የመጽሐፈ አስቴር

መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ባለፉት 20 ዓመታት ስለ ተፈጸመው የኢትዮጵያ ታሪክ አስብ። መንግሥትን፥ ቤተ ክርስቲያንንና የግል ሕይወትህን በመቆጣጠር ረገድ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እንዴት አየህ? ምሳሌዎችን ስጥ።

መጽሐፈ አስቴር እግዚአብሔር በማይታይ መንገድ በሉዓላዊነቱ ሕዝቡን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔር እጅ በሥራ ላይ ሆኖ ባያዩም እንኳ እግዚአብሔር በብዙ በማይታዩ መንገዶች ለራሳቸው ጥቅምና ለመንግሥቱ መስፋፋት በመሥራት ላይ ነው። ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንደ ዕድል የሚያየውን ነገር እኛ ክርስቲያኖች ዕድል እንዳይደለ እናውቃለን። ይልቁንም እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችንም ሆነ እጅግ ጥቃቅን የምንላቸውን ድርጊቶች ሁሉ ፈቃዱን ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል።

መጽሐፈ አስቴር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልዩ መጻሕፍት ከምንላቸው አንዱ ነው። ምሁራን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥሩ ከሚባሉ ሥነ ጽሑፎች አንዱ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ወይም በማንኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ተመሳሳይ የሆነ ሥነ-ጽሑፍ አለመገኘቱ በጣም ያልተለመደ ነገር ነው። መጽሐፈ አስቴር እጅግ አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢሆንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን እንደተካተተ ምሁራን ብዙ ጊዜ በመደነቅ ይጠይቃሉ። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ የእግዚአብሔር ስምም ሆነ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ ወዘተ ጨርሶ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ መጽሐፉን ለማይረዱት ሰዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ አይታያቸውም። ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጽሐፉ ስለ ሌሉች ዓለማዊ ታሪኮች የሚጠቅሰው አንዳችም ነገር ስለሌለ የታሪኩን እውነተኛነት ይጠራጠራሉ። ስለሆነም ይህ ነገር አጭር ልብ ወለድ ወይም ሰዎችን ለማስተማር የተሰጠ ምሳሌ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን መጽሐፈ አስቴርን ከማንበብ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው ታሪኩን በእውነተኛነቱ እንደተመለከተው ነው (ለምሳሌ፣ አስቴር 102)

የመጽሐፈ አስቴር ርእስ

መጽሐፈ አስቴር ከዋና ዋናዎቹ ባሕርያት አንዷ በሆነችው በአስቴር ስም የተሰየመ ነው። አስቴር አባትና እናቷ የሞቱባት በኋላም የፋርስ ንግሥት የሆነችና የአይሁድን ሕዝብ ሁሉ ያዳነች ሴት ናት። ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሴቶች ስም ተሰይመዋል፤ አንደኛው መጽሐፈ ሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፈ አስቴር ነው። መጽሐፈ አስቴር ወደ ግሪክ ቋንቋ በተተረጎመበት ጊዜ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ያክሉበት ጀመር። እነዚህ ታሪኮች መርዶክዮስ ስላየው ሕልም፣ መርዶክዮስ ለአርጤክስስ ስለጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎችና አስቴርና መርዶክዮስ ስላደረጉዋቸው የተለያዩ ጸሎቶች የሚናገሩ ናቸው። እነዚህ ታሪኮች በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የታከሉ ቢሆኑም፥ በመጀመሪያው መጽሐፈ አስቴር ውስጥ ያልነበሩ ታሪኮች ወይም ጥቅሶች ናቸው።

የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ

መጽሐፈ አስቴርን ማን እንደጻፈው መጽሐፉ ራሱ የሚናገረው ነገር የለም። በአይሁድ አፈ ታሪክ መሠረት መጽሐፈ አስቴር የተጻፈው በመርዶክዮስ ነው ቢባልም ይህን በሚመለከት አንዳችም መረጃ የለንም፡፡ ሆኖም መጽሐፉን በምናጠናበት ጊዜ በግልጥ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው አንድ አይሁዳዊ፥ የተማረና የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ያለው፥ የፋርስ ቤተ መንግሥትን መዛግብትና የቤተ መንግሥት ባህልንም ሊያገኝ የሚችል ሰው እንደ ነበረ ነው (አስቴር 102) እንዲሁም ጸሐፊው በአስቴርና በመርዶክዮስ መካከል የተደረጉትን ውይይቶች ያውቅ ነበር። መርዶክዮስ እነዚህን ሁሉ መመዘኛዎች ስለሚያሟላ መጽሐፉን እርሱ ጽፎት ሊሆን ይችላል።

መጽሐፈ አስቴር የተጻፈበት ጊዜ

ጸሐፊው ማን እንደሆነ ስለማይታወቅ፣ መቼ እንደተጻፈ አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር 200 .. በፊት መጻፉን ነው። መጽሐፉ 400-350 .. ባለው ጊዜ ሳይጻፍ አልቀረም። ከዚያ በኋላ የፉሪም በዓል የአይሁድ ብሔራዊ በዓል ሆነ።

የመጽሐፉ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ አጋማሽ ላይ ነው። የተፈጸመውም በዕዝራ 6 በዕዝራ 7 መካከል ነው። እንደ መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በይሁዳ ሳይሆን በፋርስ ምድር ነው። እግዚአብሔር በሥራ ላይ የነበረው በይሁዳ ብቻ ሳይሆን፥ በምርኮ በነበሩ አይሁድ መካከልም ነበር።

የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ ንጉሥ የነበረው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ አሕሻዊሮስ በመባል የሚታወቀው ቀዳማዊ አርጤክስስ ነበር። የዚህ ሰው አባት ታላቅ ጦረኛ የነበረውና የፋርስን መንግሥት ክልል በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ያስፋፋው ታላቁ ዳርዮስ ነበር።

አርጤክስስ አዳዲስ ምድርን በወረራ ከመያዝ ይልቅ፥ ትኩረቱ ዋና ከተማ የነበረችውን ሱሳንና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞችን በመሥራት ላይ ነበር። አማካሪዎቹ ግን ግዛቱን እስከ አውሮጳ ድረስ ለማስፋፋት ይችል ዘንድ ግሪክን እንዲወጋ መከሩት፤ ነገር ግን በዚህ ጦርነት አልተሳካለትም። ግሪኮች በጦርነቱ አሸነፉትና አብዛኛውን ጦሩንና የባሕር ኃይሉን ደመሰሱበት።

የዓለም ታሪክ ስለ አርጤክስስ የሚናገረው በርካታ ነገር ቢኖርም አስቴርን ግን የሚጠቅስ ታሪክ የለም። አስጢን የምትባል አንዲት ሚስት እንደ ነበረችውና በኋላም እርሷን በማስወገድ አስቴርን በንግሥትነት እንዳገባ የሚናገር ታሪክም የለም። የዓለም ታሪክ የሚናገረው አሚስቲሪስ ስለተባለች አንዲት ንግሥት ብቻ ነው። ይህ ስም የአስጢን ወይም የአስቴር ሌላ ስም እንደሆነም የምናውቀው ነገር የለም።

የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው ንጉሡ አርጤክስስ ከግሪኮች ጋር ለመዋጋት ወደ ጦር ሜዳ ከመሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ምሁራን የግብዣው ዓላማ በግሪክ ላይ ስለሚደረገው ወረራ ለመነጋገር ነበር ብለው ያስባሉ። አስጢን እንደተወገደች አስቴር ወዲያውኑ ንግሥት ያልሆነችበት ምክንያትም ይህ ሊሆን ይችላል። አስጢን የተወገደችው አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ሲሆን፥ አስቴር ንግሥት የሆነችው ደግሞ 7ኛው ዓመት ነው። በመካከሉ 4 ዓመታት ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህም ማለት የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው 483-471 .. ነበር ማለት ነው።

የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች እና አስተዋጽኦ

የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች

1. መጽሐፈ አስቴር የእግዚአብሔርን ታላቅነትና በዓለም ሕዝብ ሁሉ ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለአይሁድ ለማስተማር የተጻፈ ታሪክ ነው። ጸሐፊው አይሁድን ለማስተማር የፈለገው ነገር፥ ሕዝቡ የሚኖሩት በተስፋይቱ ምድር ሳይሆን በምርኮ ምድር ቢሆንም እንኳ፥ እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ አሁንም ቢሆን ታማኝ መሆኑን ነው፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለማስተማር ጸሐፊው የተጠቀመው የመጽሐፍ ቅዱስን የተለመደ መንገድ አይደለም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ በአጠቃላይ ግልጽ ተአምራትን በማድረግ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያስተማራቸውን እውነቶች እናያለን። እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን የተሻገሩበትንና ፈረዖን ከነሠራዊቱ የሰጠመበትን፥ ሕዝቅያስ ባደረገው ጦርነት እግዚአብሔር 180000 የአሦር ወታደሮችን የደመሰሰበትን ታሪክ እናነባለን። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለማመልከት ጸሓፊው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ስልት ሲጠቀም እናያለን። ጸሐፊው ሆን ብሎ የእግዚአብሔርን ስም አልጠቀሰም። ይልቁንም እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከጥፋት ለማዳን በጣም ጥቃቅንና ኢምንት ናቸው የሚባሉ ድርጊቶችን እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው በተደጋጋሚ ትኩረት ሰጥቶት እናያለን።

ለምሳሌ፡- አስቴር ንግሥት ሆና ለመመረጥና ሕዝቧን ከጥፋት ለማዳን ቻለች። መርዶክዮስ እንደአጋጣሚ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ ለመስማትና ንጉሡን ለማስጠንቀቅ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሰ። ንጉሡ አንድ ለሊት እንቅልፍ ርቆት ስለ መርዶክዮስ እንዲያነብብና የሚያሸልመው ድርጊት እንዲጋለጥ ሆኖ መርዶክዮስ ተሸለመ። አንድ የማያምን ሰው ይህንን ተመልክቶ አይሁድ ከጥፋት ለመዳን ዕድለኞች ሆኑ ቢልም፥ እንደ ጸሐፊው አስተሳሰብ ዕድል የሚባል ነገር የለም። ይልቁንም እግዚአብሔር ጥቃቅን ድርጊቶችን እንኳ በመቆጣጠር ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም ይጠቀምበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ሰዎች የሆኑት በዕድል ነው ብለው የሚያስቧቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ) እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙት በዕድል እንደሆነ የሚያስቡ ክርስቲያኖች አሉን? አብራራ። ) ለዓለም ዕድል ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚመለከቱአቸው እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር አሠራር በማያምኑ ሰዎች ወይም በሥጋዊ ክርስቲያኖች ዘንድ የማይታዩና ለመረዳት የሚያስቸግሩ ቢሆኑም እንኳ በክርስቲያኖች ዘንድ ግን ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡ ናቸው። ለእኛ በሚያደርገው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን እጅ በመሥራት ላይ መሆኑን ማየት መቻል አለብን። የብሉይ ኪዳን ተአምራት በማይፈጸሙበት ጊዜና አይሁድ በዓለም ሁሉ ተሠራጭተው በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር የጥንቱን ዓይነት ተአምራት ባይሠራም አይሁዳውያንን ግን አሁንም እንደደገፋቸው ነበር። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማድረግ ሕዝቡን ይጠብቅ ነበር (ለምሳሌ፡- ዘካ. 12) እግዚአብሔር የክፉዎችን ዕቅድ ፍሬ ቢስ ለማድረግ ይሠራ ነበር (መዝ. (140) መጽሐፈ ምሳሌ 1024-25 አንብብ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአሁኑ ዘመን ክርስቲያኖችስ ይህንን እውነት መረዳት ያለባቸው ለምንድን ነው?

2. አይሁድ ፉሪም የሚባል ዓመታዊ በዓል ነበራቸው። ይህ ቀን ለአይሁድ እጅግ ከተወደዱ በዓላት አንዱ ሆነ። መጽሐፈ አስቴርን በማንበብ፥ በመብላትና በመጠጣት፥ ደግሞም ስጦታን በመለዋወጥ ያከብሩታል። የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ ለአይሁድ የፉሪምን በዓል አጀማመር ለመግለጥ ፈልጓል።

3. እኛ በቀላሉ የምንገነዘበው ባይሆንም፥ ጸሐፊው በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል ስለሚደረገው የማያቋርጥ ጦርነት መናገሩ እንደሆነ አይሁድ ይገነዘቡት ነበር። ከብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ጠላቶቻቸው አማሌቃውያን ነበሩ (ዘጸ. 178-16 ተመልከት) ስለዚህ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸው አይሁድን አዘዘ፤ (ዘዳ. 2517-19) አይሁድ ግን ይህንን በማድረግ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፥ በብሉይ ኪዳን ታሪክ በአጠቃላይ በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል የተደረገውን የማያቋርጥ ጦርነት እንመለከታለን (ለምሳሌ. 1 ሳሙ. 15 1 ዜና 443) በእስራኤላውያን አእምሮ አማሌቃውያን እነርሱንና እግዚአብሔርን ለሚቃወሙ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ሁሉ ተምሳሌት ናቸው። ሐማ ከአማሌቃውያን ወገን እንደመጣ ተገልጦአል (መጽሐፈ አስቴር 31-6 95-10) የሐማ ዕቅድ እንደ ከሸፈና እርሱም እንደተደመሰሰ በማሳየት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ሁሉ አንድ ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚጠፉ ጸሐፊው አስተምሮአል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ዛሬ እኛን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

የመጽሐፈ አስቴር አስተዋጽኦ

  1. አስጢን ከንግሥትነትዋ ተሻረች (1)
  2. አስቴር ንግሥት ሆነች (21-18)
  3. መርዶክዮስ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ አጋለጠ (219-23)
  4. ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ያወጣው ዕቅድ (3)
  5. መርዶክዮስ የአይሁድን ሕዝብ እንድትረዳ አስቴርን አሳመናት (4)
  6. የአስቴር የመጀመሪያ ግብዣ (51-8)
  7. መርዶክዮስ ተሸለመ (59-614)
  8. የአስቴር ሁለተኛ ግብዣና የሐማ መሰቀል (7)
  9. የአይሁድ ሕዝብ ሕይወት መትረፍና የመርዶክዮስ መሾም (8-10)

5 ጥያቄ፥ ስለ አስቴር ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ፤ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችንም ዘርዝር።

አስቴር 1-6

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም የሚሠራው እንዴት ነው? ብዙ ጊዜ ቀይ ባሕርን እንደመክፈል ያሉ ታላላቅ ተአምራትን ይሠራልን? ብዙ ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ይህንን የመሳሰሉ ታላላቅ ተአምራትን እንዲሠራ እንፈልጋለን። በመሆኑም በልሳን መናገርና ፈውስን ወደ መሳሰሉ አስደናቂ ተግባራት እንሳባለን። አዎን እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን በመካከላችን በታላላቅ መንገዶች ይሠራል፤ ነገር ግን ለአስደናቂ ነገሮች ብቻ ትኩረት በመስጠታችን፥ እግዚአብሒር በተለመዱ ጥቃቅን ነገሮችም ውስጥ እንደሚሠራ እንዘነጋለን። እግዚአብሔር የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውሳኔ በመቆጣጠር ይሠራል። እግዚአብሔር ለወንጌል ሥራ ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጡ በሚችሉበት ትክክለኛ ስፍራ ልጆቹን በማስቀመጥ ይሠራል። እግዚአብሔር ልናስባቸው በማንችል በሕይወታችን በሚፈጸሙ ጥቃቅን ነገሮች ውስጥ እንኳ ሲሠራ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፥ በየቀኑ ሊጎበኙን የሚመጡ ሰዎችን የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። በመንገድም ሆነ በቢሮ የሚመጡትንና የሚገናኙንን ሰዎች የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በአስደናቂ ነገሮች ላይ ብቻ የምናተኩር መሆን የለብንም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በሚያደርጋቸው ዕለታዊ የተለመዱ ነገሮችም ላይ ማተኮር ያስፈልገናል። በሕይወታችን የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሔር መሪነት የሚከናወኑ ናቸው። እነዚህ ለእኛ በጣም ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ልናስተውላቸው እስከማንችል ድረስ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥

  1. ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩባቸውን የእግዚአብሔርን ኃይል የሚያሳዩ አስደናቂ ሁኔታዎች የሚገልጹ ነገሮችን ዘርዝር
  2. እግዚአብሔር በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች የማይገነዘቡአቸውን ተራና የተለምዶ የሚመስሉ ነገሮችን ዘርዝር።
  3. ተአምራታዊ ከሆኑ መንገዶች ይልቅ በእነዚህ የተለመዱ ነገሮች ላይ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ሌሎች የበለጠ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ልብ ልትላቸው የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

የውይይት ጥያቄ፥ አስቴር 1-6 አንብብ።

  1. በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተገለጹትን ዋና ዋና ድርጊቶች ዘርዝር።
  2. ለአይሁድ ሕዝብ ጥቅም ሲል እግዚአብሔር እንዴት በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ጥቃቅን ነገሮችን ዘርዝር።

አስቴር 1-6 የአስቴርን ታሪክ የተለያዩ ደረጃዎች ያሳያል። በፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተፈጸሙ ጨርሶ የማይገናኙ የሚመስሉ ነገሮችን ይዟል። እነዚህ ታሪኮች ሲነገሩንም ለዋናው ታሪክ ያላቸው አስፈላጊነት አልተጠቀሰም። ለታሪኩ መሠረት የሆነው ዋናው ነገር በሓማ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤላዊያን ጠላትና በአስቴርና በመርዶክዮስ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ያለውን ትግል ነው። ቀጥሎ ይህንን ትግልና በባዕድ ምድር ሕዝቡን ለመታደግ በመሥራት ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን እጅ የሚያሳዩትን ነገሮች አስተውል።

1. ንግሥት አስጢን: ከንግሥትነት ሥልጣንዋ ተወግዳ አንዲት የማትታወቅ አስቴር የተባለች ሴት የምትቀጥለዋ የፋርስ ንግሥት ሆና ተመረጠች። ይህ በጣም አስፈላጊ የነበረው በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግና የአይሁድን ሕዝብ ከጠቅላላ ጥፋት ለማዳን የቻለች ንግሥት አስቴር ስለነበረች ነው። እግዚአብሔር በአንድ የአሕዛብ ግብዣ ተጠቅሞ አንዲት ንግሥት እንድትወገድና ሕዝቧን ለማዳን እንድትችል አስቴር ንግሥት እንድትሆን አደረገ።

2. የአስቴር አጎት: የነበረው መርዶክዮስ ንጉሡን ለመግደል የተደረገውን ሴራ ሰማና ይህንን ለንጉሡ ነገረ። መርዶክዮስ ይህን ሴራ በማክሸፉ ረገድ ያበረከተው በቤተ መንግሥቱ መዛግብት ውስጥ ተጻፈ። ይህ መረጃ የአይሁድ ሕዝብ ጠላት የነበረው ሐማ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር በተገደደበት ጊዜ አስፈላጊ ሆነ። የንጉሡ የግል አማካሪ የነበረውን የሐማ ስፍራ የወሰደም መርዶክዮስ ነበር። በዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ እናያለን። እግዚአብሔር ንጉሡ እንዳይገደል አደረገ፤ ቢገደልም ኖሮ አስቴር በአዲሱ ንጉሥ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ አትችልም ነበር። እግዚአብሔር ሴራውን ሊያከሽፍ በሚችልበት ትክክለኛ ስፍራ ላይ መርዶክዮስን አስቀመጠው። በኋላም የመርዶክዮስን ሥራ እግዚአብሔር ለንጉሥ አስታወሰና በፋርስ መንግሥት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ስፍራ በማስቀመጥ እንዲያከብረው አደረገ።

3. አጋጋዊው ሐማ: ያለ ምንም ምክንያት የጠላቸውን የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ሴራ አሴረ። እንደምታስታውሰው፥ አጋግ ከአማሌቃውያን ነገሥታት አንዱ ነበር (1 ሳሙ. 1520) ስለዚህ ሐማም አማሌቃዊ መሆኑን መገመት ትክክል ነው። ሐማ በምድሪቱ ያሉትን አይሁድ በሙሉ ለማጥፋት ከአርጤክስስ ፈቃድ አገኘ።

4. መርዶክዮስ አይሁድን: ለማዳን የምትችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባት አስቴርን አሳመናት፡ አስቴር 414 በመጽሐፉ ውስጥ ያለ ቁልፍ ጥቅስ ነው። ስለ ሕይወቷ ለፈራችው ለአስቴር መርዶክዮስ እንዲህ አላት፡- «አንቺ፡- በንጉሥ ቤት ሰለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃልበዚህ ንግግር ውስጥ ሁለት እውነቶችን እናያለን። የመጀመሪያው፥ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ያደረገው እግዚአብሔር የአይሁድ ሕዝብ እንዳሉ እንዲጠፉ እንደማይፈቅድ መርዶክዮስ ያውቅ እንደ ነበር ነው። ብዙ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ፥ እግዚአብሔር አይሁድን ሙሉ ለሙሉ ከመጥፋት ሁልጊዜ ይጠብቃቸዋል።

ሁለተኛው ነገር እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም ግለሰቦችን በልዩ የኃላፊነት ስፍራ በማስቀመጥ እንደሚጠቀምባቸው መርዶክዮስ ተገንዝቦ ነበር። መርዶክዮስ አስቴር ንግሥት የሆነችው በዕድል እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። አስቴርን የፋርስ ንግሥት በማድረግ አይሁድን ለማዳን ሊጠቀምባት የወደደው እግዚአብሔር እንደሆነ መረዳት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ጠቃሚ የሆኑ ክርስቲያኖችን ትክክለኛ በሆነ የአመራር ስፍራ በማስቀመጥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንዴት እንደተጠቀመባቸው የሚያሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ተመሳሳይ ሁኔታ ስጥ።

5. አስቴር ወደ ንጉሡ በመሄድ: ወደ አዘጋጀችው ግብዣ እንዲመጣ ጠየቀችው። በፋርስ ባሕል ማንም ሰው ንግሥቲቱም ብትሆን እንኳ ያለ ንጉሡ ጥሪ እርሱ ወዳለበት መግባት አይችልም ነበር። አስቴር ወደ ንጉሡ በመግባቷ በትረ መንግሥቱን የምታመለክተውን በትር ወደ እርሷ ካልዘረጋላት ሕይወቷን እንኳ ልታጣ እንደምትችል ታውቅ ነበር፤ ነገር ግን የእርሷ ሕይወት ከወገኖች ሁሉ ሕይወት እንደማይበልጥ ተገነዘበች። ስለዚህ በፈቃዴ ወደ ንጉሡ ገባች። ይህንን ከማድረጓ በፊት ግን እግዚአብሔር በሥራዋ የተዋጣለት ያደርጋት ዘንድ አይሁድ ሁሉ እንዲጾሙና እንዲጸልዩ ጠይቃ ነበር። አስቴር፥ በንጉሡ ፊት ሞገስ እንድታገኝ ሊያደርግ የሚችል እግዚአብሔር እንደሆነ ታውቅ ነበር! ስለዚህ አይሁድ ሁሉ እንዲጸልዩላት ጠየቀች። እግዚአብሔር ጸሎቷን አከበረ። እንዲሁም በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ የነበራትን እምነት ሕይወቷን እንኳ ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆኗን በንጉሡ ፊት ሞገስ በመስጠት አከበረላት።

6. ለእርሱ ክብር ለመስጠት: መርዶክዮስ ባለመስገዱ ሐማ ተቆጣ። ስለዚህ ለመርዶክዮስ የመስቀያ ግንድ አዘጋጀ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን ለመስቀል ከንጉሥ ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት፥ እግዚአብሔር ለንጉሡ እንቅልፍ በመከልከል መርዶክዮስ ሕይወቱን ማዳኑን እንዲያስታውስ አደረገው። በዚያን ጊዜ ሐማ፥ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር ተገደደ፤ ስለዚህ ጸሐፊው የማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቢጠሉም እንኳ አንድ ቀን ሊያከብሯቸው እንደሚገደዱ ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ፊልጵ. 29-11 አንብብ። የኢየሱስ ጠላቶች አንድ ቀን እርሱን እንዲያከብሩት የሚገደዱት እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፥

  1. ከዚህ የመጽሐፈ አስቴር ክፍል የምንማራቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር።
  2. እነዚህ እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች በሚመለከት ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አስቴር 7-12

የውይይት ጥያቄ፡ ምሳሌ 211 አንብብ።

  1. እግዚአብሔር በምድር መሪዎች ላይ ስላለው ቁጥጥር ይህ ጥቅስ ምን ያስተምረናል?
  2. ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር በሚሠሩበት ጊዜ ይህ ነገር እንዴት ማበረታቻ ይሆናቸዋል?
  3. ይህ ነገር ሲፈጸም እንዴት እንዳየህ ምሳሌዎችን ስጥ።

እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ብሎ ሁልጊዜ የሚሠራ መሆኑን አይተናል። ተአምራትን ባናይም እንኳ እግዚአብሔር በሥራ ላይ አይደለም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ የሚሠራው ሕዝቡ እንኳ በማያውቁት መንገድ ነው። ክርስቲያኖች ግን ዕድል ወይም አጋጣሚ የሚባል ነገር እንደሌለ መገንዘብ አለባቸው። ይልቁንም ጸጋን የተሞላው ሰማያዊ አባታችን ለክብሩ፥ ለመንግሥቱና ለሕዝቡ ሲል ነገሮችን ሁሉ እየተቆጣጠረ ይሠራል።

መጽሐፈ አስቴር፥ እግዚአብሔር በአስቴር ዘመን ይህንን ለአይሁድ እንዴት እንዳደረገላቸው የሚገልጥ ሥዕላዊ ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ጠላቶች፥ የእርሱን ሕዝብ አይሁድን ለማጥፋት ቢወስኑም እንኳ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን በአንዲት ሴት በመጠቀም በጸጥታ ሠራ።

የውይይት ጥያቄ፥ አስቴር 7-12 አንብብ።

  1. አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት ያዳነችው እንዴት ነው?
  2. በዚህኛው የአስቴር ታሪክ ክፍል የእግዚአብሔር እጅ የታየው እንዴት ነው?
  3. ከዚህ ታሪክ የምንማረው መንፈሳዊ ትምህርት ምንድን ነው?

አስቴር 1-6 እስራኤላውያን ራሳቸውን ያገኙበትን አደገኛ ሁኔታ የሚገልጥ ሲሆን፥ አስቴር 7-12 ግን እግዚአብሔር የሐማና የጠላቶቹን ዕቅድ ለማፈራረስ እንዴት እንደሠራና ሕዝቡን እንደጠበቀ ይገልጣል። የሚከተሉትን ትምህርቶች ተመልከት፡-

1. አስቴር፥ እርስዋንና ሕዝቧን ያለ ምንም ምክንያት ሊገድል ማሰቡን በመናገር ሐማን ከሰሰችው። በውጤቱም ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው ግንድ ላይ ተሰቀለ (መዝ. (28)1-5 ተመልከት)

2. ንጉሥ አርጤክስስ በመንግሥቱ ሁሉ አይሁድን ለመዋጋት በሚያስቡ (ወይም በሚሞክሩ) ጠላቶቻቸው ሁሉ ላይ የመስቀል ሥልጣን ለአይሁድ እንደተሰጣቸው የሚገልጥ ትእዛዝ አስተላለፈ። ንጉሡም መርዶክዮስን የቅርብ አማካሪው አደረገው። በአንድ ወቅት በቤተ መንግሥት የሐማ የነበረውን የክብር ስፍራ መርዶክዮስ ወሰደ።

3. አይሁድ በጠላታቸው በሐማ ላይ ስላገኙት ድል የፉሪምን በዓል አከበሩ። ፉሪም የሚለው ቃል «ፉር» ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን፥ ትርጉሙም ዕጣ ማለት ነው። ይህም የሚያመለክተው ሐማና ንጉሡ አይሁድን ስለሚያጠፉበት ቀን ለመወሰን ያወጡትን ዕጣ ነው (አስቴር 37) እስራኤላውያንን ለማጥፋት ሐማ ዕጣ ቢጠቀምም እግዚአብሔር ግን ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ዕጣው በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ወደቀና ብዙ ሺህ አሕዛብ ተገደሉ። አይሁድ ዛሬም ይህንን በዓል በታላቅ ደስታ ያከብሩታል። በዚህ በዓል ዕለት መጽሐፈ አስቴር ለቤተሰቡ አባላት በሙሉ ይነበባል።

የመጽሐፈ አስቴር ዋና ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የግለሰቦች ታሪክ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል የሚካሄድ ጦርነት ታሪክ ነው። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የዚህን ጦርነት ፍንጮች እናያለን። ሰይጣን በጦርነቱ ለመዋጋት የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀምም ዓላማው ሁልጊዜ አንድ ነው። የእግዚአብሔርን ዕቅድና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ይፈልጋል።

በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ሁሉ ሰይጣን የደኅንነት መስመር እንዲቋረጥ ለማድረግ በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማበላሸት ታግሏል። ከዘፍ. 315 እንደምታስታውሰው፥ ከሴቲቱ ዘር ሰይጣንን የሚያጠፋ ሰው እንደሚመጣ እግዚአሔር ተስፋ ሰጥቷል። ሰይጣን የሴቲቱ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ስለሚያውቅ የሚመጣበትን የዘር ግንድ ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ የግብፅ ንጉሥ ሣራን በሚስትነት እንዲወስድ በማድረግ የአብርሃምን የዘር ግንድ ለማቋረጥ ሞክሮ ነበር። ርብቃንም መኻን በማድረግ የዘር ሐረጉ እንዲያበቃ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። በኋላም ሰይጣን የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በራብ ለመጨረስ የሞከረ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን በዮሴፍ በኩል እነርሱን ታድጎአቸዋል። በኋላም መሢሑ የሚመጣው በእርሱ በኩል መሆኑን እግዚአብሔር ለዳዊት ነግሮታል (2 ሳሙ. 714) ሰይጣን ግን የዳዊትንም ዘር ለማጥፋት በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሊያበላሽ ጥሮ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ እግዚአብሔር ካዳነው ከአንድ ትውልድ በቀር ጎተልያ የዳዊትን ዘር በሙሉ አጥፍታ ነበር፤ (2 ነገ. 111-3) አሁን ደግሞ በአስቴር ታሪክ ሰይጣን ሐማ የተባለውን የአንድ ሰው ጥላቻ በመጠቀም አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። አይሁድ ተደምስሰው ቢሆን ኖሮ መሢሑ ባልተወለደና ዓለምም አዳኝን ባላገኘ ነበር። እግዚአብሔር ግን የሰይጣንን ዕቅድ አከሸፈ።

ይህ እውነት ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን አንዳንድ የአይሁድ ታሪክ ለመረዳት ይጠቅመናል። በየትኛውም ስፍራ ይሁኑ አይሁድ ሁልጊዜ የሚሰደዱ ሰዎች ነበሩ። ይህም በተለይ የታየው 2ኛው የዓለም ጦርነት ሂትለርና ጀርመኖች 6 ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያንን ቢገድሉም፥ እግዚአብሔር ግን አሁንም ቢሆን ለአይሁድ ሕዝብ ዕቅድ ስላለው ሙሉ በሙሉ ሊያጠፏቸው ባለመቻሉ ነው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ በታሪክ ሁሉ ቅሬታዎችን በመጠበቅ አንድ ቀን ሊጎበኛቸውና በመካከላቸው ታላቅ ሥራን ሊያደርግ ዕቅድ አለው (ሮሜ 11 ተመልከት)

የውይይት ጥያቄ፥

  1. የማያምኑ ሰዎች ከክርስቲያኖች ጋር የሚታገሉትና ሊያጠፏቸው የሚሹት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይህ እውነት እንዴት ይረዳናል?
  2. ይህ እውነት በተጨማሪ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ እግዚአብሔር እንደማይፈቅድ ምን ያስተምረናል?

የታሪክ መጻሕፍት ክለሳ

እስካሁን ድረስ ባካሄድነው ጥናታችን ሁለት ዋና ዋና የብሉይ ኪዳን ክፍሎችን ተመልክተናል። በመጀመሪያ ፔንታቱክ በሚል ስም የታወቁትን በሙሴ የተጻፉትን አምስቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ተመልክተናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አሥራ ሁለቱን የታሪክ መጻሕፍትን ተመልክተናል። እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉት በተለያዩ ያልታወቁ ጸሐፊዎች ነበር። የሚናገሩትም በብሉይ ኪዳን ያሉትን የቀሩትን የእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ነው። ታሪኩም 1400 እስከ 400 .. ድረስ ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። እነዚህ 12 መጻሕፍት 1000 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናሉ። ታዲያ ሁሉም የታሪክ መጻሕፍት ቢሆንም በትምህርት ቤት እንደምንማራቸው የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉ አይደሉም። ይልቁንም እያንዳንዱ መጽሐፍ የተጻፈው መንፈሳዊ እውነትን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለማስተማር ነው። ከእነዚህ መጻሕፍት በምናነብበት፥ በምናጠናበትና በምንሰብክበት ጊዜ በውስጣቸው ያለው መንፈሳዊ እውነት ምን እንደሆነ ልንረዳና ለቤተ ክርስቲያን አባሎቻችን ልናስተምር ይገባናል።

የውይይት ጥያቄ፥

  1. 12ቱን የታሪክ መጻሕፍት ዘርዝር።
  2. እያንዳንዱን መጽሐፍ በሚመለከት መጽሐፉ የሚናገራቸውን ዋና ዋና የታሪክ ወቅቶች ዘርዝር። 
  3. በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ገጸ ባሕርያትን ግለጥ፡
  4. በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር።

የሚከተሉትን መጻሕፍት ዝርዝር ተመልከት

1. ኢያሱ፡- እንደምታስታውሰው ኢያሱ ሙሴ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ መሪ ነበር። ሕዝቡን ወደ ከነዓን ለመምራትና በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማሸነፍ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር። ኢያሱ በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። በኢያሱ ዘመን የተገኘው ድል አብዛኛው በምድራዊ ጠላቶች ላይ ነበር፤ ለእኛ ግን በመንፈሳዊ ጠላቶቻችን ላይ ስለሚገኝ ድል የሚያስተምረን ነው።

2. መሳፍንትና ሩት፡- ዘመነ መሳፍንት ኢያሱ ከሞተ አንሥቶ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ እስከ ሳኦል ዘመን ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን ወደ 400 ዓመታት ይጠጋል። የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና አሳብ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳ. 176 2125) በሚለው ጥቅስ ውስጥ ይገኛል። አይሁድ እግዚአብሔርን በመካድ የሐሰት አማልክትን (ጣዖታትን) የተከተሉበት የክሕደት ጊዜ ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት አይሁድ ያለፉበትን የውድቀት ሂደት ይናገራል። በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው በከነዓናውያን እጅ አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። ሦስተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ በባርነት ቀንበር ሥር ቆዩ። አራተኛ፥ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ እንዲያወጣቸው ወደ እርሱ ጮኹ። አምስተኛ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ የሆነ መስፍንን ወይም የጦር መሪን በማስነሣት ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና እንደገና ኃጢአት ሠርተው እስኪፈረድባቸው ድረስ የነፃነት ዘመን ሰጣቸው። በዚህ ዘመን የተነሡ ዋና ዋና መሳፍንት ናትናኤል፥ ናዖድ፥ ዲቦራና ባርቅ፥ ጌዴዎን፥ ዮፍታሔና ሶምሶን ነበሩ። የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመው በዘመነ መሳፍንት ሲሆን፥ አብዛኛው ሕዝብ እንዴት እግዚአብሔርን እንዳላከበረና በዚህ ዓይነት ጨለማ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ጥቂት ሰዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ነው።

3. 1 ሳሙኤል፡- 1 ሳሙኤል እስራኤል ከዘመነ መሳፍንት በአንድ ንጉሥ ሥር አንድ መንግሥት ሆና ትተዳደር ወደነበረችበት ወደ ነገሥታት ዘመን ስላደረገችው የሽግግር ጊዜ የሚናገር መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የእስራኤል የመጨረሻ መሳፍንት ስለሆኑት ስለ ዔሊና ስለ ሳሙኤል ይገልጣል። በተጨማሪ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ስለሆነው ስለ ሳኦልም ይናገራል። ስለ ሳኦል ውድቀትና ተከታዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እግዚአብሔር ዳዊትን እንዴት እንደመረጠው ይናገራል። 1 ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የሚናገረው ስለ ዳዊት ዝና አጀማመርና ሳኦልም ዳዊትን ለመግደል ስላደረጋቸው የተለያዩ ሙከራዎች ነው።

4. 2 ሳሙኤልና 1 ዜና መዋዕል፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የሚሸፍኑት ተመሳሳይ ጊዜያትን ነው። የሚናገሩትም በእስራኤል ተወዳዳሪ ስላልተገኘለት ስለ ታላቁ ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ለዳዊት የዘላለም ቃል ኪዳንን በመግባት በእስራኤል ሁሉ ላይ ገዥ የመሆን መብትን ለዘሩ እንደ ሰጠ እንመለከታለን። ይህንን ቃል ኪዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚፈጽመው አይተናል። እነዚህ መጻሕፍት በዳዊት ሕይወት ስለታየው መንፈሳዊ ታላቅነትና ወታደራዊ ኃይል ይናገራሉ። 2 ሳሙኤል በዳዊት ወታደራዊ ታላቅነትና ኃጢአት ላይ ሲያተኩር፥ 1 ዜና የሚያተኩረው ደግሞ በዳዊት መንፈሳዊ ሕይወትና ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድና ለቤተ መቅደሱ ሥራ ዝግጅት በማድረግ እግዚአብሔርን እንዴት እንዳከበረ በመናገር ላይ ነው።

5. 1 ነገሥትና 2 ዜና መዋዕል 1-18- እነዚህ መጻሕፍት ከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ወደ ተከፋፈለው መንግሥት የተደረገውን የሽግግር ዘመን የሚናገሩ ናቸው። የሁለቱም መጻሕፍት የመጀመሪያ ክፍሎች የሚናገሩት ጠቢብ ስለነበረው ስለ ዳዊት ልጅ ስለ ሰሎሞን ነው። 1 ነገሥት እስራኤልን ወደ ክሕደት በመምራት የእስራኤልን መንግሥት በሁለት ስለከፈለው ስለ ሰሎሞን ኃጢአት ይናገራል። 2 ዜና መዋዕል ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንዴት እንደሠራ ይናገራል። ቀጥሉ እነዚህ መጻሕፍት የሚናገሩት አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት እንዴት ለሁለት እንደተከፈለ ነው። በስተ ሰሜን የሚገኙት አሥሩ ነገዶች እስራኤል ተብለው የተጠሩ ሲሆን፥ ዋና ከተማቸውም ሰማርያ ነበረች። የብንያምና የይሁዳን ነገዶች የያዙት ሁለቱ ነገዶች ዋና ከተማቸውን ኢየሩሳሌም በማድረግ የይሁዳን መንግሥት መሠረቱ። 1 ነገሥት የሰሜኑንና የደቡቡን መንግሥታት የተለያዩ ነገሥታት በአጭር በአጭሩ ሲያቀርብ፥ 2 ዜና ደግሞ ያተኮረው በደቡብ መንግሥት ነገሥታት ላይ ነው። እንደዚሁም 1 ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ 2 ዜና የሚያተኩረው ግን በሌዋውያን ሥራ ላይ ነው።

6. 2 ነገሥትና 2 ዜና መዋዕል 19-36- እነዚህ መጻሕፍት የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል 722 .. በአሦር መንግሥት መደምሰሱንና የይሁዳ መንግሥት የሚባለው የደቡብ መንግሥት ደግሞ 586 በባቢሎናውያን መማረኩን ይናገራሉ። 2 ነገሥት የሚናገረው ስለ ሰሜኑና ላለ ደቡቡ መንግሥት ሲሆን 2 ዜና የሚያተኩረው ግን በደቡቡ መንግሥት ላይ ሆኖ በተለይ ደግሞ በይሁዳ እውነተኛ አምልኮን ለመመለስ የተሐድሶ ሥራ በሠሩ እግዚአብሔርን በሚፈሩ መሪዎች ታሪክ ላይ ነው። 2 ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ማተኮሩን ሲቀጥል፥ 2 ዜና ግን ስለ ሌዋውያን ሥራ ይናገራል።

7. መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር፡- እነዚህ ሦስት መጻሕፍት የሚናገሩት ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በኋላና አይሁድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ ስላለው ጊዜ ነው። ዕዝራና ነህምያ የሚያተኩሩት ከምርኮ ወደ ይሁዳ በተመለሱት አይሁድ ላይ ነው። መጽሐፈ ዕዝራ በዕዝራና በዘሩባቤል መሪነት የተመለሱትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት የእስራኤል ቡድኖች የሚገልጽ ሲሆን፥ በተጨማሪ ስለ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ መሠራትና ዕዝራ በይሁዳ ስለመራው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ ነህምያ ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራትና ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሰሙ ጊዜ በመካከላቸው ስለተፈጸመው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር የሚያተኩረው በምርኮ ምድር በነበሩ አይሁድ::

ላይ ነው። መጽሐፉ እዚአብሔር ሕዝቡን በቸርነቱ የፋርስ ንግሥት አድርጎ ባስቀመጣት በአስቴር አማካይነት ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸውና የሐማን ዕቅድ እንዳከሸፈ ይናገራል። የብሉይ ኪዳን ጥናት የመጀመሪያ ክፍል የሆነውን የዚህን መጽሐፍ ጥናት የመጨረሻውን ፈተና ለመውሰድ ተዘጋጅ። የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሚቀጥለው ጥናት እንመለከታለን።