነሳ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸው ተጽእኖ ሁሌም በአእምሮአችን ላይ የሚመጣው እንድምታ እና በብርቱ ሊታወሰን የሚገባ ብርቱ ጉዳይ ቢኖር ስራቸውና አስተምህሮታቸው ነው። 

ነው። ሐሰተኞችና የሐሰት ትምህርታቸው ምን ያህል ለቤተ ክርስቲያን፣ ለእውነተኛ ቅን አገልጋዮች፣ ለአማኝ ክርስቲያንና ለሐገር ምን ያህል ተግዳሮት እንደሆኑ የማይታበል እና ልንክደው የማንችለው ሐቅ ነው። 

ለቤተ ክርስቲያን የእነርሱ ተግዳሮት የዛሬ ሳይሆን ከጥንትም  ከጌታችን ከክርስቶስ መወለድ በፊት በብሉይ ኪዳን ዘመንም የነበረ ነው። “ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?” — ኤርምያስ 5፥31። “በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ።” — ዘካርያስ 13፥2 ::

ሐሰተኞች ከሚለዩባቸው ዋነኛ ምልክቶች አንደኛው ከእውነተኛው እምነት ባፈነገጠ በተፃራሪ ጎን በመቆም የተቃዋሚነት ስሜት ያለውን ሐሳብ ከእግዚአብሔር እንደ  ተቀበሉ አድርገው በማቅረብ ከራሳቸው ስሜት በመነሳት፣ ሁኔታን በማየት ሰውን ማሳሳትና ወደ ጥፋት መምራታቸው ነው። “አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ።” — ኤርምያስ 23፥25
ሰው በቀላሉ የሚታለለው ሐሰተኛው አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም በመነሻነት ይዞ መቅረቡ ሲሆን አድማጭ ተመልካቹም በቀላሉ ለሐሳባቸው ተገዢ ይሆናል የቀድሞውን እውነተኛ እምነቱን በቀላሉ ይጥላል።

ዝርዝር ሃሳብ

ነብይና ነብይት፣ አስተማሪ የመሆን ጸጋ እግዚአብሔር ወድዶና ፈቅዶ ለሰው ልጅ እንዲያገለግሉና እንዲያገለግሉት የሚሰጥ ስጦት እንጂ፣ ይህም ጥሪ የሚመጣው ከጌታ ሲሆን፣ እግዚአብሔር አንድን ሰው ለዚህ ስራ ሲጠራውና ሲለየው ታማኝ አድርጎ ቆጥሮት ጸጋውን የሚሰጠው ሲሆን ይህንንም እግዚአብሔር በወሰነው ስፍራና ጊዜ ለፈቀደው እና ለወደደው ሰው የሚሰጠው ሹመት ነው። 

እንዱ የሐሰተኞች ነቢያትና አስተማሪዎች መለያ ከእግዚአብሔር በጥሪ የተቀበሉት ሳይሆን አንድም እራሳችውን ነቢያትና አስተማሪዎችዎች ብለው ሰይመው መሾም፣ አሊያም በሰዎች ሹመት ሲሆን፣ ይህንንም በዚህ የትምህርት ዝግጅት  ውስጥ ባህሪያችውንና መገለጫ ባህሪያቸውን እናጤናለን። “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና?   ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?”— 2ኛ ቆሮ 6፥14 

ሐሰተኞች በምን ይታወቃሉ፦ በአያሌው መታወቂያቸው እና በቀላሉ የምንለያቸው በእነዚህ እንቅስቃሴዎቻቸው ነው።

1-አሳቾች ናቸው፦ በተለይ አውድ አፈንግጥ የማስተማር ዘዴያቸውን በመጠቀም፣ ቃል ነጠቅ በተለይ ጥቅስን ከአውዳዊ ፍቺ ወጪ ትርጉም በመስጠትና በመሰንዘር የስህተት አስተምሮአቸውን በሌሎች ላይ ያጭቃሉ። በተለይ ዋነኛ አስተምሮአቸው የክርስቶስ የልቡ አጀንዳ ባልሆነ፣ ከሐዋርያት ትምህርት ወጪ የሆነን አስተምሮ በመያዝ የሚነጉዱ ናቸው።“በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።” — ሐዋርያት 2፥42። ስህተታቸውን ቢነግሯቸውም ሊያስተውሉ አይችሉም። “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።”— ማርቆስ 13፥5። በተለይ ዋነኛ መለያቸው እንዳወቀ፣ የጨረሰና የበቃ ምሁር በማድረግ ራሳቸውን በመቁጠር ለሌሎች ራሳቸውን በግለጥና ማሳየትን ይመርጣሉ።

2- አመፀኞች ናቸው፦ ለእውነት እንዳይታዘዙ አዚም የተደረገባቸው ያህል የደረሱ ናቸው። እውነትንም እያወቁ በሌሎች እንዳይተቹ በአመፀኝነታቸው ይቀጥላሉ። ዋነኛ መገለጫቸው ለታላላቆቻቸው አለመታዘዛቸው ሲሆን በእምቢተኝነታቸው በመቀጠል አመፀኛ መሆናቸውን ይቀጥላሉ። በሚበልጥ ሃሳብ የማያምኑ ወይም በሃሳብ ብልጫ፣ በተጠይቃዊ አስተሳሰብ እንኳን የማያምኑ ናቸው። እውነተኛውን አገልጋይ እና እውነትን በአመፃ ለመጋረድ ይከለክላሉ።“እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤” — ሮሜ 1፥18

3- የጥፋት ምንጮች ናቸው፦ በእውነተኛው አገልጋይ ስር ባሉ ተከታይ አማኞች ዘንድ እና በራሳቸው ተከታዮች ዘንድ የጽንፈኝነት ሐሳብን በመፍጠር በጎራ በተደራጀ መልኩ ከሐሳብ ግጭት ባለፈ እስከ አካላዊ ጥቃት ተፈላልጎ እስከ መቀጣጠር በሚያደርስ ጎራዊ ክንፍ በማበጀት ለሐገርም ይሁን ለማህበረሰብ እረፍት የሚነሳ የጥፋት ምንጭና ሐሳብ ያፈልቃሉ። በሐሳብ ብልጫ በማያምን ጎራዊነት ይፈላለጋሉ። በተለይ በዚህ በስልጣኔ ዘመን የማህበራዊ መገናኛን በመጠቀም የሚታየው መቆራቆስ ዋነኛ ማሳያ ነው።

4- ስም ተሸካሚ ናቸው፦ በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተንተርሰን የምናየው እውነታ በገሃዱ አለም አሁን የምናያቸው አገልጋዮች የያዙት ስም (ማዕረግ ልበለው) እጅግ በጣም የተራራቀ ነው። በዋናነት የያዙት ስም በሐገራችን የነበሩ ቀደምት የወንጌል አርበኞች፣ በእግር በፈረስ ተጉዘው እጅግ ብዙ ቤተ ክርስቲያን የመሠረቱና ሠርተው የተከሉ ሊጠሩበት እንኳን የማይደፍሩትን የዛሬ ዘመን ደፋሮች ይዘውት እናያለን። “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤” — ራእይ 2፥2

5- አሳዳጅ ናቸው፦ የያዙትን የሐሰት ትምህርት እና ትርክት የሚቃወማቸውን፣ ስሕተታቸውን እንዲያርሙ የሚመክሯቸውን በመንገዳቸው የቆሙ ያህል በመቁጠር ድጠውና አጥፍተው፣ አሳድደው ይባስ ብለው እስከ ህይወት ማጥፋት የሚደርሱ ናቸው። 

በተለይ በንዋይና በምንዳ የተደራጁ ከሆነ ከእኔ በላይ ለአሳር በማለት በእጅ መንሻ ለእውነት የሚኖሩትንና የሚሠሩትን እግር በእግር በመከተል ከየትኛውም ስፍራ ማራቅና ማጥፋት አይነተኛ ባህሪያቸው ነው።

6- ውሸተኞች ናቸው፦  የመገናኛ አውታር ላይ በመገለጥ ከሚታይ ባህሪያቸው አንፃር ብንመለከት፣ የምናያቸው ነገሮች ለጆሮ የሚቀፍፉ፣ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ቀፋፊ ጉዳዮች ከእውነት የራቁና ያፈነገጡ ናቸው። የእነርሱ ውሸት የባህሪየቸው መገለጫና የማይቀረፍ ልማዳቸው ነው፣ ተላምደውትም የኖሩት ለህሊናቸው የማይቀፋቸውና የማይቆጠቁጣቸው ነው። በክርስቶስ ትምህርት ላይ መሠረት ያላደረገ አስተምሮታቸው እና የክርስቶስ የልቡ ሐሳብ ባልሆነ አስተምሮታቸው ያፈነገጠ መሆኑ አንዱ የውሸተኝነት መገለጫቸው ነው።“እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና።”  — 2ኛ ቆሮ 11፥13

7- ውጫዊ ማንነታቸው ከውስጣዊ ማንነታቸው የተለየ ነው፦ ንግግራቸው እጅግ የዋህ፣ ፃዲቅ እና ቅን የመሰሉ ሲሆኑ ውሰጣቸው የቅሚያና የዝርፊያ መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው። በውጫዊ ነገራቸው የማንጠረጥራቸው ሆኖም ግን ከብዙ ቆይታ በኋላ በመቅረብ የምንለያቸው ናቸው። በአንድ ጀንበር አንለያቸውም ልንጠረጥራቸውም አንችልም። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” — ማቴዎስ 7፥15

8- በፍሬያቸው ይታወቃሉ፦ ከፍሬያማነት አንፃር ስንመለከት እነዚህ ሰዎች በጭራሽም ይዘን የተነሳነው ይሄ ነው ብለው ቢነሱም ነገራቸው በፍሬ የታጀበ አይደለም። ከተነሱበት ጉዳይ አንፃር ብንመለከትም ነገሮቻቸው በፍሬ አይገለጥም። ከእነርሱ የሚጠበቅ ነገር አይኖርም። “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?” — ማቴዎስ 7፥16

9- ድንቅና ምልክትን ለማሳት ያሳያሉ፦ ሐሰተኞች በባህሪያቸው የእኛን ትግል የሚፈልጉና የሚገዳደሩ ናቸው። ሌሎችን በሚያደርጉት ድንቅና ምልክት ከእውነት እን ከእውነት መንገድ ሰው እንዲያፈነግጥ ያደርጋሉ፣ ከክርስቶስ ላይ ትኩረት ለማንሳትና ወደ ራስ ለመሳብ የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ድርጊቶችን ያነሳሉ። ይህ ማለት በሌሎች ላይ ጥርጥር እንዲያነሱና ከአላማ ፈቀቅ የማድረግ ሥራን ይሠራሉ። ጥርጣሬን በዋነኛነት በሌሎች ላይ ይጨምራሉ። ለዚህም ማሳያው የፈርዖን አስማተኞች ከሙሴና ከአሮን ጋር በንጉሱ ፊት ያደረጉትን ልብ ማለት ይቻላል። “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” — ማቴዎስ 24፥24

10- አስተምሮታቸው ከንቱን ነው፦ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ያልሰሙትን፣ እግዚአብሔር ያልነገራቸውን በስሙ እንዲህ ይላል በማለት ይቀርባሉ። በተለይ በዚህ ዘመን ከተመለከትናቸው ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ይሄ ነው። በመገናኛ አውታር በመጠቀም የተነገረን እና የሰማነው ለዚህ እማኝና አስረጂ ነው። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ።” — ኤርምያስ 23፥16

11- ከእኛው ጋር አሉ፦ በየትኛውም ዘመን ይሁን ሐሰተኞች የተለየ የመኖሪያ ስፍራ ከከተማ፣ አሊያም ከሰው መኖሪያ ራቅ ብለው አይደለም ሚገኙት። ይልቁኑ በአቅራቢያችን እኛው ውስጥ ነው ያሉት። በቤተ ክርስቲያን እንኳን ተሰግስገውና አላማቸውን አንድም በግልጽ ወይም በስውር ስራቸውን ይሰራሉ።“ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤” — 2ኛ ጴጥሮስ 2፥1።“ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።” — ራእይ 2፥14። “እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።”
  — ራእይ 2፥15
12- መመርመር አለባቸው፦ መነሻቸው ከጨለማው አለም ሲሆን በብዙ ዘዴና ብልሃት ሥራቸውን ለመሥራት ከጨለማው አለም ተመድበው የሚሠሩ ናቸው። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ይሁኑ አይሁኑ በእግዚአብሔር መንፈስ መለየት መቻል አለብን። “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” — 1ኛ ዮሐንስ 4፥1።

13- ምግባረ ብልሹ ናቸው፦ በተለይ ያላቸው ባህሪ እጅግ ጸያፍ ሲሆን ይህ ምግባራቸው በተለይ በዋናነት የሚገለጠው ለቀደሙ አባቶች ቦታና ክብር የላቸውም፣ ዘወትር በዘለፋቸው ይታወቃሉ። ለቀደሙ አባቶች፣ የእግዚአብሔርን መንገድና እውነትን ላሳዩአቸው፣ በእግዚአብሔር ቃል እውነት አስተምረው ያሳደጉአቸውን ክብር አይሰጡአቸውም። “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።”— ዕብራውያን 13፥7።

14- ወቅታዊና ሁኔታዊ ናቸው፦ በተለይ ይኸኛው አደገኛና ጎጂ ባህሪያቸው ነው። በከፍተኛ ሁኔታ አብዛኛውን ክርስቲያን የሚያስቱበትና የሚያሳስቱበት ትልቁ ዘዴያቸው ነው። የሰውን ፊት፣ ዝና፣ ሐብት በማየት የሚተነብዩበት መንገዳቸው ነው። የሰውን ልብ ትርታ ላይ ተንተርሰው ደጋፊ ለማብዛት ጣፋጭና በሰው ስስ ሐሳቡን በመንካት የሚናገሩና የሚያስተምሩ ናቸው። “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።”— ሉቃስ 6፥26።

በተለይ በውስጣቸው የማታለልና የቀማኛነት ባህሪ ስላለባቸው የሚመጡበት መንገድ በማይነቃ መልኩ ወደ ሰው ልብ ይቀርባሉ። “ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ።”— ኤፌሶን 5፥6።

15- የአስተምሮ አቋማቸው፦ የአስተምሮ አቋማቸው ከራስ ሐሳብ በመነጨ እንጂ መሠረታዊ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ተንተርሶ እና ተመስርቶ የሚቀርብ ትምህርትም አስተምሮም የላቸውም። በተለይ ዋነኛ ሐሳባቸው ጽንፍ ይዘው የሚለዩበትን አስተምሮ ይዞ በዋናነት ማቀንቀን ሲሆን በዚህም ሐሳብ የክርክር መድረክን መፍጠርና ሕዝበ ክርስቲያንን ሥራ ማስፈታት ነው።

እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።  — 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥3። በተለይ በዚህ ረገድ የሚወሰዱ ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስር ሰድደው ያልቆሙ ሲሆን እነዚሁ ሰዎች ለእነርሱ የጠበቃ ያህል ተከራካሪና ተሟጋች ይሆኑላቸዋል ደግሞም ናቸው። አስተምሯቸውም ይሁን ትምህርታቸው ሰውን ተኮርና ሰውን ያማከለ ነው። በክርስቶስ ትምህርት ላይ መነሻ አድረገው የሚነሱት ትምህርት የላቸውም። “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥9። ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝና የሚያጣብቅ ትምህርት የላቸውም፣ ምድራዊና ሰው ተኮር ነው።“የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።” — ማቴዎስ 15፥9 “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”
  — ቆላስይስ 2፥8።

16- የተቃርኖ ሐሳብ ያነሳሉ፦ በዋናነት የሚያስተምሩት ትምህርት እና እውቀት ስለሌላቸው ለመታወቅ በማሰብና ታዋቂነትን፣ ዝነኝነትን በመሻት የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገሩትን በመተቸት እና በመንቀፍ፣ ተዋቂ የሆነ የቅንነት አገልጋይን በመንካት ተዋቂ ለመሆን የሚጥሩበትን መድረክ በመፍጠር ራሳቸውንም በማሳየት ሌሎችንም በቀላሉ በመሳብ ደጋፊንና ተከታይን ያፈሩበታል የሰውን ትኩረትም ይስባሉ፤ትኩረትን ወደ ራሳቸው ይስባሉ። በዚህም መንገድ አይነታቸውን ያበዛሉ። ቅንና በመልካም አስተምሮአቸው የሚታወቁትን ያደበዝዛሉ፣ ያጠፋሉ ሌሎች ሰሚዎቻቸውን በጥርጥር እንዲታዩ በማድረግ የነዚህን ሰዎች ቦታና ዕውቅና ይወስዳሉ። ይህም ዋነኛ ዘዴአቸው ነው። “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤” — ሮሜ 16፥17።

17- አፈንጋጭ ሐሳባውያን ናቸው፦ በአንድ ነጠላ ሐሳብ ላይ እርሱም የክርስቶስ ትምህርት ባልሆነ፣ የክርስትና መሠረተ ሃሳብ በሌለው ትምህርት ላይ በመመርኮዝ ለዘመናት በማቀንቀን ይዘልቃሉ፣ ሌሎችንም በዚህ እምነት በመክተት አራማጅ ያደርጓቸዋል። ቋሚ የሆነ የእምነት መሠረት ሐሳብና መግለጫ የላቸውም፣ ማሳያም የላቸውም። “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥9።  “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥10። 

ሁልጊዜ በዘመናት እና በሕዝብ መሐል እንግዳ ትምህርት ይዘው ይበርባሉ። ይህም እንግዳ ትምህርት ለክርክርና ለጠብ እስከሚያደርስ ድረስ እንደ ትልቅ ጉዳይ በሕዝብ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በሐገር እንደ ትልቅ ጉዳይ የመጋገሪያና መከራከሪያ ሆኖ ይቀርባል። “ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።” — ዕብራውያን 13፥9።

መደምደሚያ

ሐሰተኛ አገልጋይ፣ ነብይ እና አስተማሪ እኔ እውነትን እያደረግሁ ነኝ ከማለት ውጪ የሚሠሩትን የትኛውንም ሥራ እንደ እግዚአብሔር ቃል ሰከን ብለው የሚመረምሩና የሚገመግሙ አይደለም። ስለ ሚሠሩት ሥራ ቢነገራቸው በፍቅር የመስማት ትዕግስት፣ ሌላውን የማዳመጥና የሚበልጡኝ አሉ የሚል የትህትና መንፈስ ጨርሶ የላቸውም። 

በተለይ በዚህ በስልጣኔ ዘመን ሁሉን የመገናኛ አውታር በመጠቀም አጀንዳቸውን፣ አስተምሮታቸውን እጅግ በፈጠነ መልኩ እየሠሩ ይገኛሉ። ከዚህም የተነሳ ለቁጥር የሚያታክት ተከታይና ደጋፊ አቀንቃኝም አፍርተው እጅግ እየሰፉና እየበዙ ሲሆን የቀደሙት ግን ከእነርሱ በተሻለ በንቃትና በትጋት ጥበብ በሞላበት አካሄድ እየሠሩ አይገኙም። እኛም በራሳችን ጉዳይ ተጠምደን እነርሱ ግን በየትኛውም መንገድ በመፍጠን የሐሰተኛውን ክርስቶስ ሥራ እያራመዱና እያስፋፉ ይገኛሉ።

የመፍትሔ ሐሳብ

ከንግግርና ሐሳብ ከማፍለቅ ባለፈ ሐሰተኞች ከሚፈጥኑት ፍጥነት በላይ በመፍጠን ሥራን መሥራት እጅግ ተገቢ ነው። በተለይ የራሳችንን አስተምሮና የእውቀት ደረጃችንን በመገምገም እጅ ለእጅ በመያያዝ እውነተኛውን የክርስቶስ ትምሀርት በማስተማር፣ ምእመናን የሐሰተኛን አስተምህሮ መቋቋም እንዲችሉ መርሐግብር በተበጀተለት መልኩ ማስተማር ተገቢ ነው። በተለይ እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አሰተምህሮ በማሳየት፣ ሐሰተኞች ይዘውት የተነሱትን አስተምህሮ በመንቀስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስተምሮአቸው ምን ይላል በማለት እውነተኛውን ማሳየት እጅግ ተገቢ ነው። 

በመጨረሻም፦  ልናጤናቸው የሚገቡን አብይና ብርቱ ጉዳዮች

1- በታመነ ቃል መጽናት

“ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።”— ቲቶ 1፥9

2- የሚገባውን መናገር

“አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር።”— ቲቶ 2፥1

3- ትምህርት ላይ ማተኮር

“የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ።” — ቲቶ 2፥7-8

4- ለትምህርታችን መጠንቀቅ

“ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።”— 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥16

ስለዚህ ምን እናድርግ

• ልንታገሳቸው አይገባም፦ “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤” — ራእይ 2፥2

• የእውነትን ቃል እንናገር፦ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።” — 2ኛ ቆሮ 2፥17

• በግልጽ ልንቃወማቸው ይገባል:- “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።”— 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥16 “የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ።” — ቲቶ 2፥7-8

                                       “ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ                                         ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።”

                                                                                           — ቲቶ 1፥9

ተባረኩ
አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ 

 

እግዚአብሔርን መስማት

Details
Written by: Bereket Sulamo
Category: ነገረ ድነት/ Salvation

እግዚአብሔርን መስማት

"ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፤ አስተዋይም ምልካም ምክርን ገንዘቡያደርጋል፡፡" መጽሐፈ ምሳሌ 1፡5

የሰው ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ እስከ ህይወት ፍፃሜው ድረስ አራት የተግባቦት ክህሎቶችን ያልፋል፡፡ አንድ ህፃን ተወልዶ ከእናቱ የሚሰም ሲሆን የሰማውን ከጥቂት የዕድገት ጊዜያቶች በ    ኋላ የሰማውን መልሶ ለመናገር የመጣጣር ሲሆን፤ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ የፊደል ልየታን የንባብ ጊዜን በመማር ቀጣዩን እና የመጨረሻውን ወደ መፃፍ ይሸጋገራል፡፡  

ብዙ ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች መስማት የሚያስፈልገንን ሳይሆን መስማት የምንፈልገውን ብቻ እየመረጠን የምንሰማ ከሆነ እጅግ ከባድ አደጋ አለው። በተለይ በዚህ ዘመን እግዚአብሔር እንዲናገረን የምንሻው በጎ፣ ደስ የሚልን፣ ምቾታችንንና ፍላጎታችን የሚነካውን ብቻ ነው። እግዚአብሔር የፈለገውን የልቡን ሐሳብ በተለይም የግሳጼን ነገር ጨርሶ ልንሰማ አንፈልግም። ስንስትና ስንሳሳት እግዚአብሔር ሊገስጸን ሲፈልግ የማንሰማው ነገር ከእሱ የሚለየን ነገር መሆኑን አለማወቃችን እጅጉን የሚጎዳን ነው። 

እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ የሚናገር ነው፣ የሰው ልጅ ግን እምብዛም ሲሰማውና ሲያደምጠው አይገኝም። መስማት አንደኛው የመግባቢያ መንገድ እንደሆነ ከቁብ አናስገባውም።

በመስማት ውስጥ አንድ የሚተላለፍ ወሳኝ መልዕክት እንዳለው ልናውቅ ይገባል። 

መስማት እግዚአብሔርን ከሚያስደስቱት ነገሮች አንደኛው ነው። እርሱን ስንሰማው ደስታው ነው። እግዚአብሔርን ስንሰማው እጅግ እያስደሰትነው እንደሆነ አለማወቃችን አንዱ ችግራችን ነው። በመስማት እጅግ ብዙ በረከት አለው።

እግዚአብሔር ሁልጊዜ ደስታ ያለበትን ነገር፣ መልካም ዜና፣ የምስራች ይዞልን አይመጣም። እግዚአብሔር ባህሪው ማስደሰት ብቻ አይደለም፣ የሳተ እንዲመለስ ይናገራል፣ ያጠፋን ይገስፃል፣ መስማት ግን የእኛ ትልቁ ምላሽ ነው፣ የዚህን ጊዜ እንዳመለክነው ሊገባንና ልንረዳ ይገባል። ሲገስጽ እንዲህ ይላል፦ የኤፌሶን ቤተክርስቲያንን ሲናገር "ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውን ሥራህን አድርግ" ራእይ 2:5፣ በማለት ይገስፃል። በሌላ መልኩ ደግሞ ለፍላደልፊያ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ይናገራል፦ "እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና" ራእይ 3:8። በማለት ድምጹን ያሰማል።

ምንድ ነው ምንሰማው

  1. የእግዚአብሔርን ሕግ- ሮሜ 2፡13 በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና፡፡
  2. እግዚአብሔርን ቃል- ያዕቆብ 1፡22 ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። 23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ያዕቆብ 1፡23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል
  3. የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ

በክርስትና ሕይወታችን መስማት ማለት፦

  1.  የሚናገረንን እግዚአብሔርን ማምለካችን ነው
  2.  ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠታችን ነው
  3.  እግዚአብሔርን አንተ ልክ ነህ እያልነው ነው

እግዚአብሔር ሲናገረንና ስንሰማው የሚበጀንን እየነገረን ነው፣ ሲገስጸን ደግሞ እየተጣላን አይደለም፣ ያልተደሰተበትን ጉዳይ፣  ያልተመቸውን እየነገረን ነው።

እግዚአብሔርን መስማት በውስጡ በረከቶች አሉት፣ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እና መሠረታዊዎቹን እንመልከት፦

1-መስማት ለበረከት 

ብዙውን በአስተምሮአችን ወይም በስብከታችን መስማት በረከት እንደሆነና እንዳለው ስንነግር አንታይም አንደመጥም። መስማት ግን በረከትን የሚያመጣ፣ የሚያስከትል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሰማን ማለት የቃሉን ባለቤት አከበርነው ማለት ነው። "የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል።" ዘዳግም 28:2

ማስታወሻ፦  ዘዳግም 28:2-14 ያንብቡ

2- አለመስማት መርገምም አለው

መስማትን ብቻ ተናግሮ መተዉ ተገቢ ባይሆንም፣ አለመስማትን መናገር ተገቢ ነው፣ ባለመስማት የሚመጣን ችግር በውል ለማወቅ ይረዳልና። እግዚአብሔርን አለመስማት በራሱ የሚያመጣው ፈርጀ ብዙ አሉታዊ ነገሮች አሉት። አለመስማት ለበረከት ሳይሆን ለእርግማን ከሚዳርጉ ነገሮች አንደኛው ነው። "ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትዕዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።" ዘዳግም 28:15

ማስታወሻ፦  ዘዳግም 2:15 ጀምሮ ያለውን ያንብቡ

3- መስማት ለመረጋጋት

ብዙውን ጊዜ በህይወታችን ውስጥ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣትን እናያለን፣ ይህም ከምን አኳያ መጣ፣ ለምን መጣ፣ በምን ምክንያት መጣ ብለን ሰከን ብለን ስናጤንና ስናጠና አንታይም። የችግሩ መነሻ ምንድነው ብለን ለማወቅ አንነሳም። ለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል አስረግጦ የሚነግረን ቃል አለ፣ የሚናገረንን እግዚአብሔር አለመስማት በተቃራኒው የሚያገኘን የማያረጋጋ ነገር ነው። "የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ስጋት የሠርፋል።" ምሳሌ 1:33

4- መስዋዕት ነው

በመፅሐፍ ቅዱስ መስዋዕት እራሱን የቻለ የአምልኮ አይነት ነው። "...ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና።" መክብብ 5:1። ከአምልኮአችን በፊት የመሚቀድመው እግዚአብሔርን መስማት ነው።

5- እግዚአብሔርን ያስደስተዋል

እግዚአብሔርን ከሚያስደስቱ ነገሮች መካከል አንዱ የራሱን ቃል መስማት ነው። "...በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?..." 1ኛ ሳሙኤል 15:22። ከምንም በላይ ቀዳማይ ነገሩ እግዚአብሔርን መስማት ነው።

የመስማት ትሩፋቶች

  1. መስማት ጥበብን ይጨምራል

ምሳሌ 1፡5 ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። 

   2. መስማት የእምነት ምንጭ ነው

               ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል   ነው።

   3. መስማት ያረጋጋል 

ምሳሌ 1፡32-33 አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ    መሆን ያጠፋቸዋልና። የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።

   4. መስማት በእውነት እንድንሔድ ያደርጋል   

ያለመስማት ውጤቶች

1.   የማይሰማ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት

  ምሳሌ 28፡9 ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።

2.   የማይሰማ የሐሰት ልጅ ይባላል

ትንቢተ ኢሳይያስ 30፡9 ዓመጸኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት  የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና

ስለዚህ ምን እናድርግ?

እግዚአብሔር ስለልጁ ስለክርስቶስ የተናገረውን ብቻ ማድረጉ እጅግ ጠቃሚ ነው፣ ምክንያቱም የክርስትናችን መሠረታዊ ነገር ስለሆነ።

ማቴዎስ እንደፃፈው

1- ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ

"... እነሆም፥ ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ማቴዎስ 17:5

ማርቆስ እንደፃፈው

2- የምወደው ልጄ

"... ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ማርቆስ 9:7

ሉቃስ እንደፃፈው

3- የመረጥሁት ልጄ

"ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ሉቃስ 9:35

እግዚአብሔርን መስማት ይሁንልን!

አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ

+251902910126

 

 

  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • የአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት
  • ጊዜ
  • ትጋት
  • ሐሰት፣ ሐሰተኛ፣ ሐሰተኝነት እና መገለጫቸው

Article Categories

  • Literature/ስነ-ጽሑፍ
  • Gospel Thoughts / የወንጌል አስተምህሮ
  • The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
  • Testimony/ምስክርነት
  • Religious News/ሐይማኖታዊ ዜና
  • Churches/ቤተ ክርስቲያን

Login Form

  • Forgot your password?
  • Forgot your username?
Copyright © 2025 yegizewkal. All Rights Reserved.