ያመንሁትን አውቃለሁ 

መሪ ቃል፦

“ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።”   — 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥12።

የቀደሙ አባቶች በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት ተፈትነዋል፣ ለእምነታቸውም በፅናት ተጋድለዋል፣ በምድር በኖሩባቸው ዘመናት ሁሉ እግዚአብሔርን ለሌሎች አሳይተዋል፣ ገልጠዋል በኑሮአቸው ሁሉ እግዚአብሔርን አሳይተው አልፈዋል። “ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” — ማቴዎስ 5፥12። “በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥6። የሚልን ንግግር ለሌሎች በመግለጥ የሕይወት ቁርጠኝነትን፣ በህይወታቸው ላይ እስከ የት ጥግ ድረስ እንደሚሄዱ ያሳያሉ፣ አሳይተውማል።

ያመኑትን የሚያውቁ በእምነታቸው፣ በክርስትና ሕይወታቸው እስከየት ጥግ ድረስ እንደሚሄዱ በውል ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ ለታመኑለት ጌታ የህይወት ዋጋ፣ የሕይወት መሥዋዕትነትን ይከፍላሉ፣ ከፍለውም አሳይተዋል። ያመኑትን የሚያውቁ ክርስቲያኖች ላመኑበት እግዚአብሔር ፅናታቸውን የሚያሳዩ ሲሆን፣ ዋጋ ቢያስፈልግ እንኳን ዋጋ ለመክፈል የቆረጡ እና የተዘጋጁ ናቸው። ምክንያቱም የተገለጠላቸውን እግዚአብሔር፣ የፈለጋቸውን እግዚአብሔር በትክክል ያውቃሉና። ለዚህ ነው ጳውሎስ ለተገለጠለት፣ በደማስቆ መንገድ ሊቋቋመው በማይችል መገለጥ ስለተገለጠለት፣ ለተገለጠለት ክርስቶስ፣ ላመነው ክርስቶስ በሌሎች ዘንድ "ያመንሁትን አውቃለሁ" ማለቱ። በሰዎች ዘንድ መሠከረ፣ የአቋም ጽናቱን ለሌሎች አሳየ፣ መሠከረ።

የቀደሙ አባቶች በእምነታቸው ምክንያት በደረሰባቸው መከራና ችግር ያመኑትን እግዚአብሔር በውል ማወቃቸው በአደባባይ፣ በብዙ ሰዎች ዘንድ መስክረው "መንግስታትን ድል ነስተው" ያለፉት። የሕይወት ጥራት ያላቸው፣ በእንከንነት የማይታወቁ፣ በሌሎች ዘንድ ጥርት ያለ የሕይወት ምሥክርነት ያላቸው ናቸው።

ጳውሎስ ለክርስቶስ ወንጌል መከራን የተቀበለ ከመሆኑ ባሻገር በዚህ መከራ አላፍርበትም፣ ምንምም የሚያሳፍር ጉዳይ የለውም ምክንያቱም ያመንሁትን ወንጌል ክርስቶስን አውቃለሁና በማለት ምክንያታዊ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል። ያመነውን በውል ያወቀ ላመነበት ዋጋ መክፈሉ ኪሳራ እንደሌለበት ባይሆን ትልቅ ብድራትና ሽልማት እንዳለው በጥንቃቄ ያውቃል። ወንጌል ይሄ ነው፣ ክርስትናም ይሄ ነው። ጳውሎስ በነበረበት ዘመን ይሄ ቃል በውል የገባው ነው፦ “በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።”   — ማርቆስ 8፥38። ዛሬም በዚህ ዘመን ላለን አማኝ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ ህይወት ሊገባን የሚገባው፣ ልንኖረው የሚገባ ህይወት ይሄ ነው። በተለይ አመፅ፣ አመፀኛ እና አመጸኝነት በበዛበት በዚህ ዘመን ልንኖረው የሚገባ ህይወት ይሄ ነው። ለሌሎችም ምስክርነትን እስኪሰጥ ድረስ ሊኖር የሚገባ ሕይወት ይሄ ነው።

በተለይ ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ የሚነግረው፣ የሚመክረው ነገር ቢኖር ረጅሙን የአገልግሎት ዘመን እንዴትና በምን አይነት መንገድ መምራትና ማገልገል እንዳለበት ሊያውቅ የሚገባቸውን ብርቱና አብይ ነገሮች ሳይነግረው አያልፍም፣ የሚጠቅመውን ሁሉ ባለመሰሰት ይነግረዋል።

ያመኑትን የሚያውቁ

ሌሎችን በማንቃት ያሳውቃሉ 

እውቀት ለክርስቲያኖች እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። አቅልለን ልናየው የሚገባ ነገርም አይደለም። በተለይ የእግዚአብሔር ቃል ከሚነግረን ነገር አንዱ በተለይ "ሕዝቤ እውቀትን በማጣቱ ጠፍቷል" ሲል ከመጥፋት መትረፊያውን "እንወቅ እናውቀውም ዘንድ እንከተል" የሚለውን በሚገባ አለማወቃችን እምነታችንን በተለይ ክርስትናችን እና ክርስቶስን እርሱን አለማወቃችን ጥፋት እና መጥፋት እንደሆነ ጨርሶ አናውቅም። ያወቀው ጳውሎስ ግን ከእውቀቱ በመነሳት ለሌሎችም ሲያጋራና ሲያነቃ በተለይም የመንፈሳዊ ልጁን ጢሞቴዎስን ሲነግረውና በመልእክቱ ሲጽፍለት እናያለን። “ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።”   — 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥12።

በመከራ የማይሸነፉ ክርስቲያኖች ያመኑትን የሚያውቁ ናቸው። ስለዚህም ሌሎች ያመኑት ማንን እንደሆነ በውል እንዲያውቁና በመከራ ውስጥ መውጫን እንደሚያዘጋጅ እንዲያውቁ ጭምር ለሌሎች ይነግራሉ።

ያመኑትን የሚያውቁ አማኞች መከራ ለሚያመጣባቸው አካል በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነትና አቋም በአንደበታቸው ይገልፃሉ። መከራ መምጣቱ ከምን ሊያስቀራቸውና ሊያጎድላቸው እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። መከራ ቀላልና የጊዜው እንደሆነ በማወቃቸው ዘላለማዊውን ነገር አያስነኩም።

ያመኑትን የሚያውቁ

በእግዚአብሔር ጉዳይ አይደራደሩም 

በየዘመናቱ እግዚአብሔርን የሚከተሉ፣ የሚያምኑ፣ የሚያመልኩ አንድም ዘመን ከመከራ ነፃ ሆነው የነበሩበት ዘመን የለም። የኖሩባቸው ዘመናት በአጠቃላይ ከመከራ ጋር የኖሩ፣ ያመኑበትን እስከሚተዉ እና እስከሚክዱ ድረስ እጅግ ክፉ የሆነ መከራን ተቀብለው በእምነታቸው በመፅናት መንግስታትን ድል ነስተው ኖረዋል። በተለይ በስደት አገር በመኖራቸው የሌላውን እምነት በመኮነን የራሳቸውን እምነት በመያዝ ጸንተው በመቆም የሌላውን እምነት አፍርሰው የራሳቸውን እምነት በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት በማሳየት እግዚአብሔር በሰው አገር በምርኮ ባሉበት አገር እግዚአብሔር እንዲመለክ አድርገዋል። “የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገርና ከተማ ሁሉ ለአይሁድ ደስታና ተድላ፥ የግብዣም ቀን መልካምም ቀን ሆነ። አይሁድንም መፍራት ስለ ወደቀባቸው ከምድር አሕዛብ ብዙ ሰዎች አይሁድ ሆኑ።” — አስቴር 8፥17። ዋጋ መክፈል እግዚአብሔርን ማስከበር እንደሆነ በውል ያውቃሉ። “ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም።” — ዳንኤል 3፥16። “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!” — ዳንኤል 3፥17። “ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።” — ዳንኤል 3፥18።

እግዚአብሔርን የሚያውቁ

ብርቱዎች ናቸው 

በዘመናችን በተለይ ለማወቅ ያለን ፍላጎት እጅግ አናሳና ለእውቀትም፣ ለማወቅም ያለን ፍላጎት ከቸልተኝነት እና አንባቢም ካለመሆናችን የተነሳ ለእውቀት ያለን አመለካከት እጅግ የወረደ ነው።  በእርግጥ እግዚአብሔርን አውቀን ልንጨርሰው ይቅርና በጀመርን ጊዜ እንኳ ጨርሶ እንዳልጀመርን ይሰማናል። እግዚአብሔርን በመከራ ዘመን እና በመከራ ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን የሚያውቁ ብርቱዎች ናቸው። መከራውን ያልፋሉ፣ ይሻገራሉ፣ አይዛቸውም። “ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም።” — ዳንኤል 11፥32።

በትዕግሥት የሚሮጡ ናቸው

ያመኑትን የሚያውቁ የተለየ ባህሪያቸው ትዕግሥተኛ መሆናቸው ሲሆን በተለይም ሌሎችም ጭምር በዚህ ማንነት ራሳቸውን እንዲቃኙና፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጭምር ሌሎችን ያነቃሉ፣ ያነሳሳሉ። የትኛውም አይነት መከራ ቢመጣ በጽናት እንደሚያልፉ ምስክሮች ናቸው። በዋናነት ከእነርሱ ቀድመው የነበሩትን አማኞች ለአብነት በማንሳት እነርሱ ለህይወታቸው ምን ያህል የጽናት ምስክር እንደሆኑና የሕይወት ምስክርነታቸው፣ ተግባራዊ ህይወታቸው፣ የአቋም ማንነታቸው እና ጽናትን በማንሳት በዚያው መንገድ ለመሄድ አምነው፣ ቆርጠው መነሳታቸውን ያመላክታሉ። “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”— ዕብራውያን 12፥1-2።

ነውርን የሚንቁ ናቸው

ያመኑትን የሚያውቁ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ፈለግ የሚከተሉ በተለይ ነውረኛን ነገር፣ ረብ የሌለውን ነገር በመናቅ ከፊት ያለውን ደስታ የዘላለምን ህይወት በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥን አይተው መከራን፣ ችግርን፣ ስደትን፣ ስቃይን ችለውና በእግዚአብሔር ኃይል ተቋቁመው ለደስታቸው ይኖራሉ ዋጋንም ይከፍላሉ። በተለይ በእጃቸው ያለውን እንኳን እስከመተውና፣ ጥቅማቸውንም ጭምር እርግፍ አድርገው በመተው የሚበልጠውን የዘላለምን ጉዳይ ያጠነክራሉ፣ ለመያዝም ይዘረጋሉ። “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” — ዕብራውያን 12፥1-2።

ያመኑትን የሚያውቁ

የአቋም ሰዎች ናቸው

በዘመናቸው እግዚአብሔርን ባመኑበት ልክና ከዚያም ባለፈ መከራ ውስጥ የሚያልፉ፣ በተለይም በሌሎች ፊት ወይም ዘንድ የደረሰባቸው መከራ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል እና እየከፈሉት ላሉት ዋጋ የሚከፍሉት መስዋዕትነት ስለእነርሱ ሌሎች ይጨነቁላቸዋል፣ መከራውን የሚከፍለው ግን በእግዚአብሔር ላይ ያለው ተአማኒነት ግን በሌሎች ዘንድ ዋጋ እስከሚያጣ የሚደርስ ሲሆን በመከራ ውስጥ ያለው የታመነበት ግን እግዚአብሔርን በማመን መከራን ይቀበላል፣ ምክንያቱም የታመነበትን ያውቃል፣ ያመገውንም ያውቃል። በተለይ በእምነቱ ላይ ለመጣ ምን ያህል እግዚአብሔርን በተመቸም ይሁን ባልተመቸ ሁኔታ እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ ቁርጥ ያለ አቋምን ይገልጻሉ። የጽናታቸው ጥግ ከፍ ማለት የትኛውም መከራ አቋማቸውን አልሸረሸረው።“እርሱ ግን አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።” — ኢዮብ 2፥10። ያመኑትን እግዚአብሔርን በውል ማወቅ መከራ ሊያናጋው አቋም ሊያስቀረውም አይችልም።

የደረሰባቸው መከራና ችግር በእነርሱ ላይ ያመጣው ምንም አይነት ችግር የለም። በእሳት መግባታቸው እና መጣላቸው የእሳቱ ኃይል በእነርሱ ላይ ያመጣው ምንም አይነት ነጀር የለም።  በእሳት የገባ እሳቱ አላቃጠለውም፣ በአናብስት ጉድጓድ የተጣለም አንበሳ አልበላውም ያመኑትን ያውቃሉና። የተከተሉትንም እግዚአብሔር በውል ያውቁታል። በሚያምኑት እግዚአብሔር አይደራደሩም። “እርሱ ግን አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።”— ኢዮብ 2፥10። “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!” — ዳንኤል 3፥17።

በተለይ ማቴዎስ በመከራ ውስጥ አልፈው የነበሩትን መጥቀሱ መከራ የዛሬ ሳይሆን ጥንት ከእኛ በፊት የቀደሙት ዋጋ ከፍለው እንዳለፉ የእምነት አባቶችን ጠቅሶ ጽፎአል። በዋናነት ግን መከራን በማስቀደም ሳይሆን ዋጋው ላይ በተለይም በሰማያት ታላቅ መሆኑን ገልጿል። ዛሬ በእኛ ዘመን የጀመረ አለመሆኑን በማሳመን ደረጃ ገልፆታል። “ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” — ማቴዎስ 5፥12።

ምንም እንኳን በምድር ሳለን መከራ እንዳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢገልጽም እርሱ አንድ ብርቱ የሆነ ተስፋን ሰጥቶናል። አይዞአችሁ እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ ማለቱ ትልቅ የድፍረት ቃላችን ሲሆን ዛሬ ያለን ክርስቲያኖች ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ብሎ በማመን ድል በመንሳቱ በሚያዞረን በእርሱ ላይ ታምነን ነውርን በመናቅ፣ ረብ የሌለውን ነገር በመተው በትዕግሥት መሮጥ ይሁንልን። በመከራችን እየተመካን የድል አክሊል፣ የጽድቅ አክሊል፣ የሕይወትን አክሊል፣ የክብርን አክሊል፣ የማይጠፋው አክሊል ለማግኘት ለሽልማታችን በመከራ መታገስ ይሁንልን። “እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።”   — ራእይ 3፥21።

GOD BLESS YOU ALL.

BEREKET SULAMO SUGEBO