እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ የልቡ የጥልቅ ሃሳብ የፈጠረው  የሰው ልጅ ደህንነት ነው። ሰው በተለይ ለነፍሱ ደህንነት፣ መኖር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔር አሳልፎ ሰጥቶአል፣ ወደ ምድርም ክብሩን ትቶ የአባቱን ትዕዛዝ ሊፈፅም መጥቶአል። እግዚአብሔር የፈጠረው የሰው ልጅ እንዲጠፋበት አይፈልግም፣ ይልቁንም የሰውን ልጅ በአድራሻው ያለበት ድረስ መጥቶ በስም ጠርቶ ይፈልገዋል። "አዳም ሆይ ወዴት ነህ" ብሎ መምጣቱ እግዚአብሔር ምን ያህል የፍቅር አምላክ መሆኑን አስረጂ ነው። በተለይ በዚህ አለም፣ በምድር ላይ ያለን አገልጋዮች ለምንመራቸው የእግዚአብሔር ህዝቦች የዚህን ያህል ልብ ከሌለን የወንጌልን እና የትውልድን አደራ እየተወጣን አለመሆኑ ልብ ልንለው የሚገባ አቢይ ጉዳይ ነው። 

በተለይ ከቀደሙት አባቶች በውል ልንማረውና፣ ልንረዳው ይልቁኑ በህይወታችን እና በቤተክርስቲያን ልንተገብረው የሚገባ ጉዳይ ቢሆን እና ቢኖር ለወንጌልና ለትውልድ ያላቸው የፀና አቋም ነው። ከራሳቸው በላይ ለወንጌል እና ለትውልድ ያላቸው የማይናጋ እና የማይናወጥ ሙሉ ሃሳባቸው እና ማንነታቸው፣ ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለእግዚአብሔር ህዝብ ያላቸው የፀና እምነት በተለይ ከራስ ምቾት ርቆ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መከራ ለመቀበል መወሰኑ የሙሴ ትልቅ አብነትና ምሳሌያችን ነው። 

"ለወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ" ማለት በህይወት ላይ ይህን የመሰለ ውሳኔ የለም፣ "የማይጠፋን አክሊልን" ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያሸልም የቆራጥ አገልጋይ አቋም ነው። 

የቀደሙ አባቶች ከእግዚአብሔር የተቀበሉት አደራ በተለይ ለእግዚአብሔር ህግ እና ለትውልድ ያላቸው አደራ በጣም የሚገርም እና ለእግዚአብሔር ጉዳይ ያላቸው የፀና አቋም ዛሬ ላይ ላለን የእግዚአብሔርን መንግስት እያገለገልን ላለን ትልቅ ትምህርትና የራሳችንንም አቋም ልናይበትና ልንፈትሽበት፣ ማስተካከል የሚገባን ነገር ቢኖር እንኳን ትልቅ ትምህርት ሰጥቶን ያልፋል።

የቀደሙት የእምነት አባቶች በእግዚአብሔር፣  በእግዚአብሔር ህዝብና በእግዚአብሔር ህግ (ወንጌል) ላይ ያላቸውን አገልግሎት ስንመለከት፣ ዛሬ በድኀሰረ ስልጣኔ ዘመን ላለን ዘመነኞች አንድ አብይና አንኳር ነገር ጥሎልን ስለሚያልፍ ለትምህርት መመልከቱ ተገቢ ነው።

ባለ አደራነት ምን ማለት ነው?

ባለ አደራነት ማለት ለአንድ የተወሰነ ጉዳይ፣ ክንውን ወይም ግዴታ ለአንድ ግለሰብ ኃላፊነት ወይም ስልጣን መስጠት ማለት ነው። አንድ ግለሰብ አንድን ነገር ለሌላ ሰው ሲሰጥ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት በታማኝነት እና በኃላፊነት እንዲወጣ በእሱ ላይ እምነት በመጣል እና በመስጠት ጉዳዩን መጣል ነው። 

አደራ መስጠት በበላይነት፣ የውሳኔ ሰጪነት ስልጣን መስጠትን፣ ምስጢራዊ መረጃን መጋራትን ወይም ጠቃሚ ጉዳዮችን መጠበቅና ማቆየትን ሊያካትት ይችላል። 

የአደራ አብይ ጉዳይ በአደራ፣ በመተማመን የተሰጠው ሰው ማንነት ላይ በመተማመን እና በማመን ላይ የተመሠረተ ነው።

ብሉይ ኪዳን

ሙሴ ለኢያሱና ለካሌብ የሰጠው ትዕዛዝ 

እግዚአብሔር አስቀድሞ ሙሴን በኮሬብ ተራራ ተገልጦለት የነገረው ትዕዛዝ በተለይ ሕዝቡ እንዴት እና በምን አይነት መንገድ መሄድ እንዳለባቸው ለሙሴ በግልፅ ሲነግረው በዘዳግም 29:9 በውል እንመለከታለን። ለሕዝቡ ይከናወንላቸው ዘንድ መከናወኛውን እርሱም የቃል ኪዳኑ ቃሎች ይጠበቁ ዘንድ እና ያደረጉም ዘንድ ነገረው። ይህንኑ ትዕዛዝ በኢያሱ 1:7-8 ያለውን ቃል እግዚአብሔር መልሶ ኢያሱን ሙሴ ያዘዘህን በማለት የአደራን መቀበል ያስታውሰዋል። ይህንኑ ቃል በአደራነት ኢያሱም ለእስራኤል ቤት ሲናገር እንመለከታለን።

ኢያሱ የእስራኤል ሽማግሌዎችን

በተለይ ኢያሱ ከሙሴ መሞት በኋላ የእስራኤልን ህዝብ ሊመራ ከሙሴ በአደራ የተቀበለ ተተኪ አገልጋይ ነው። ካሌብም አብሮት የተቀበለ መሆኑ አይዘነጋም። የመከናወንና የስኬት መንገዱ ያለው በእግዚአብሔር ህግ ውስጥ እንደሆነ ሙሴ አበክሮ የነገረው ሲሆን ይህንንም እንዲያስቀጥል እግዚአብሔር ሙሴ የነገረውን ኢያሱን አስታወሰው። ኢያሱ 1:7-8 መመልከት ይቻላል።

ኢያሱም እንዲሁ በሽምግልናው በተለይ በመሞቻው ጊዜ የእስራኤልን ሽማግሌዎች እና ነገዶች በመሰብሰብ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከእግዚአብሔር እና ሲመራቸው ከነበረው ሙሴ በአደራ የተቀበላቸውን ህዝቦች ስኬት እና መከናወን እንዲሆንላቸው ከእግዚአብሔር ህግ ፈቀቅ እንዳይሉ የእግዚአብሔርን ህግ በአደራ እንደ ተቀበለ በአደራ ሲሰጣቸው በኢያሱ 23:1-6 መመልከት እንችላለን። 

ዳዊት ልጁን ሰለሞንን

ዳዊት ከልጅነት እግዚአብሔር በብዙ የህይወት ጉዳና ውስጥ ያሳለፈው፣ እግዚአብሔር በምድረበዳ በእረኝነት ህይወቱ ብዙ ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ሃይልና እርዳታ የኖረ፣ የመሪነትን እና የጦረኝነትን ህይወት፣ የእረኝነትን ህይወት እግዚአብሔር ያሰለጠነው ትልቅ የእግዚአብሔር ልብ ያለው ጀግና ንጉስ ነው። በተለይ በመዝሙር 119 ላይ የፃፋቸው በእግዚአብሔር ህግ ላይ በዚህ በተጠቀሰው መዝሙሩ ላይ እውቀቱን መረዳት እንችላለን። ምን ያህል ሕጉን ይዘን ስንኖር መከናወን እንዳለ ቁልጭ አድር ጎ ያሳየናል። ለዚህ ነው በተለይ የዳዊት የህይወቱ ማብቂያ ላይ ከመሞቱ አስቀድሞ ምን ማድረግ እንዳለበት በእግሩ በተተካው ልጁን ሰለሞንን በብርቱ ሲመክረው የምናየው። 1ኛ ነገሥት 2:3 ላይ ሰለሞን ምን ማድረግ እንደሚገባው የህይወት ዘመን ምክርን ዳዊት አባቱ በአደራ ሲመክረውና አስረግጦ ሲነግረው በዚህ ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን። 

በዚህ ትምህርት ምን ያህል ዳዊት ለእግዚአብሔር ህግ እና ለትውልድ አደራነት እንደሚጨነቅ መመልከት እንችላለን። አደራነት ለቀጣይ ለእግዚአብሔር ህግና ለትውልድ ማሰብ መቻል ማለት ነው።

አዲስ ኪዳን

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ የሰጠው አደራ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ከመሄዱ አስቀድሞ ለጴጥሮስ የነገረው የአደራ መልዕክት እንደነበረ ሁላችን የማንዘነጋው ብርቱ ጉዳይ ነው። ይህንንም አደራ እንደምስክር የተመለከተው ዮሐንስ በመልዕክቱ በጥንቃቄ ሰድሮ ዛሬ ላይ ላለን አገልጋዮች ፅፎልናል።

 አደራ አደራን በሰጠው በሰጪው ልክ ተረድተን እና ተገንዝበን የምንቀበለው ብርቱ መልዕክት እና ትዕዛዝ ነው። በተለይ በዮሐንስ 21:15-17 ያለው መልእክት ለእኛም በዚህ ዘመን ላለነው አገልጋዮች አደራ ምን ያህል ከባድ የሆነ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት መሆኑን መረዳትና ማወቅ እንዳለብን በአፅንኦት ያሳየናል።

ጌታ ኢዩበዘኑ ሁሉ ምን ያህል ለትውልድ እንደሚጨነቅ ማየት የምንችለው ብርቱ እና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ለቀጣይነቱ በትውልድ ላይ ምን ያህል መሠራት እንዳለበት አስረግጦ ይነግረናል። "ህፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው" ማለቱ ለትውልድ ምን ያህል አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚናገር ማወቅ ይቻላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ 

ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥18።

በመጨረሻም፦

ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። 1ኛ ተሰሎንቄ 2፥4።