የተቃኘንበትን ቅኝት ያጠፉ ቕኝቶች

 

 

ቀድሞ የመጣንባቸው ትምህርቶች በክርስቶስ ትምህርት የተቃኘንበት፣ ያስተማሩንም የተቃኙበት ቅኝት የክርስቶስ ትምህርት ላይ ሆኖ ዛሬ ላይ መቃኘታችንም ይሁን ቅኝታችን በክርስቶስ ላይ ሳይሆን "ሃሳባቸው ምድራዊ በሆኑ" ከክርስቶስ ትምህርት ቅኝት ውጪ በሆኑ ከምድር የሚሰፉና የሚያጣብቁ ቅኝቶች መብዛታቸው የመከራ ጊዜ ሲመጣ መቋቋም የማይችሉትን ማፍራታቸው ቅኝታቸው ላይ ፈርጀ ብዙ ችግር መኖሩን ያሳብቃሉ።

የዘመኑ የትምህርት ቅኝቶች ለጊዜውም ቢሆን ደስታን ቢያጭርም ለመጻኢው ጊዜ ዘላቂና ቋሚ ያለመሆኑ ቅኝቱ ቢያስደስትም ከማስጨፈር ያለፈ ዘላቂውንና ዘላለማዊ አጀንዳን ከማናጋት ያለፈ እያስረሳን መሆኑን ለአፍታም ሰከን ብለን ነገሮችን አለመቃኘትና መንገድን አለመሰለል ትልቁ ውድቀታችን እንደሆነ አለማወቅ ሐሳባችን በዘመኑ ቅኝትና አጀብ ተዘናግተን ከግንዱ በመለየታችን በፍሬም አለመገለጣችን እንዲያው ባለማፍራታች ተቆርጠን ወደሚነደው ሳንጣል ከወዲሁ መንቃት ተገቢ ነው።

ከቅኝቶቹ በጥቂቱ

ባልገመትናቸው እና ቀድሞ በክርስቶስ እና በክርስቶስ ላይ በነበራቸው ትምህርት እና አቋማቸው የምናውቃቸው ዛሬ ላይ በቀደመው በተነሱበት እና በጀመሩት ቅኝት አለመሔዳቸው ዛሬ ላይ ግን ቃናቸው ጠፍቶ ነገራቸው የኮመጠጠ ለአፍም የጎመዘዘ ነገራቸው ዛሬ ላይ ክርስቶስን ብሎ ለሚኖርና ክርስቶስን ብቻ ለመስበክ የተነሳን አመቺ እና አማራጭ ባሉት መንገድና ብሒል የነዚህን ቅኝት ሊያጠፉ መነሳታቸው የራስን ቅኝት አቀንቅኑልን በሚሉ ለመዋጥ የተነሱ የዘመኑ ተኩላና ቀበሮ አምራቾች ቅኝት የጠፋባቸው፣ ቃና ለዋጮችን ወግድ ብሎ መሸሹ ያለ አማካሪ የሚወሰን ቁርጠኝነት ነው።

እየጠጣን የነበርነውን ንፁሁን ውሃችንን ዛሬ ላይ በተነሱ አገልጋዮች (መነሻቸውን በደረሱበት እንለካ) ነብዩ ሕዝቅኤል እንዳለው በእግሮቻቸው አደፈረሱት፣ መንጋውም ይህንኑ እየጠጣ ጤናማ የነበረውን የመንፈሳዊ ጤንነቱ ታመመ። እንደ ጳውሎስ ጤናማ ቃል የሚናገር ጠፋ። ጤናማ ንግግርም ጠፋ። “በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።” — ሕዝቅኤል 34፥19።

መልዕክት አልባ ቆንጆ ዜማ

ብዙ ነገሮቻችን በላይ ከላይ ዕይታ ያማሩ ማር ቅብ የሆኑ ነገር ግን መልእክት የለሽ፣ ውሃ የማያነሱ፣ ሰማይ የማያውቀው እውቅና አልባ ነገሮቻችን ዛሬ ላሉት ትውልዶች አድንቆ ከመሄድ ውጭ ህይወት ላይ ጠብ የማይል፣ ከእግዚአብሔር የማያገናኝ እያጫወተ ዋናውን የሚያዘናጋ የጣፋጭ ቅኝቶች፣ የዘላቂ ዋስትና የማይሆኑ ብዙ ነገሮቻችን መዳሰስ፣ መታየት፣ መገምገም፣ ማስወገድ ተገቢ ነው።

በተለይ ዘመናችን ላይ እየተለቀቁ ያሉ አስተምሮቶች ከወንጌል እውነታ ውጪ የሆኑ አውድ አፈንጋጭ አስተሳሰቦች ቦታውን በመያዝ እውነትን ሰዎች እንዳይረዱ አዚም ያደረጉ፣ ክርስቶስ እንደተሰቀለ፣ እንደ ሞተ፣ ሞቶም እንደተነሳ፣ ኋላም እንደሚመጣ የማስተምሩ እንግዳ ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ቤት እየሞሉት እንዳሉ ይታያል። በተለይ በነገረ ድነት ላይ ያለን አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንድምታን አለመያዙ ግርታንና ግርግር ፈጥሮ ይታያል። “ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።” — ዕብራውያን 13፥9።

ከክርስቶስ ትምህርት ነጣይ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋናነት ወደ ምድር መምጣቱ ለምን እንደሆነ በውል ካለመረዳት፣ ካለማወቅ የተነሳ ዛሬ በምድራችን ላይ የሚሰበኩት፣ በትምህርትም መልክ የሚሰጡት ጨርሶውኑ ክርስቶሳዊ ትምህርቶች አይደሉም። የክርስቶስ ትምህርት ዓላማን የሳተና ያፈነገጠ ነው።

ምናልባትም የክርስቶስ ትምህርት ምንድን ነው ልንል እንችላለን፣ የክርስቶስን ትምህርት ለመረዳትና ለማወቅ የተራራውን ስብከት መመልከቱ ተገቢ ሲሆን በተጨማሪም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወቱን መመልከት ከበቂ በላይ ነው። (ማቴዎስ ወንጌል 5፣6፣7) መመልከት ይቻላል። “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥9።

ከክርስቶስ ነጣይ ትምህርት

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋናነት ወደ ምድር መምጣቱ ለምን እንደሆነ በውል ካለመረዳት፣ ካለማወቅ የተነሳ ዛሬ በምድራችን ላይ የሚሰበኩት፣ በትምህርትም መልክ የሚሰጡት ጨርሶውኑ ክርስቶሳዊ ትምህርቶች  አይደሉም። የክርስቶስ ትምህርት ዓላማን የሳተና ያፈነገጠ ነው።

 

ምናልባትም የክርስቶስ ትምህርት ምንድን ነው ልንል እንችላለን፣ የክርስቶስን ትምህርት ለመረዳትና ለማወቅ የተራራውን ስብከት መመልከቱ ተገቢ ሲሆን በተጨማሪም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወቱን መመልከት ከበቂ በላይ ነው። (ማቴዎስ ወንጌል 567) መመልከት ይቻላል።ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2 ዮሐንስ 19

 

ሐዋርያት ተለይተው የቆሙለትን አለማወቅ

ሐዋሪያት በትምህርታቸውም፣ በሕይወታቸውም አንድም ቀን በምድራዊ ነገር ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ እንጂ ምድር ነክ አሊያም ምድራዊ የሆነን ነገር በሚያስተምሩአቸው ዘንድ ነግረውም አስተምረውም አያውቁም። አጽንኦት ሰጥተው የሚያስተምሩትና የሚነግሩት ትልቁ ሥራቸው ኢየሱስን አሳይተው ከማለፍ ውጪ ሌላ አጀንዳ፣ መልእክት፣ ስብከት የላቸውም። ነቢያትም ቢሆኑ በሩቅ ይሁን በቅርብ ኢየሱስን አሳይተው፣ ነግረው፣ ተናግረው ነው ያለፉት። ሕዝብን ከምድር አላገናኙም፣ ባለፈና በሚያልፍ ነገር ላይ ሕዝብን አላስተማሩም፣ ኢየሱስን ግን በጊዜውም አለጊዜውም ተናግረው፣ ዘላለማዊውን ጉዳይ ብቻ፣ የሰማዩን ብቻ ተናግረው፣ ተርከው አልፈዋል። በእርግጥም በነቢያት እና በሐዋሪያት መሠረት ላይ መታነፃቸውን በትክክል በምቾትም ይሁን በመከራ ውስጥ ሰብከው አልፈዋል። በተለይ በምቾት ውስጥ ሆነው ከሰበኩት ይልቅ በመከራ ውስጥ ሆነው የሰበኩት በእጅጉ የተለየና የሚበልጥ ነበረ። “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” — ኤፌሶን 2፥20።

1- ጳውሎስና በርናባስ

ሀ- ወንጌልን

“እንዲህም አሉ፦ እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን።” — ሐዋርያት 14፥15።

ለ- ክርስቶስን

“እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥” — 1ኛ ቆሮንቶስ 1፥23።

ሐ- የምስራቹን

“እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤” — ሐዋርያት 13፥32።

የጳውሎስ አቋም

እርግጥ ነው ጳውሎስ የነበረበትን ሕይወትና ልምድ በሁላችን የታወቀ ነው። “እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።”— ፊልጵስዩስ 3፥4። “በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤” — ፊልጵስዩስ 3፥5። “ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።” — ፊልጵስዩስ 3፥6። “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።”— ፊልጵስዩስ 3፥7። “አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤” — ፊልጵስዩስ 3፥8-9።

ብልጽግና

ብዙውን ጊዜ የክርስትናን ሕይወት በምድራዊ ሐብትና ቁስ ስንለካው፣ ስንገምተውና፣ ስንተምነው እንገኛለን፣ በዚህም ጉዳይ አስተምህሮ አዘጋጅተን እንሰብካለን። እግዚአብሔር የእጆቻችንን ሥራ በእርግጥም ይባርካል ሆኖም ግን የመንፈሳዊነት በረከት መለኪያ ግን አይደለም፣ ጨርሶውንም ሊሆን አይችልም። መቁጠር ካለብን ካለብን ምንቆጥረው ይሄን የእግዚአብሔር ቃል ይዘን ብቻ ነው። ያላቸውን ትተው የተከተሉ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። "ሁሉን ትተን ተከተልንህ"፣ ሙሴ ከፈርኦን ቤት ትቶ መውጣቱን መዘንጋትም የለብንም፣ ጳውሎስ ሁሉን እንደ ጉድፍ ቆጥሮ ለወንጌል መኖሩን አንዘንጋ። “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” — ኤፌሶን 1፥3።

ጥንቃቄ በነዚህ ነገሮች አስተውሎት ይኑረን

1- መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለኝ ውጪ አይደለሁም

ስሁት ከሆኑ አስተምህሮዎች መካከል በተለይ "መንፈስ ነኝ/ነን) በሚል አስተምህሮዎቻቸው የምናውቃቸው ብዙዎች የመኖራቸውን ያህል ትንንሽ አምላኮች ነን የሚሉት ብቅ ማለታቸው ምን ያህል መንፈሳዊ ዝቅጠት ውስጥ መገኘታችንን ያሳየናል። መጽሐፍ ቅዱሳችን አፅንኦት ያልሰጠበትን ለመናገር አለመቸኮል መልካም ነው። ትኩረት በተሰጠው ላይ መገኘት ተገቢ ነው። “ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።” — ገላትያ 4፥7። “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።” — ዮሐንስ 15፥15።

2- መጽሐፍ ቅዱስ የነገረኝን እንጂ ሰው የነገረኝን አላምንም

በተለይ ጥቅም ተኮር፣ ንዋይን መሠረት ያደረገ፣ ቁሳዊ ከሆኑ፣ ክርስቶስን ከማያሳዩን እጅግ በጣም ፈቀቅ ልንላቸው ይገባል። ራስ ተኮር ከሆኑ፣ ክርስቶስ ተኮር ካልሆኑት መሸሹ ተገቢ ነው ። ምክንያቱም ዘላለማችንን ከሚነኩና ሊያሳጡ ከሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ መሸሹ በጣም ያዋጣል። “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።” — ገላትያ 1፥8። “አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” — ገላትያ 1፥9።

3- መጽሐፍ ቅዱስን መርህ ያላደረገ ትምህርት አልቀበልም

ዛሬ ዘመን ሰው በተለይ ክርስቲያን በምድራዊ ነገር እጅግ መባረክን ይሻል። መመኘቱ መልካም ነው፣ አይከፋም። ባራኪውንና መባረኪያውን ግን ወደ ጎን ማድረጉ ግን ተገቢ አይደለም። ይህ ነገር እይታችንን ከዘላለማዊ አጀንዳችን ላይ ያነሳል፣ ሸውራራ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ነው። በተለይ ብድራታችንን ትኩር ብለን እንዳናይ፣ የክርስትና ጉዞአችንም ላይ እንቅፋት እና ሳንካን ይፈጥርብናል። “አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ።” — ዘጸአት 23፥25።

4- በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርት ላይ የማያተኩረውን አስተምህሮ አልቀበልም

ክርስቶስ ትልቁ አላማው ከእግዚአብሔር ጋር የለንን የተቋረጠውን ህብረትና አንድነት ማስኬድና ህይወት ሊሆንልንና ሊበዛልን፣ በዘላለም ከጀንዳ ላይ ተካትተን፣ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት መባረካችንን ለማሳየትና እንድንይዘው፣ ይህም ትልቁ በረከታችን አንድ ብለንም የምንቆጥረው ነው። “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥9። “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤”— 2ኛ ዮሐንስ 1፥10።

                        በመጨረሻም

ሀ- ከአለማዊነት መራቅ

“ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤” — 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥20።

ለ- ለመንፈሳዊ ጤንነት ጤናማ ቃል መያዝ

“በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥13።

ሐ- አደራን መጠበቅ

“መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥14።

መ- በተማሩት መኖር

“አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14።

ሠ- ቅዱሳን መጻሕፍትን ማወቅ

“ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥15።

ቸር ይሁን

ወንድም በረከት ሱላሞ ሱጌቦ