መሥዋዕት
የሚበልጥን ነገር ለሚበልጠው መስጠት፣ ማቅረብ ነው። ያለቁጭት፣ ባለመፀፀት የሚቀርብ ነው። ያለኝ አንድ ብቻ ነው ሌላ የለኝም፣ አማራጭ የለኝም፣ ትርፍ የለኝም ብለን የምናስቀረው አይደለም። ያለኝን እሰጥሃለሁ፣ ከጉድለቴ እሰጥሃለሁ፣ ዋናውንና ምርጡን እሰጥሃለሁ ብሎ ባለማቅማማት፣ ባለመፀፀት የምንሰዋው አንዱ እና ዋነኛው አምልኮ እና የአምልኮ አይነት ነው። ለሰጪው መልሶ መስጠት ነው።
1- በአይነት የሚቀርብ አምልኮ
ይህ የአምልኮ ስርዓት የሚፈጸመው በግብርና ሙያ ላይ የተሰማሩ የሚያቀርቡት መስዋዕት ነው።
1.1. የእፅዋት ዘር መስዋዕት
“ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤” — ዘፍጥረት 4፥3።
1.2. የእንስሳ መስዋዕት
“አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤” — ዘፍጥረት 4፥4። መሥዋዕት የፈለገ ይሁን ከሥጋ ተዋፅዖ ብቻ ነው የሚቀርበው ብሎ ማሰቡ ትልቁ ስህተት ነው። የእንስሳት መስዋዕት ከእፀዋት ይበልጣል ብሎ ማሰቡ ተገቢም ትክክልም አይደለም። ዋናው ቁም ነገሩ ከተሰጠን የትኛውም ነገር የሚበልጠውን በእምነት ማቅረብ ሲሆን፣ ምርጡን ለራስ ቀጣዩን ለእግዚአብሔር ብለን የምናቀርበው አይደለም።
2- ሕይወታዊ መስዋዕት
2.1. በእግዚአብሔር ጥያቄ የሚቀርብ
ከአብራክ የወጣን በተለይም ማህፀን ቀድዶ የወጣን በኩር ልጅ ለመስዋዕት ማቅረብ ነው። በአብዛኛው እንዲህ ያለውን መስዋዕት የሚያቀርቡት መሃኖች ሲሆኑ፣ በስለት አሊያም በልመና ያገኙትን ብትሰጠኝ እሰጥሃለሁ ባሉት ቃል መሠረት መልሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የምላሽ የአምልኮ አይነት ነው። በዚህ መሥዋዕት የሚታወቁት አብርሃም እና ሳራ፣ ሃና ያቀረቡት ነው። አብርሃም በእግዚአብሔር ጥያቄ መሠረት ለመሥዋዕት አንድ ልጁን አቅርቧል።
2.2. በራስ ፍላጎት የቀረበ
ሃና ግን በልመናዋ መሠረት ብትሰጠኝ መልሼ እሰጥሃለሁ በማለት ስለትን ለእግዚአብሔር የመስጠት መስዋዕት ነው።
ሌላኛው የልጅ መሥዋዕት ያቀረበው ዮፍታሔ ሲሆን በተለይ በቤተሰቦቹ የተገፋ፣ በራሱ ወንድሞች ተንቆ የተገፋ ግን ወንድሞች እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያስቀመጠውን ጉዳይ ያላወቁ፣ የእስራኤል ሽማግሌዎች ግን የፈለጉት፣ በተለይ እስራኤልን ከጠላት ነፃ ያወጣል ብለው አምነው የፈለጉት፣ ዮፍታሔም እግዚአብሔርን አንድ ነገር ለመነ፣ በድል ብትመልሰኝ ከፊቴ የሚወጣውን አንድ ሰው እሰዋልሃለሁ በማለት ቃል የገባ፣ እግዚአብሔርም በድል የመለሰው፣ አንዲት ሴት ልጁን ግን ሰዋት። ለሚበልጠው የሚበልጠውን አቀረበ፣ ሰዋ። መሥዋዕት ምንም እንኳ የሚያሳሳ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ከበለጠ አንሳሳለትም፣ እግዚአብሔር ይበልጣልና።
መሥዋዕት ከተሰበረ ልብ የሚወጣ ንፁህ አምልኮ ነው። በብሉይ ዘመን የነበሩ ቀዳማይ አገልጋዮች ከመሥዋዕታቸው ቀደም ብሎ ጭንቀታቸው መሥዋዕቴን ይቀበላል የሚለው ሳይሆን ትልቁ ጭንቀታቸው በእግዚአብሔር ፊት እራሳቸውን አዋርደው የመንፃትን ስርአት መፈፀሙና ከስርዓቱ በኃላ እኔን ይቀበላል ወይ ትልቁ ጭንቀታቸው ነው፣ ሲቀበላቸው እግዚአብሔር ምልክትን እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ፣ በቀጣይነትም መስዋዕታቸውን ይቀበላል። “ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ።” — 2 ዜና 7፥1። “የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም።” — 2 ዜና 7፥2።
ከምን መሥዋዕት አይቀርብም
1- እግዚአብሔርን ከማይሰሙት አይቀበልም
እግዚአብሔር ከጠላቸውና ከጠላው ነገር በምንም አይነት መልኩና መንገድ መሥዋዕት አይቀርብም። በተለይም ፈጽሞ እንዲጠፋ እግዚአብሔር ከፈለገው ነገር ምንም እንኳን ለአይን ያማረ ቢሆን ለእግዚአብሔር ካላማረ ጨርሶ መሥዋዕት አይቀርብ። “ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።” — 1ኛ ሳሙኤል 15፥22። “ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና።” — መክብብ 5፥1።
2- መንፈሳቸው ካልተሰበረ
“እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” — መዝሙር 34፥18። “መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።” — መዝሙር 51፥16። “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” — መዝሙር 51፥17። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በቀዳሚነት መሥዋዕት ያቀረቡት አቤልና ቃየን የመሥዋዕታቸው ልዩነት በእግዚአብሔር ዘንድ ታይቷል። በቀዳሚነት አይነ ገብ የሆነው የአቤል መሆኑ ከመንፈሱ መሰበር የጀመረ ሲሆን፣ የቃየን በእግዚአብሔር ፊት በመንፈስ መሠበር ያልመጣ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። “ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።” — ዘፍጥረት 4፥5። አቤል ግን መሥዋዕቱን ከተሰበረ ልብ ማቅረቡ፣ ከበኩራቱም ማቅረቡ ተቀባይነት አገኘ፣ እግዚአብሔርም ተመለከ። የተሠበረ መንፈስ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተመረጠን ያቀርባል እግዚአብሔርም ይቀበለዋል። “አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤” — ዘፍጥረት 4፥4።
መሥዋዕት እንዴት ይቀርባል
በንጽሕና ይቀርባል
ብዙውን ጊዜ በተለይ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች እጅግ በድፍረት እየቀረብንም እያቀረብንም ያለነው መሥዋዕት በድፍረት ነው። ያለምንም ንጽህና ከነእድፈታችን በእግዚአብሔር ፊት የምናቀርበው መሥዋዕት እጅግ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ነው። የመሥዋዕት ማቅረብ ስርአታችን እጅግ ሕገወጥ የሆነ የድፍረት አቀራረብ ነው። ያዕቆብ በልብ፣ በመንፈስ መሠበር ከቤተሰቡ ጋር መሥዋዕት ማቅረብ ፈለገ ከመሥዋዕቱ ቀድሞ ምን መደረግ እንዳለበት ግን ጠንቅቆ ያውቃል ያንንም እጅግ በጥንቃቄ እንዲያደርጉ ቤተሠቡን ጥብቅ በሆነ ትዕዛዝ በማዘዝ አሰፈፀመ እርሱም ፈጸመ።
መሥዋዕት፦ በብሉይ ኪዳን ሲቀርብ የነበረው በዚህ መልኩ ሲሆን፣ እግዚአብሔር ከሰጠን ከየትኛውም ነገር ለእግዚአብሔር ምርጡን፣ የመጀመሪያውን፣ የበኩሩን ይሠዋለታል። ይህም እንድምታው እግዚአብሔር አንድ ልጁን ያውም የበኩር ልጁን የመስጠቱን ምስጢር በዋናነት ያመለክታል። የቀደመው ለአዲሱ ጥላ ነው።
መሥዋዕት፦ በአዲስ ኪዳን የሚቀርበው ማንነታችን ሲሆን ይኸውም ሕይወታችን ለራሳችን የበኩር ነው። “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።”— ሮሜ 12፥1።
በተለይ በወንድማማች ህብረት ውስጥ በባለንጀርነት ያለ ሊያጤነው የሚገባ ብርቱ ነገር ቢሆን በሚያስፈልገው ሁሉ፣ በሚጠይቀውና በሚጠበቅብን ነገር ሁሉ መውደድ አንዱ መሥዋዕት እንደሆነ ማወቅ ተገቢ ነው፣ ሊዘነጋም አይገባም በተለይ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚነሱ ጠብና ጭቅጭቅ ይህን በውል ባለመገንዘብ የሚመጣ ነው። ይህን የተረዳ ግን ሁሉን ስለ ፍቅር ይተዋል። መውደድ ከየትኛውም መሥዋዕት በላይ ነው ነው። ይህን የሚያውቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት ያልራቀ ሁሉ የሚያውቀው ነው። “በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው።” — ማርቆስ 12፥33።
በተለይ በዚህ ባለንበት ዘመን ጌተሠችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱን ለእኛ አሳልፎ መስጠቱን የምናምን እጅግ ሲበዛ ንፉጎች ነን። ስግብግብ መሆናችን በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። በመስጠት ደካሞች ባለመስጠት የታወቅን ነን። ከመስጠት መቀበል የሚቀናን ነን። ለሌሎች በመቆረስ፣ በማካፈል አንታወቅም፣ ይልቁኑ መለያችን ንፉግ መሆናችን ነው። ከዚህ የተነሳ መስጠት፣ ለሌላው መካፈል በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መሥዋዕት እንደሚቆጠርና እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘው መሆኑን አለማወቃችን ትልቁ አለማወቃችን እና ድክመታችን ነው። “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።” — ዕብራውያን 13፥16።
ጌታ ይባርካችሁ
በረከት ሱላሞ ሱጌቦ
+251902910126
