ክርስትና በእግዚአብሔር ፊት በምመካድ፦ለሰው ህይወትና መስተጋብር የምንገልጸው ሕይወት ነው። እግዚአብሔር የሚጠላውን ጠልተን፣ እግዚአብሔር የሚወደውን ወድደን እግዚአብሔርን እያስደሰትን የምንኖረው ሕይወትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው። 

ብዙውን ጊዜ እኛ አማኞች የክርስቶስ ተከታይ ክርስቲያን ነን ብለን በኑሮአችን ግን ክርስቶስን የሚመስል፣ የሚገልጽ፣ የሚያሳይ ግን ያይደለ፣ ስለ ክርስትና እና ስለክርስቲያንነታችን ግድ ያለው አንመስልም። ምክንያቱም በሥራችን ክደነዋልና። " እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።" ቲቶ 1:16

ክርስትና አንዱ ባህሪው ፈተና ያለበት የእውነት እምነት ነው። መከራ ያለበት፣ ፈተና የማይለየው፣ ውጊያ የማይጠፋበት ግን አንድ ቀንም ሽንፈት አስተናግዶ የማያውቅ፣ መጨረሻው በድል ዜማ የሚንበሸበሽ፣ ይህም አንዱ ባህሪው የማይሸነፈው እግዚአብሔር ከፊቱ ያለበት እምነት ስለሆነ ነው። ስለዚህ በእምነታችን ብንፈተንም እንዲህ የሚል የጸና የእግዚአብሔር ቃል አለን፦ "በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።" ያዕቆብ 1:2

በክርስትና ሕይወት ውስጥ የፈተና መብዛቱ፣ የመከራ ማየሉ፣ የችግር መጽናቱ ኢላማ አድርጎ ሚነሳው ወይ ሊያጠነክረን አሊያም ከእግዚአብሔር ሊለየን ይሆናል። ለዚህ አብነት ለማንሳት ያህል ኢዮብ የተፈተነበት መፈተን የሰው ልጅ ሊገጥመው የማይገባ ፈተና እንደሆነ እናስባለን፣ ሆኖም ግን ይህ መከራ እሱን ከእግዚአብሔር ሊለየው አልቻለም፣ መከራው ያልለየው ኢዮብ የሚስቱ ፈተና ድራቢ በችግሩ ላይ መጣ።  እንዲህ ስትል፦ "ሚስቱም፦ እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው።" ኢዮብ 2:9። በዚህ ዘመን እጅግ ካልተጠነቀቅን እምነታችንን የሚያሳጣ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መልካምና ጤናማ ግንኙነት የሚያሻክር ይባስ የሚያጠፋ ነገር እጅግ ብዙ ነው። "ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል"። አንዳንዴም መከራ ያልጣለን ክፉ እና ሰነፍ ሰው ሊጥለን አሊያም ሊያስጥለን ይችል ይሆናል።

ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ የሚያስረግጥልን፦ "ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትእግስትን እንዲያደርግ፥ ትእግስትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን" ሮሜ 5:3-4 የድል አክሊል ይጠብቀናል።

መከራን ለመሻገር ግን ዋነኛው እና ትልቁ አቢይ ጉዳይ ተስፋና ጸሎት ነው። "በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ" ሮሜ 12:12

ሌላኛው መፍትሔ የእግዚአብሔር ቃል አስረግጦ እንደሚነግረንና እንደሚያስረዳን፦ "ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው።" 2ኛ ቆሮንቶስ 1:6። ስለዚህ በመከራ መዳናችንን እንዳናጣ በምናገኘው ሽልማት መጽናናት ይሁንልን።

የጊዜው መከራ፣ የማይዘልቀው ችግር ዘላለማዊውን ህይወት እንዳያሳጣን በእጅጉ ልንጠነቀቅ፣ ፍጹምነታችንን ከመያዝ እንዳይከለክለን፣ እንዳያሳጣን እንጠንቀቅ። "የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።" 2ኛ ቆሮንቶስ 4:17-18። ስለዚህ እትኩሮታችን በማይታየው እጅግ ዘላለማዊው ላይ ይሁን።

መለያ ባህሪው፦

1- አለማዊነትን መካድ፦ ብዙውን ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ክርስቲያን እንባል እንጂ ምልልሳችን ግን ከአለማዊያን በእጅጉ የሚራራቅ አይደለም ይልቁኑ የሚቀራረብ እንጂ። ለማያምኑት ምሳሌ የምንሆነው ነገር የለንም። በየትኛውም ቦታ እንሁን የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችን ምልልሳችን፣ ባህሪያችን፣ ተግባቦታችን በእግዚአብሔር ፊት እየተመላለስን እንደሆነ አይደለም ሊገልጽ ፍንጭ አይሰጥም።  በእግዚአብሔር ፊት መመላለሳችን ኑሮአችን፣ የኑሮአችንም ዘይቤ እና አይነቱ ነው። "ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ እራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል።" ቲቶ 2:12-13።

2- ኃጢአትን መካድ፦ በእጅጉ እኛን ክርስቲያኖችንና እግዚአብሔርን ከሚለዩን ነገሮች አንዱ የኃጢአት ልምምድ ሲሆን፣ ይህም ልምምድ ከቆይታ የተነሳ አመል ሆኖን ምንም እስከማይመስል ድረስ ይደርሳል። ይህም ኃጢአተኝነት ሞትን የሚወልድ መሆኑን ለአፍታ ልንዘነጋው አይገባም። "...ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን...." ቲቶ 2:12-13። ስለዚህ ከኃጢአት መራቅ ነው። 

ኃጢአት በመስራታችን ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው በረከቶችና ትሩፋቶች ጎድለን ተገኝተናል፣ ኃጢአትን ባለመስራት ግን ክብሩ አይጎድልብንም። "ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋልና" ሮሜ 3:23። "ሰውንም፦ እነሆ፦ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።" ኢዮብ 28:28።

3- ስጋዊነትን መራቅ

4- አካሄድን ማስተካከል

5- ከክፋት መራ፦ከክፋት አለመራቃችን አንድም ለእግዚአብሔር ክብር፣ አንድም ለማያምኑት ምሳሌ እና ምስክርነት አይሆንም፣ ለእኛም ጨርሶ በረከትን አያመጣም፣ ከማራቅ በስተቀር።

"የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል።" ምሳሌ 16:17።

በክርስቶስ የዳነ ሁሉ ሊሸሻቸው ከሚገቡ ነገሮች እነዚህ አምስቱ ዋነኞቹ ናቸው። በራሳችን ስህተት የምናመጣው ስህተት፣ችግር፣ መከራ፣ ፈተና ይዞ ሊመጣ ይችላል። በመጨረሻም በክርስትና እምነታችን ላይ፣ በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት የሚደርስብንን የትኛውንም አይነት ችግር፣ መከራ፣ ፈተና እንደ ሙሉ ደስታ እንቁጠረው። "ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት" ያዕቆብ 1:2-3

ተባረኩ

አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ