እግዚአብሔርን መስማት

"ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፤ አስተዋይም ምልካም ምክርን ገንዘቡያደርጋል፡፡" መጽሐፈ ምሳሌ 1፡5

የሰው ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ እስከ ህይወት ፍፃሜው ድረስ አራት የተግባቦት ክህሎቶችን ያልፋል፡፡ አንድ ህፃን ተወልዶ ከእናቱ የሚሰም ሲሆን የሰማውን ከጥቂት የዕድገት ጊዜያቶች በ    ኋላ የሰማውን መልሶ ለመናገር የመጣጣር ሲሆን፤ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ የፊደል ልየታን የንባብ ጊዜን በመማር ቀጣዩን እና የመጨረሻውን ወደ መፃፍ ይሸጋገራል፡፡  

ብዙ ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች መስማት የሚያስፈልገንን ሳይሆን መስማት የምንፈልገውን ብቻ እየመረጠን የምንሰማ ከሆነ እጅግ ከባድ አደጋ አለው። በተለይ በዚህ ዘመን እግዚአብሔር እንዲናገረን የምንሻው በጎ፣ ደስ የሚልን፣ ምቾታችንንና ፍላጎታችን የሚነካውን ብቻ ነው። እግዚአብሔር የፈለገውን የልቡን ሐሳብ በተለይም የግሳጼን ነገር ጨርሶ ልንሰማ አንፈልግም። ስንስትና ስንሳሳት እግዚአብሔር ሊገስጸን ሲፈልግ የማንሰማው ነገር ከእሱ የሚለየን ነገር መሆኑን አለማወቃችን እጅጉን የሚጎዳን ነው። 

እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ የሚናገር ነው፣ የሰው ልጅ ግን እምብዛም ሲሰማውና ሲያደምጠው አይገኝም። መስማት አንደኛው የመግባቢያ መንገድ እንደሆነ ከቁብ አናስገባውም።

በመስማት ውስጥ አንድ የሚተላለፍ ወሳኝ መልዕክት እንዳለው ልናውቅ ይገባል። 

መስማት እግዚአብሔርን ከሚያስደስቱት ነገሮች አንደኛው ነው። እርሱን ስንሰማው ደስታው ነው። እግዚአብሔርን ስንሰማው እጅግ እያስደሰትነው እንደሆነ አለማወቃችን አንዱ ችግራችን ነው። በመስማት እጅግ ብዙ በረከት አለው።

እግዚአብሔር ሁልጊዜ ደስታ ያለበትን ነገር፣ መልካም ዜና፣ የምስራች ይዞልን አይመጣም። እግዚአብሔር ባህሪው ማስደሰት ብቻ አይደለም፣ የሳተ እንዲመለስ ይናገራል፣ ያጠፋን ይገስፃል፣ መስማት ግን የእኛ ትልቁ ምላሽ ነው፣ የዚህን ጊዜ እንዳመለክነው ሊገባንና ልንረዳ ይገባል። ሲገስጽ እንዲህ ይላል፦ የኤፌሶን ቤተክርስቲያንን ሲናገር "ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውን ሥራህን አድርግ" ራእይ 2:5፣ በማለት ይገስፃል። በሌላ መልኩ ደግሞ ለፍላደልፊያ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ይናገራል፦ "እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና" ራእይ 3:8። በማለት ድምጹን ያሰማል።

ምንድ ነው ምንሰማው

  1. የእግዚአብሔርን ሕግ- ሮሜ 2፡13 በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና፡፡
  2. እግዚአብሔርን ቃል- ያዕቆብ 1፡22 ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። 23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ያዕቆብ 1፡23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል
  3. የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ

በክርስትና ሕይወታችን መስማት ማለት፦

  1.  የሚናገረንን እግዚአብሔርን ማምለካችን ነው
  2.  ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠታችን ነው
  3.  እግዚአብሔርን አንተ ልክ ነህ እያልነው ነው

እግዚአብሔር ሲናገረንና ስንሰማው የሚበጀንን እየነገረን ነው፣ ሲገስጸን ደግሞ እየተጣላን አይደለም፣ ያልተደሰተበትን ጉዳይ፣  ያልተመቸውን እየነገረን ነው።

እግዚአብሔርን መስማት በውስጡ በረከቶች አሉት፣ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እና መሠረታዊዎቹን እንመልከት፦

1-መስማት ለበረከት 

ብዙውን በአስተምሮአችን ወይም በስብከታችን መስማት በረከት እንደሆነና እንዳለው ስንነግር አንታይም አንደመጥም። መስማት ግን በረከትን የሚያመጣ፣ የሚያስከትል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሰማን ማለት የቃሉን ባለቤት አከበርነው ማለት ነው። "የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል።" ዘዳግም 28:2

ማስታወሻ፦  ዘዳግም 28:2-14 ያንብቡ

2- አለመስማት መርገምም አለው

መስማትን ብቻ ተናግሮ መተዉ ተገቢ ባይሆንም፣ አለመስማትን መናገር ተገቢ ነው፣ ባለመስማት የሚመጣን ችግር በውል ለማወቅ ይረዳልና። እግዚአብሔርን አለመስማት በራሱ የሚያመጣው ፈርጀ ብዙ አሉታዊ ነገሮች አሉት። አለመስማት ለበረከት ሳይሆን ለእርግማን ከሚዳርጉ ነገሮች አንደኛው ነው። "ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትዕዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።" ዘዳግም 28:15

ማስታወሻ፦  ዘዳግም 2:15 ጀምሮ ያለውን ያንብቡ

3- መስማት ለመረጋጋት

ብዙውን ጊዜ በህይወታችን ውስጥ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣትን እናያለን፣ ይህም ከምን አኳያ መጣ፣ ለምን መጣ፣ በምን ምክንያት መጣ ብለን ሰከን ብለን ስናጤንና ስናጠና አንታይም። የችግሩ መነሻ ምንድነው ብለን ለማወቅ አንነሳም። ለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል አስረግጦ የሚነግረን ቃል አለ፣ የሚናገረንን እግዚአብሔር አለመስማት በተቃራኒው የሚያገኘን የማያረጋጋ ነገር ነው። "የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ስጋት የሠርፋል።" ምሳሌ 1:33

4- መስዋዕት ነው

በመፅሐፍ ቅዱስ መስዋዕት እራሱን የቻለ የአምልኮ አይነት ነው። "...ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና።" መክብብ 5:1። ከአምልኮአችን በፊት የመሚቀድመው እግዚአብሔርን መስማት ነው።

5- እግዚአብሔርን ያስደስተዋል

እግዚአብሔርን ከሚያስደስቱ ነገሮች መካከል አንዱ የራሱን ቃል መስማት ነው። "...በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?..." 1ኛ ሳሙኤል 15:22። ከምንም በላይ ቀዳማይ ነገሩ እግዚአብሔርን መስማት ነው።

የመስማት ትሩፋቶች

  1. መስማት ጥበብን ይጨምራል

ምሳሌ 1፡5 ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። 

   2. መስማት የእምነት ምንጭ ነው

               ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል   ነው።

   3. መስማት ያረጋጋል 

ምሳሌ 1፡32-33 አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ    መሆን ያጠፋቸዋልና። የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።

   4. መስማት በእውነት እንድንሔድ ያደርጋል   

ያለመስማት ውጤቶች

1.   የማይሰማ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት

  ምሳሌ 28፡9 ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።

2.   የማይሰማ የሐሰት ልጅ ይባላል

ትንቢተ ኢሳይያስ 30፡9 ዓመጸኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት  የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና

ስለዚህ ምን እናድርግ?

እግዚአብሔር ስለልጁ ስለክርስቶስ የተናገረውን ብቻ ማድረጉ እጅግ ጠቃሚ ነው፣ ምክንያቱም የክርስትናችን መሠረታዊ ነገር ስለሆነ።

ማቴዎስ እንደፃፈው

1- ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ

"... እነሆም፥ ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ማቴዎስ 17:5

ማርቆስ እንደፃፈው

2- የምወደው ልጄ

"... ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ማርቆስ 9:7

ሉቃስ እንደፃፈው

3- የመረጥሁት ልጄ

"ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ሉቃስ 9:35

እግዚአብሔርን መስማት ይሁንልን!

አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ

+251902910126