የታጠቀ ትውልድ

 

በዘመናት ሁሉ በየትኛውም የአገዛዝ ስርአት አይነት ውስጥ መንግስታት፣ የመንግስታት መሪዎች ትልቁ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው የወጣቱ ትውልድ ቁጥር ነው። የቁጥራቸውና የብዛታቸው ማነስ ስጋትን ሲያጭር፣ የቁጥራቸው መብዛት የነገ ተስፋ ፍንትው ብሎ ይታያቸዋል። የቁጥራቸው መብዛት የነገ የደህንነት ስጋታቸውን በእጅጉ ይቀንሰዋል፣ ብቁና የጠነከረ ትውልድ መኖሩ ነገ ለሚመጣው አሉታዊ ነገር ምላሽ የሚሰጥበት አቅም እንዳለው ፍርሃትን ይቀንስለታል። 

ብዙውን ጊዜ ተፃራሪ መንግስታት አንዱ አንዱን መሠለል የዘወትር ሥራቸው ሲሆን ይህም ምን ያህል ለውትድርና ብቁ የሆነ ወጣት አለ? የመጠነ ሐብትስ ምን ያህል ነው? ተባብሎ መፈታተሹና አንዱ አንዱን መሠለሉ የአቅምን ሁኔታ ለማደርጀትና ለማጎልበት ግብዓት ይሆናቸዋል። 

ዛሬም በቤተክርስቲያን ይህንን ዕሳቤ እና እውነት-ሐቅ ይዘን ካልተጓዝን ነገ ወንጌል እንዴት? ቤተክርስቲያን እንዴት ትቀጥል? የጨለማውን መንግስት እንዴት ድል አንንሳ የሚለው በእጅጉ በአእምሮአችን ዘወትር  ሊመላለስ ይገባል። 

ዛሬም በቤተክርስቲያን አያሌ ወጣት ቢኖርም፣ ቁጥሩ የበዛ ግን በእግዚአብሔር የእውነት ቃል ላይ ተመርኩዞ ያልታጠቀ፣ ጥቂት በቁጥር ያነሰ ወጣት ቢኖርም የታጠቀ ግን ሥራ ላይ ያልዋለ የባከነ ወጣት ይታያል። “ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ።”— 1ኛ ሳሙኤል 13፥22።

ያልታጠቀ ትውልድ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሁን ለጠላት ምቹ ሆኖ የሚገኝና ጠላትም እንዳሻው የሚያደርገው ነው። ጠላት እንደፈለገው ከሚያደርጋቸው የትውልድ አይነቶች አንደኛው ጎልማሳው በእግዚአብሔር ቃል ሙላት ያልታጠቀ ትውልድ ነው። በተለይ በትምህርት ንፋስ ወዲህና ወዲያ እየተፍገመገሙ ያሉ እርግጠኝነት የሌለበቸው፣ ሁሌም በጥርጥር የሚኖሩ እነዚህ ሁሌም ተሸናፊዎች ናቸው። “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።” — መዝሙር 119፥9። 

                               

      የታጠቀ ትውልድ

 

1) ደፋር ነው
በእርግጥ እግዚአብሔር በዘመናት መሐል በአንድ ነጠላ ሰው ሲሰራ አይተናል። "በብዙም በጥቂቱም መዳን እንደማይሳነው" እርግጥና እውነት ነው። “ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው።” — መሳፍንት 3፥16። ለዘመናት ሲያስገብር፣ ግብር የለመደ ኤግሎም በአንዱ በታጠቀ፣ እግዚአብሔር ጥበብን የሰጠው ባዘጋጀው ሁለት አፍ ባለው ሰይፍ ገደለው። እንዲህ ማዘጋጀት ይሁንልን! አሜን! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ያሸነፈው በእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ በሙላት ይኑርብን! አሜን!
“ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤” — መሳፍንት 3፥21። “የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።”— መሳፍንት 3፥22። ናኦድም በታጠቀው መሣሪያ የዘመናት ጠላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል አሸነፈው። "እረኛውን መታ መንጋው ተበተነ"። “በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች።” — መሳፍንት 3፥30። የታጠቀ የዕረፍት ሰው ነው፣ የእረፍት ሰው የሆነ መስፍን ምድሪቱን እስራኤልን ከሞዓብ አሳረፈ፣ ሞአብም ተዋረደ። 

እንግዲህ ቤተክርስቲያንም በታጠቁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያውም ኤፌሶን 6 ላይ አንደተገለጸው የታጠቁ ትውልዶች ይኑሩን። የእግዚአብሔርን እቃ ጦር መልበስና መንሳት ለትውልድ ይሁን። 

2) አይፈራም

የታጠቀ ሰው በምንም መልኩ ይሁን ፍርሃትና መደናበር ስጋት አይታይበትም። ይልቁኑ ለሌሎች ነፃ መውጣትና፣ ከጠላት ለመከላከል በታጠቁት መሣሪያዎች ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ቤተክርስቲያንን፣ ሐገርን፣ ራሳቸውንም ከሚዞራቸው ከጠላት ይጠብቃሉ። ከመታጠቃቸው ባሻገር ጠላቶቻቸውን ሄደው ፈልገው ይዋጋሉ። ልበ ደፋሮች ናቸው፣ ከመድፈራቸውም በላይ አ ገባቸውም ያለው እጅግ ልበ ደፋሮች ናቸው። “ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ጭፍራ እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው።”— 1ኛ ሳሙኤል 14፥6። “ጋሻ ጃግሬውም፦ ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፤ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው።”— 1ኛ ሳሙኤል 14፥7። 

3) ዝግጁ ነው

በአለም ላይ ካሉ እምነቶች ወይም የሐይማኖቶች መሐል እጅግ ጠላትና ቀበኛ ያለው እምነት ቢኖር ክርስትና ነው። የተቃዋሚው ብዛት ቁጥሩ ትንሽ የማይባል ሲሆን በብሉይ ካዳን ይሁን በአዲስ ኪዳን ፈተና የበዛበት እምነት ቢኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ ተመርኩዘው በክርስቶስ መንገድ የሚሄዱት ናቸው። ስለዚህ ጠላት የበዛበት ዘወትር ታጥቆ የሚኖር፣ መሣሪያና ጋሻን የሚያመርትም ነው። “ሰውነቱንም አጸናና፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ ሠራ።”— 2 ዜና 32፥5። ስለዚህ፦ “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ....” — ቆላስይስ 3፥16። “ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።” — ኤፌሶን 6፥13። “የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” — ኤፌሶን 6፥17። 

በመጨረሻም፦ የታጠቀ ትውልድ ያለባት ቤተክርስቲያን በምንም አይነት መንገድ ይሁን ለጠላት ምቹ አይደለም፣ ለሌላውም ይተርፋል፣ የእረፍት ሰውም ነው። ለአርባ ቀናት የጎልያድን ስድብ የጠገቡ ሳዖልና ሰራዊቱ በአንዱ በታጠቀ ዳዊት ሕዝበ እስራኤል ነፃ ወጣ። ሐገረ መንግስቱም፣ መሪውም፣ ሠራዊቱም ነፃ ወጣ።  ታጥቆም የማይዋጋ ሠራዊት እንዳለም መዘንጋት የለብንም። 

ሙሴ ኢያሱን እንዳለ ዛሬም ቤተክርስቲያን ይህንን መርህ መከተል አለባት። “ሙሴም ኢያሱን፦ ጕልማሶችን ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው።”— ዘጸአት 17፥9።
ትውልድ በውስጡ የተዋጊነትን ስሜት ካላደበረ እና ሁሌም በውጊያ አውድ ውስጥ እንዳለ ሊረዳና ሊያውቅ ይገባል።
 
የእግዚአብሔርን ጦርነት የምንዋጋ ነን!
በረከት ሱላሞ ሱጌቦ