መጋቢነት 

 

 

የእግዚአብሔር ለህዝቡ መራራቱ የዛሬ አሊያም የቅርብ ጊዜ አይደለም። ከጥንትም የእግዚአብሔር ባህሪ ለሕዝቡ መራራቱ ነው። ምንም እንኳን አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ፈቀቅ በማለት በመሸሻቸው እግዚአብሔር መጣራቱና መፈለጉ ምን ያህል እግዚአብሔር እጅግ ርኅሩህ መሆኑን፣ ለልጆቹም ምን መሐሪ መሆኑን ማወቅ እንችላለን። 

እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚቀና ለምድሩም የሚራራ አምላክ ነው። ይህ የእግዚአብሔር መለያውና የምህረቱ ባህሪው ነው። በተለይ ለኪዳኑ ህዝብ፣ ለጠራውና ለለየው ህዝብ የሚራራ ነው። ከመራራቱም በላይ አንድያ ልጁን መስጠቱ እንድንጠፋበት አለመፈለጉን መግለጫ ነው።

በዋናነት የእግዚአብሔርን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በምናነብት ጊዜ እግዚአብሔር ምን ያህል ለሕዝቡ እንደተጨነቀና፣ በአገልጋዮቹም ተጠቅሞ ምን ያህል ለህዝቡ የእረኝነቱን ባህሪ እንዳሳየን በስፋት እንመለከታለን።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በአብዛኛው የተገለጡት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ምን ያህል በእግዚአብሔር እረኝነት ውስጥ ያለውን የእረኝነትን እሳቤ ተረድተው በሱ ልክ መጨነቃቸውን በውል መመልከት እንችላለን። በአብዛኛው በአገልግሎታቸው ውስጥ ለህዝብ መራራታቸው እግዚአብሔር በፈለገው ልክ ተረድተው አገልግሎታቸውን ሠርተው ፈጽመዋል።

እረኝነት ክርስቶስ የመጣበት ዋነኛ አላማው እንደነበረ፣ በተለይም በበረት ውስጥ ላሉት ብቻ ሳይሆን፣ ከበረት ውጭም ላሉት ጭምር የእረኝነቱ ጭንቀት ነበረ።

የእረኝነት ትልቁ ተልዕኮው አደራን ከመቀበል ጋር ተያይዞ አንድም መንጋ እንዲጎድል፣ አንድም መንጋ እንዲጠፋበት አይፈለግም፣ ይህም አይጠበቅበትም።

ብዙውን ጊዜ ችላ ባይ እረኞች፣ ኃላፊነትን እና አደራን ቸል በማለት እንኳን የጠፋውን በአጠገብ ያለውን ያጣሉ፣ ይጠፋባቸውማል።

ዛሬም በዘመናችን የምናያቸው አንድም በስም መሾም ግን በግብር፣ በምግባር፣ በሥራ ግን የማይገለጥ መጋቢ ተብሎ በመቀመጥ፣ መጋቢ ሳይሆኑ ተመጋቢ፣ አደላቢ ሳይሆኑ ደላቢ፣ አሰማሪ ሳይሆኑ ተሰማሪ፣የከሳውን ተመልካች ሳይሆኑ፣ መክሳታቸውን የሚመለከቱ፣ የተመረጠውን ለመንጋው ሳይሆን ለራስ መናኛውን ለመንጋው አቅራቢ በበዛበት ዘመን፣ የሰባውን መርጦ ተመጋቢ እጅግ የበዛበት ዘመን ቢኖር ይህ ዘመን ነው።

ዳዊት እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም።” — መዝሙር 23፥1። እግዚአብሔር እረኛውና እንደማያሳጣውም በውል ያወቀ ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው፣ በዘመኑ የእግዚአብሔርን ሐሳብ አገልግሎ የኖረ፣ በምድረ በዳ የአባቶቹን በጎች ሲጠብቅ የኖረና፣ ድብና አንበሳ ግልገሎቹን ሲውድበት ተከታትሎ የሚናጠቅ፣ የነጠቁትንም ዳግም እንዳይመለሱ ገድሎ የሚመጣ በእርግጥም እረኝነት የገባውና የተረዳ ትልቅ መሪ፣ በምድረበዳ እግዚአብሔር ባለማመደው ህይወት ወገኑን ከጠላት እጅ ያስጣለ፣ ጎልያድን በአንድ ድብልብል ድንጋይ በእግዚአብሔር ስም የጣለ ትልቅ ለሐገሩ፣ ለሕዝቡ፣ ለእምነቱ፣ ለእግዚአብሔር ክብር እረኝነቱን የጀመረ አገልጋይ ነው። በዚህ እውነታና መረዳት ውስጥ ካልገባን እረኝነት እጅግ ከባድ ነው። “በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።” — 1ኛ ሳሙኤል 17፥40።

 

መንጋን ለይቶ ማወቅ 

 

 

እረኛና መንጋ አብረው ለመቆየት የእርስ በእርስ መተዋወቅ፣ ድምፅን መለየት፣ መልክን ለይቶ ማወቅ እና መተዋወቅ የግድ ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።” — ዮሐንስ 10፥14-15።

መንጋን ለይቶ ማወቅ የእረኛ ትልቁና ዋነኛ ተግባሩ ነው። ምንም እንኳን አካላዊ ቁመና እና መልካቸው ለየቅል ቢሆንም የራስን መንጋ ለመለየት እጅግ ጠቃሚ ነው።

ዛሬ በዘመናችን ያሉ እረኞች ለቀረቧቸው አሊያም ያዋጡናል ብለው የሚያስቡትን እንጂ የደከመን፣ በማህበራዊም ይሁን በኢኮኖሚ አቋማቸው ዝቅ ያሉትን የደከሙትን ሲመለከቱ ሲጎበኙ አይታይም። ይህ ደግሞ የአንድ እረኛ ባህሪ ጨርሶ ሊሆን አይችልም። ለዚህ ነው በመንጋውና በእረኛው መሃል እጅግ የሰፋ ክፍተት የበዛው፣ ለቤተክርስቲያንም ተግዳሮት የሆነው። “መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።” — ዘካርያስ 11፥17።

እረኛ የደከመን ካላየ፣ የከሳው ካልተመለከተ፣ የተጎዳን ካላበረታ የእረኝነቱ ትርጉም ይጠፋል። በሚገባው መልኩ ካላሰማራና ካልመሰገ የመንጋው ህልውና አደጋ ላይ ይሆናል። “እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም።” — ሕዝቅኤል 34፥5።

የዛሬ እረኛ እራሱን የሚያሰማራ እና የደለበውን ለራስ ጥቅም ከማዋል ባሻገር ለመንጋው ያውም ክርስቶስ ለሞተለት ህዝብ ግድ የሚለው የአደራ ሰው አይደለም፣ ከዚህም የተነሳ ለነጣቂ ተኩላ ተላልፎ በመሰጠቱ ቤተክርስቲያን አደጋ ተጋርጦባት በተግዳሮት ውስጥ ነች። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና”— ሕዝቅኤል 34፥8።

 

 

ባለቤትነትን በትክክል ማወቅ 

ብዙውን ጊዜ በዘመናችን የምንመለከተው መንጋን የመጠበቅና የመንከባከቡ ጉዳይ እጅግ በጣም የደከመ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን በበረቱ ያሉትን ይቅርና አጠገብ በበረት አሉ ተብለው እንኳን የሚታሰቡት በትክክል በእንክብካቤ ሲያዙ አይታይም። መፅሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን አይነግረንም። ጌታ ኢየሱስ ከተናገራቸው አብይ ንግግሮቹ በበረት ያልሆኑ፣ ከበረት ውጭ የሆኑ አሉኝ እያለ ሲናገር እንሰማለን። ስለዚህ በዘመናችን ያለን በእርግጥም በእረኝነት አለን ለምንል ይህ ቃል ሊገባን ይገባል። እረኝነት በእጅ ያለን ብቻ ሳይሆን ከእጅ ውጭ ያሉትንም ጭምር ይመለከታል። እያጎደሉ መሄድ ሳይሆን እየጨመሩ መሄድ ነው። እያጡ ሳይሆን እየተንከባከቡ መያዝና እየበዙ መሄድ ነው። በዚህ ቃል እውነታ ላይ መገአት ይሁንልን። “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” — ዮሐንስ 10፥16። 

ምናምንቴ እረኛ

ምናምንቴነት ከባህሪ ባለፈ በተለይ ከግብር አንፃር እጅግ ጸያፍ የሆነ፣ እምነት የማይጣልበት፣ ለአደራ የማይበቃ፣ ለራስ ጥቅም ብቻ የሚኖርበት አመል ወይም ባህሪ ነው።

ምናምንቴነት እጅግ የወረደ፣ ጸያፍ ባህሪን ያዘለ የውርደትና የውድቀት ጥግ መገለጫና ማሳያ ው። ዛሬም በዘመናችን ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ አገልጋዮች ዘንድ በውልና በግልፅ እየታየ ያለ ነው።

ምናምንቴ ሌላኛው መገለጫው በተለይም የከፋው መለያው እግዚአብሔርን አለማወቁ በተጨማሪም እግዚአብሔርን ጨርሶውኑ የማይፈሩ ደፋርና የመሠላቸውን ከማድረግ የማይመለሱ፣ የእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ቦዘኔዎች (ይቅርታ) ናቸው።

ምናምንቴዎች ለአደራ የማይበቁ ታማኝነት የጎደላቸው ሰዎች ናቸው። በተለይ ጉባኤን የሚያነውሩ እና የሚያስነውሩ ናቸው። “ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።” — 1ኛ ሳሙኤል 2፥22። “ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።” — 1ኛ ሳሙኤል 2፥24። “መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።” — ዘካርያስ 11፥17።

ሰነፍ እረኛ 

 ሰነፍ ለአደራና ለቁምነገር ጨርሶ የሚሆን፣ ሊሆንም የማይችል ነው። ሰነፍ በባህሪው እያወቀ እያወቀ በቸልተኝነት፣   እየገባውም ቢሆን በምን አለብኝነትና በምንአገባኝ የሚንቀሳቀስ ነው። አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን የሚኖር ሲሆን በጥቅሙ ረገድ ግን የራሱን አስጠብቆ የሚኖር ነው። እራሱን ከማሰማራት ወጭ ሌላውን "በለመለመ መስክ" አያውልም አያሰማራም። መንጋውን ተገቢ በሆነ መልኩ አይመስግም፣ ወደየት እንደሚመስግም ጨርሶ አያውቅም። ለሌላው ግን ግድ የሌለው፣ ለስልጣንና ለስም ብቻ ነገሩን፣ ጥቅሙን አስጠብቆ የሚኖር ነው።

ዛሬም በዚህ በድህረ ዘመን በስልጣኔ ሁሉ በረቀቀበት ዘመን ያሉ በስም የተካቡ፣ በስም የተተበተቡ፣ በዝናና በታዋቂነት የተጠነዙ ግን የሚታይ የተገለጠ፣ የሚዳሰስ የተጨበጠ፣ የሚሰማ የሚቀር የማይረሳ ነገር የሌላቸው በበዙበት በዚህ ዘመን ባሉ አገልጋዮች የአህዛብ መሳለቂያ እና መሰደቢያ የሆንነው።

የዛሬ አገልጋይ ስንፍና የማይከሳቸው፣ በሥራ የማያምኑ፣ ግን ጥገኛ ሆነው ተመፅዋች፣ ተሠፋሪ ግን የማይሠፍሩ፣ ሁሌም እንደተሰፈረላቸው የሚኖሩ፣ መንጋን እያከሱ ራሳቸው የሚደልቡ አሁን ግን አይሆንም። ከኃላፊነት መነሳት፣ የሹመቱም ምልክት መገለጫ ይወሰድበታል። የማዘንና የመራራት ልብ የላቸውም። “እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ።” — ዘካርያስ 11፥15።

 ሞያተኛ እረኛ

በእረኝነት ደረጃ ብናየውና ብንመለከተው እረኛ ነው ሆኖም ግን የባለቤትነት ስሜት ጨርሶውኑ የለውም፣ የባለቤቱን ያህል ምንም ነገር አይሰማውም።

ሙያተኛ እረኛ ሊመግብ፣ ሊያበላ፣ ሊያጠጣ ይችላል ከአጥፊ ጠላት ግን አይከላከልም አያስመልጥም፣ አያተርፍም። ለትውልድና ለተተኪ ጨርሶውኑ ግድ የለውም። የኃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት የለውም። ሙያተኛ እረኛ የተሻለ ነገርና ጥቅም ካገኘ ቀድሞ የነበረበትን ለቅቆ ለራሱ ጥቅም የሚበጀው ላይ ለሥራት ትቶ የሚሄድ ነው፣ ሙያተኛ የተቀጣሪ ያህል ስሜት ያለው ነው።ምክንያቱም የባለቤትነት ስሜት የለውምና። ለራሱ የሚፈልገውን ከአጣ ለሌላው ግድ አይለውም። አዛኝ፣ የሚራራ ልብ የላቸውም። ጌታችን ኢየሱስ እንዳደረገው "ነፍሱን ለወዳጆቹ አሳልፎ እንደሰጠ" ይህን አይነት ትልቅ አደራ የለውም። “እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።” — ዮሐንስ 10፥12።

የሚያዝን ልብ

ትክክለኛ እረኛ በባህሪው የሚያዝን ልብ ያለው ነው፣ አይቶ ዝም የሚል አይደለም፣ በስጋም ቢሆን በመንፈሳዊ ነገር ይመግባል፣ ያስተምራል። በአብዛኛው በመንፈሳዊ ነገር መግቦቱ ትልቅ ነው፣ ምክንያቱም የመጣበት አላማ ህዝብን አጠፋበት ከእግዚአብሔር እቅፍ መልሶ ወደ እግዚአብሔር እረኝነት ወደ በረቱ የሚመልስ ነው፣ ለመንጋው ይጨነቃል።

ትክክለኛ እረኛ ልቡ የሚያዝን፣ የትና መች እንደሚያሰማራ እና እንደሚመስግ በትክክል በውል ያውቃል። በቀን ወዴት እንደሚያሰማራ፣ በለሊት ወዴት እንደሚመስግ ያውቃል። እራሱን ለማሰማራት አይጨነቅም፣ አብሮ ግን ወዴት እንደሚሰማራ ያውቃል። ከመንጋው አይርቅም፣ አብሮነቱ የሁልጊዜ ነው። “ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።” — ማርቆስ 6፥34። “እርሱ ግን መልሶ፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት።” — ማርቆስ 6፥37። “ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው።” — ማርቆስ 6፥39።

በባለቤቱ ልክ አደራን መወጣት

ዛሬ በዘመናችን ከምናየው በጥቂቱ ትላንት አንቱ የተባሉ፣ አብረውን ሲያመልኩ እና ሲያገለግሉ የነበሩ ዛሬ ግን በአለም ያሉ በሞት መንገድ በሰፋው እንዳሻቸው እየሆኑ ያሉ፣ ትላንት ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው ዛሬ ግን የአለምን ነገር ጭልጥ ብለው ገብተው የሚጨልጡ፣ እንዲህ የመሆናቸው ዋናው ምክንያት አንድም በሰነፍ እረኛ ሁለትም በሙያተኛ እረኛ ሶስትም በምናምንቴ እረኛ እንደሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም አደራ በሰጠው በክርስቶስ ልክ ካለመወጣት የተነሳና፣ አደራ ሰጪውን ካለመውደድ የተነሳ ነው። የዛሬ ዘመን እረኛ እንኳን ለደካማው ለበረታውም ክርስቲያን መውደቂያ እና አንገት መድፊያ ሆነዋል። “ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው።”— ዮሐንስ 21፥15።

“ደግሞ ሁለተኛ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” — ዮሐንስ 21፥16። “ደግሞ ሁለተኛ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” — ዮሐንስ 21፥16። “መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።” — ዘካርያስ 11፥17።

የተነሱ እረኞች ግን ለኃላፊነት የማይበቁ

ምንም እንኳን እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታ ባይፀፀትም፣ ብዙዎች ግን በመልካም አነሳስ ቢነሱም፣ አገልግሎታቸው ለሁሉም ተደራሽ ቢሆንም አብዛኞቹ አጀማመራቸው ላይ እንደነበረው እያስኬዱ ባይሆንም፣ እንደጀመሩት ሳይሆን የጠፉም እንዳሉ የማይደበቅና የማይካድ የማይታበል ሐቅ ነው።

ብዙዎች በንዋይ መታለል፣ በባለጠግነት ምኞት መዋጥ፣ የትላንት መነሻ ህይወትን ጨርሶ መርሳት፣ በሌሎች ከፍታ ምኞት መታለል ባመጣው ጣጣ የቀድሞን የአገልግሎት ፍቅር ችላ በማለት ከዳር ሳያደርሱ ሩጫቸውን በመንገድ በመሐል ያቆሙ እጅግ አያሌዎች ናቸው። በተለይ በአይን አምሮት ተጠምደው የከበረ አገልግሎታቸውን ወደጎን ያደረጉ ብዙዎች ናቸው። ይማርካሉ ተብለው የታሰቡ ተማርከው የተገኙ የቀሩ ብዙዎች ናቸው። “እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል።” — ዘካርያስ 11፥16።

ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን የሚያውቅ እረኛ

እረኛ ለቅጽበትም ቢሆን እይታው አንድም በመንጋው ሁለትም ለመከላከል በነጣቂ አውሬ ላይ መሆኑ የግድ ነው። በተለይ ቀድሞ ለመከላከል ያመች ዘንድ በርቀትም ቢሆን ያለን ነጣቂን በጥንቃቄ ለመከላከል ያመች ዘንድ የማይዘናጋ ነው። ይህም የመልካም እረኛ መለያ ባህሪውና የተጠያቂነትና የኃላፊነት ስሜት በውስጡ ያለበት የእውነኛ እረኛ ባህሪ ነው።

እውነተኛ እረኛ በቃ መንጋዬ በአውሬ ተወሰደ ብሎ ዝም የሚል አይደለም፣ ተከትሎ የሚያስጥል፣ አስጥሎም የነጠቀውን አውሬ ዳግም ላይመለስ መትቶ ገድሎ ይመለሳል። “ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር።” — 1ኛ ሳሙኤል 17፥34። “በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር።” — 1ኛ ሳሙኤል 17፥35። ለዚህ ነው ዳዊት፦ ይናጠቅ የነበረ፣ ያስጥል የነበረ፣ ያተርፍ የነበረ፣ በላተኛውን ይገድል የነበረ።

ትክክለኛ እረኛ ለወደፊቱም ይጨነቃል

ትክክለኛ እረኛ አደራውን በሰጠው ልክ የሚረዳና መጋቢነቱን በትክክል የሚከውን ነው። ምንም እንኳን አገልግሎቱን እና ሩጫውን ቢጨርስም፣ ለቀጣዩ ትውልድ አደራውን አስቀጥሎና አሸክሞ የሚሄድ የሚሰናበት ነው። በሜዳ በትኖ የሚሄድ አይደለም። አደራን እንደተቀበለ አደራን ሰጥቶ የሚሰናበት ነው። የጀመረውንና የተሰጠውን አደራ በመልካም አጨራረስ የሚያጠናቅቅ ነው። በተለይም እጅግ በማስጠንቀቂያ ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ምን መጠንቀቅ እንዳለባቸው ጭምር በመንገር ይለያል። በተለይ በመካከላቸው ምን እና ማን እንደሚነሳ ጭምር እንዲነቁ አድርጎ ይሰናበታል። የጥንቃቄ አመላካች ሐሳብን ይጠቁማል። “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።” — ሐዋርያት 20፥29-30።

ትክክለኛ እረኛ ለመንጋው ይጨነቃል

 “ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን፦ ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው።” — ሐዋርያት 15፥36። ሐዋርያው ጳውሎስ ካሉት ሐዋሪያት አንድ የሚለይበት ባህሪ በተለይ በአገልግሎቱ አንዴ ወንጌልን የነገራቸውን ሲተው የምናየው አገልጋይ አይደለም። በመጎብኘት ባህሪው የሚለይና የሚታወቅ ነው። አብያተክርስቲያናትን ያጸና የነበረ፣ የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ የሚናገር እንደነበረ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።” — ሐዋርያት 20፥27። “አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።” — ሐዋርያት 15፥41።

ይህ ነው የትክክለኛ መጋቢ ባህሪ፣ ምንም እንኳን አገልግሎቱን፣ ሩጫውን ቢጨርስም ሌሎች እንዲቀጥሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና የቀጣዩን ዘመን አገልግሎት በምን መልኩ መከወን መተግበር እንዳለባቸው ጭምር በአጽንዖት ይነግራቸዋል፣ ያስቀጥላልም። “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” — ሐዋርያት 20፥28።

እነዚህን ወሳኝ ነገሮች ልብ ልንል ይገባል፦ የቤተክርስቲያን መጋቢ ማለት በእግዚአብሔር የተመረጠ፣ የክርስቶስን መንጋ፣ ምእመናንን በመመገብ፣ በመጠበቅ፣ በመምራት እና በመንፈሳዊ ዕውቀት በማነጽ በቤተክርስቲያን ውስጥ ኃላፊነት የሚወጣ መንፈሳዊ መሪ ነው። መጋቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማርና መልካም ምሳሌ በመሆን ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድጉ ይረዳሉ።

ዋና ዋና ተግባራት እና ባህሪያት፡

1- መንጋውን መመገብ፦ የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማርና በመስበክ ምእመናንን በቅዱሳት መጻሕፍት መመገብ።

2- መጠበቅና መምራት፦ መንፈሳዊ ጥበቃ ማድረግ፣ መምከር፣ መገሰጽና ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር መንገድ መምራት።

3- አርአያነት (መልካም እረኛ)፦ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር፣ ትሕትና እና ታማኝነት በማሳየት ለአርአያነት ማብቃት።

4- ባህሪ፦ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3:1-7 ላይ እንደተጠቀሰው የማይነቀፍ፣ በዕውቀት የጎለመሰ፣ አስተዋይ እና ቤተሰቡን በአግባቡ የሚመራ መሆን አለበት።

በአጠቃላይ፣ መጋቢ ማለት የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያንን በማስተዳደርና ምእመናንን በማገልገል ላይ ያለ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርቶችን የሚያሟላ መሪ ነው።

በመጨረሻም፦ ትክክለኛ፣ እውነተኛ፣ መልካም እረኛ ለበጎቹ ድምጹን እንጂ በያዘው በትር ሲመታ አይታይም፣ ባይሆን ሙሴ በበትሩ እንደተጠቀመ ይጠቀምበታል እንጂ መንጋውን መደብደቢያ አሊያም መምቻ አድርጎ አይጠቀምበትም። ግራኙ ናኦድ በደበቃት ሰይፍ ለጠላቱ እንደተጠቀመ የመንጋውን ጠላት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚመታበት ነው።

ሰናይ ዘመን ይሁንልን!

ወንድም በረከት ሱላሞ ሱጌቦ