የትውልድ አደራ

የትውልድ ባለአደራነትን መወጣት

አደራ ለአንድ የተወሰነ ተግባር እና ክዋኔ ወይም ግዴታ ለአንድ ሰው ሃላፊነት ወይም ስልጣን መስጠት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እና በኃላፊነት እንዲወጣ እምነትን መጣል ሲሆን፣ አደራ የአደራን ተግባር በአደራ፣ በመተማመን እና በአደራ የተሰጠው ሰው አቅም ላይ በማመን ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። 

 

አደራን የመወጣት እና አደራን ከግብ ማድረስ እንዴት ያለ መታደል ነው። በተለይ የትውልድን አደራ ተቀብሎ ትውልድ በመልካም መንገድ የእግዚአብሔርን ሕግ ተከትሎ እንዲሄድ አድርጎ እና በዚህም ፍሬን ማየት እንዴት እጅግ ያስደስታል። 

ትውልድን ከክፋት ነጥሎ ትውልድን በእውነት መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ማገናኘት እንዴት አይነት ትልቅ ሥራ ነው? በእውነት መንገድ ሄደውም ማየትን የመሠለ ነገር የለም። 

በተለይ በትውልድ ላይ በእውነትና በሐቅ እየለፉ፣ እየታተሩ ያሉ ምን ያህል ለውጤት እንደሚተጉ ሲታዩ የጭንቀታቸውን ልክ በጥቂቱ መገመት የሚቻል ቢሆንም እውነታውን የሚረዳው አይነቱ እና እራሱ ባለቤቱ ነው። 

አለም የራሷን ትውልድ ገዳይ አሰናድታ ባስቀመጠችበት ዘመን ቤተክርስቲያን በመዘናጋት ለገዳይ እድልን መስጠቷ ከመዘናጋቷም የተነሳ አጥፊው እየተጋ ባለበት ዘመን አለመንቃት የነገ ተስፋዎቿ እየተነጠቁባት መሆኑ ለአፍታም ግድ ያላላት ምን ልትሠራ? ሥራዋስ ምን እንደሆነ ጠንቅቃ አለማወቋ ትውልድ ከማህፀን ጀምሮ እየመከነ መሆኑ አለመረዳቷ የነገ የቤተክርስቲያን ተስፋዋ ጭምር እየጠፋ መሆኑን አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖአል። “የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ።” — ዘጸአት 1፥15። “እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር።” — ዘጸአት 1፥16። “የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ፦ ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው።”— ዘጸአት 1፥18። የነቁትም ቢሆን እጅግ ጥቂት መሆናቸውና ሥራውም ሰፊ ከመሆኑ አኳያ አለመጣጣሙ ትውልድን ከጥፋት መመለሱ በበቂ ሁኔታ እየተሠራ አለመሆኑ ትልቁ ማሰያና ማረጋገጫ ነው። “አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው።” — ዘጸአት 1፥17። “አዋላጆቹም ፈርዖንን፦ የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት።” — ዘጸአት 1፥19።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ዘመን ለትውልድ ያለውን የጠለቀ ፍቅሩን የገለጠበት መንገድ የሁላችን አእምሮ ውስጥ ያለ ነው። ህፃናት የነገ ተስፋዎች መሆናቸውን ከተናገረበት ንግግር አኳያ መረዳት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ትልልቆች በተሠበሰቡበት የትኛውም ስፍራ ህፃናት እንዲደርሱ አሊያም እንዲገኙ ጨርሶ አይፈቀድላቸውም። "ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም" በሚል ከንቱ ብሂል ህፃናትን እናሳንሳለን፣ እንዲጠጉንም አንሻም፣ አናምናየውም። በእርሪልጅ ባለበት ጥፋት እንደማይጠፋ ይታወቃል፣ አርቆ ማሳደጉ የእኛ ድርሻ ነው፣ ከአይናችንም ባይርቁ መልካም ነው።

ጌታ ኢየሱስና ጴጥሮስ
ዮሐንስ 21:15፣ ለጴጥሮስ የተሰጠው የትውልድ አደራ የሁሉንም የዕድሜ ክልል ያካተተ ሲሆን፣ በተለይ "ቤተክርስቲያኔን በአንተ ላይ እመሰርታለሁ" ማለቱ ምን ያህል ቤተክርስቲያን የትውልድን አይነት ይዛ እንደምትገኝ ማሳያ ነው። ለዚህም ነው ለጴጥሮስ የተሠጠው የትውልድ አደራ ከብዶና በተደጋጋሚ መጠየቁ የጉዳዩ የአደራ ክብደቱን፣ አሳሳቢነትና ኃላፊነትን የሚያሳየው። ስለዚህ በአደራ ባለቤትና ሰጪው ልክ ተረድተን አደራን መወጣት አለብን። ለውጤታማነትና ለፍሬያማነቱም መትጋቱም ጭምር ታሳቢ ማድረጉ መልካም ነው። ቆጥሮ የሰጠን ቆጥሮ ይረከበናል።

መልዕክተኛው_ዮሐንስና_ልጆቹ
የአንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ መልዕክት ፀሐፊው
ዮሐንስ ከመልዕክቱ እንደምንረዳው ምን ያህል ከስሩ ባሉት ላይ እንደሠራና ተደስቶም  ስለ እነርሱ ከሌሎች የሰማውን ምስክርነት፣ የተመሰከረውን በመጥቀስ መናገሩ የልፋቱን ውጤት ማየቱ እንዳስደሰተው በመልዕክቱ ሲናገር እናየዋለን። የልፋቱን ልክ በዙሪያቸው ባሉት ሰዎች ምስክርነት መሠጠቱ የዘራውን ዘር በሌሎች ዘንድ ተዘርቶ ማየቱ እና ፍሬው ወደ ሌሎች መሻገሩ ምን ያህል ደስታን እንዳጫረበት መመልከት ይቻላል።  “ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ።”— 3ኛ ዮሐንስ 1፥1።

“ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና።” — 3ኛ ዮሐንስ 1፥3። “ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፥ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፥ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።” — 3ኛ ዮሐንስ 1፥12። “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።” — 3ኛ ዮሐንስ 1፥4።

ዛሬስ በዚህ ዘመን ያለን እግዚአብሔርን እና የእግዚአብሔርን ሕዝብ የምናገለግል፣ አደራ የተሰጠን በእርግጥ የቀደሙት አባቶች እንዳደረጉት ዛሬም እንዲሁ እያደረግን ይሆን? የትውልድን አደራ ተሸክመን ያለን ተገቢውን ነገር እያደረግን ይሆን?

“ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።” — 1ኛ ሳሙኤል 2፥24።

 ትናንት ትውድን ሊያጠፋ የሞከረ ፈርኦን በቀጣይ በሄሮድስ የቀጠለው ዛሬም ትውልድን ሊያጠፋ የተዘጋጀ መልኩንም፣ ስሙን፣ አይነቱንም፣ አሰራሩንም ቀይሮ የተዘጋጀ መኖሩን ለቅፅበት መርሳት የለብንም። ይልቁን መልኩን ቀይሮ በመምጣት ትውልድን ለራሱ ሊማርክና ብሎም ሊያጠፋ የቆረጠን የጨለማ ተልዕኮ አስፈፃሚን እኛ በእግዚአብሔር ፊት በምናደርገው የትኛውም ትጋት ተልዕኮውን እንደምናፈርስ መዘንጋት የለብንም።

የቤተክርስቲያን_መሪና_ተተኪ_ትውልድ

 ዛሬ ላይ በዚህን ጊዜ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ በይሆንም እጅግ በአብዛኛው የነገ ተስፋ የሆኑት ትውልድ   ላይ እየሰራን አለመሆኑ አልታወቀንም። እየሠሩ ነው የሚባል መከራከሪያ ነጥብ እንኳን ቢነሳ ተልዕኮውና አላማው       ከራስ ጥቅምና ፍላጎት የተነሳ እንጂ የትውልድ አደራነት ተሰምቶት የሚሠራው እጅግ ጥቂት ነው። "የመከሩ ሠራተኞች ጥቂቶች ናቸው" የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል ማሰቡ እጅግ ተገቢ ነው። 

መሪነት አንድም በደጅ አንድም በቢሮ ተቀምጠን ብቻ የምንሠራው ሥራ አይደለም። ለተጠራንበት አላማ ለግቡ መሳካት አውራውን ሥራ መሥራት አለብን። የፈዘዘ፣ የደነዘዘ በምንም አይነት መልኩ ሥራ አይሠራም፣ አጥፊ ትውልድን እንኳን በቅጡ አይመክርም፣ አይገስፅም፣ አይቆጣም፣ ልጆችህ እንዲህ አደረጉ ቢባል እንኳን "እግዚአብሔር የወደደውን ያድርግ" በሚል ሽንፈትና ተስፋ መቁረጥን ያዘለ ከመፍትሔ መሸሻና ማምለጫ ሃሳብን በመሰንዘር ጉዳዩን ወደ ጎን መተው መጨረሻው አያምር አይነት ይሆናል። ትውልድን የሚያረክስና የሚያበላሽ ትውልድ ከመምጣቱ በፊት በእጅ ያለን ትውልድ ከወዲሁ አርቆ ማስተካከሉ መሠረቱን ማስተካከል እንደሆነ ማወቅ ይጠቅመናል። ነገን ዛሬ ላይ እንሥራ። 

ካህኑ ኤሊ እና ልጆቹ

“ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።” — 1ኛ ሳሙኤል 2፥22። ጥፋተኛን አይተን፣ ስለጥፋተኛ ሰምተን "ጆሮ ዳባ ልበስ"፣ "የዝሆን ጆሮ ይሰጠን" ባንል መልካም ነው። “እርሱም አላቸው፦ ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?”— 1ኛ ሳሙኤል 2፥23።
“ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።” — 1ኛ ሳሙኤል 2፥24። እግዚአብሔር ከምናምንቴዎች ጋር እንደማይሠራ ልብ ልንል ይገባል።

ነቢዩ ሳሙኤል እና ልጆቹ

ነብይ ሳሙኤል በዘመኑ ሀገር ምድር ያረፈችበት፣ እግዚአብሔርም ያረፈበት፣ እስራኤል ከጠላቱ ከፍልስጥኤማውያን ያረፈችበት ትልቅ ነብይ የነበረ በሞቱ እንኳን እስራኤል ለቀናት ያለቀሰችለት ትልቅ ነብይ ነበረ። (እንዲህ አይነት መሪ ይስጠን! አሜን!) የነብዩ ሳሙኤል ልጆች ግን እሱ በሄደበት መንገድ ልክ አልሄዱም። በአባታቸው እግር ተተክተው ያገለግላሉ ተብለው የተሾሙና የተቀመጡ አባታቸው በሕይወት ዘመኑ ያልሄደበትን መንገድ በመሄድ እግዚአብሔር በማይፈልግበት መንገድ ሕዝብ እንዲሄድ ከደረጉ፣ የሕዝብንም ልብ ከእግዚአብሔር አሸፈቱ፣ የአህዛብን ስረዓት እንዲመኙ አደረጉ።  “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት።” — 1ኛ ሳሙኤል 8፥5። “የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።” — 1ኛ ሳሙኤል 8፥6።
       

              በመጨረሻም:-
የመፍትሄ_ሐሳብ፡ 
1. የሚሄድበትን መንገድ መምራት
       1.1. ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማገናኘት
እጅግ ከማቅረብና ከመቅረብ በቀጠለ ትውልድ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማቆራኘት፣ እንዲጠብቅና እንዲያሰላስል ማድረግ። “ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።” — ምሳሌ 3፥1።

ልጅን አግባብ በሆነ መልኩ ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ ማስተማር፣ ለነገ እንደሚጠቅመው እና የእግዚአብሔር ቃል ዋስትና እንደሆነ ማሳየት። 

   1.2. ልጅን ማሰልጠን፣ ማስተማር
“ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” — ምሳሌ 22፥6።

“Train up a child in the way he should go: and when he is old, he will not depart from it.” — Proverbs 22፥6 (KJV)

2.  ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማገናኘት
ኢያሱና ሰለሞን የተነገራቸው የእግዚአብሔር ቃል ምክር ሲነገራቸው የነገን፣ የወደፊቱን ነገራቸው የሚሳካው በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመመርኮዝ ብቻ እንደሆነ አጠንክረው ነገረዋቸዋል።

    2.1. እግዚአብሔር ሙሴ ለኢያሱ የነገረውን ኢያሱን ሲያስታው፦
“ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።” — ኢያሱ 1፥7። 

    2.2. ዳዊት ልጁን ሰለሞንን የመከረው ምክር
“በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።” — 1ኛ ነገሥት 2፥3።

3. በአደራነትና በኃላፊነት መምራት
መፅሐፍ ቅዱሳችን በትውልድ ላይ የአደራነትን ተልዕኮ የተሰጠው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ተደጋግሞ የተነገረው ጉዳይ ቢኖር በእያንዳንዱ የዕድሜ ደረጃ ያሉትን ምን እንዲያደርግላቸው እንደሚገባ ጌታችን ኢየሱስ በመንገርና አደራን በመስጠት ነግሮታል። ዛሬም በዚህ ዘመን ላለን ይህንኑ አደራ እንደተቀበልን ማወቅ አለብን። ዮሐንስ 21:15-18 መመልከት ይቻላል።

4. ቤተሰባዊ ምክር መለገስ
ንጉስ ዳዊት ልጁን ሰለሞንን አንድም እንደ ሃገር መሪ፣ አንድም እንደ ወላጅ አባት ምክሩን ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ ነግሮታል። አደራውን ተወጣ። “በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።” — 1ኛ ነገሥት 2፥3። “እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው።” — ኤፌሶን 6፥4። “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።” — ዘዳግም 6፥6። “ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” — ዘዳግም 6፥7።

አደራን መወጣት ይሁንልን!
በረከት ሱላሞ ሱጌቦ