
------------------------------------------------------------------------------------------
ትጋት
“ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው”
(ምሳ. 12፥27)።
መግቢያ
በዚህ ዓለም ላይ ፍሬያማ ሠራተኛ ወይም ውጤታም ሠራተኛ የምንለው ሰው ለውጤታማነትና ለፍሬያማ ሠራተኝነት ከሚያበቃው ዋነኛ ነገር አንዱ ትጋት እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ የሚተጉ ሰዎች ዋነኛ መገለጫ ባህሪያቸው ለጊዜ ያላቸው የጠለቀ አመለካከት እና ዋጋ ትጋታቸውን ጨምሮላቸው ውጤታማ መሆነቸው ነው፡፡
የሚተጉ ሰዎች ሌላኛው ባህሪያቸው እጅግ ትዕግሰተኛ መሆናቸውና ሁልጊዜ ላለሙት ግብና ስኬት ዘወትር በትዕግስት እና እጅግ ብልሃት በታከለበት መንገድ ሥራን መከወናቸው ሲሆን ጥረታቸውን ለቅፅበት ያህል አለማቋረጣቸው ለትጋታቸው ግብዓት ሆኖ ተጠቅመው ግባቸው ላይ ይደርሳሉ፡፡
ትጋት ብዙ ጥረትን፤ የጊዜ አጠቃቀምነ፤ ትዕግስተኝነትን፤ መቋቋምን፤ ግብን ዓላማን ውጤትን ትኩረት አድርጎ የሚነሳ የሥራ መከወኛ ኃይል እና ብርታት ነው፡፡ ትጋት የጊዜን አጠቃቀም፤ ለጊዜ ዋጋን የሚሰጥ፤ ጊዜ እንዲባክን የማይፈልግ፤ ከሁሉ በላይ ለስንፍና ቦታ የሌለው አንዳች ኃይል ነው፡፡
ትዕግስት ከሌለ ትጋት የለም፤ ትጋት ከሌለ ስኬት የለም፤ ስኬት ከሌለ ቀጣይ ምዕራፍ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ትዕግስትና ትጋት በእጅጉ ተሰናስለው የሚኖሩ ነገሮች ናቸው፡፡
ትጋት ማለት በግሪክ SPODAZO (ስፓዳዞ) ሲሆን ትርጉሙም ፍጥነትን መጠቀም፣ ጥረት ማድረግ ሲሆን የማይበርድ ጥረት፣ በጽናት የሚደረግ ሥራ፣ በሙሉ ኃይልና ጥንቃቄ የሚደረግ ሥራ ማለት ነው። እንዲሁም የአንድ ሰው ጽናትና ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ጠንካራ፣ ጽናት እና ቀጣይነት ያለው ስራ እንዲያከናውን ያስችለዋል። ትጉ ሰዎች ሥራን የመፈጸም አቅም አላቸው!
በክርስትና እምነት ውስጥ እጅግ የሚፈለግ እና የሚመከር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተደጋግሞ ከተጠቀሱት ቃላቶች አንዱ ትጋት ነው። ይህም የሚያሳየው ትጋት ለሰው ልጅ ምን ያህል ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ ነው። የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊው ሰለሞን ትጋት ለሰው ልጅ የከበረ ሀበት እንደሆነ ይናገራል። “ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው” (ምሳ. 12፥27)።
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ትጋት የተሰጠንን በረከት የምንወርስበት አቅም እና ጉልበት ነው፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላት መሠረት ትጋት መንቃትን፣ ቸል አለማለትን፣ እንዲሁም ሳይታክቱ ያለ እንቅልፍ እና ድካም መጠበቅ ነው። በክርስትና አስተምህሮ ትጉህ መሆን ማለት ለእግዚአብሔር ባለን ቁርጠኝነት ውስጥ ሀላፊነት፤ ዘላቂነት እና ወጥነት ያለው መሆን ነው። በተጨማሪ ትጋት ማለት ሥራ አለመፍታትና ተግባርን እስከ ፍፃሜው ይዞ መዝለቅ ነው።
ትጋት ሁልጊዜ
- ለዓላማ
- ለግብ
- ለውጤት ይጨነቃል
ክርስቲያን፣ አገልጋይና ትጋት
በቤተ ክርስትያን አገልጋይ ሊጠነቀቅና ሊያስብበት ከሚገቡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ትጋቱ ነው፡፡ የማየተጋ አገልጋይ በምንም ተዓምር ፍሬያማና ውጤታማ መሆን አይችልም፡፡ ትጋት የጎደለው አገልጋይ ፍሬያማነቱ አይታይም ቀጣይነቱም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡ አገልጋይ ሁልጊዜ በፍሬ መታየት አለበት፡፡ ውጤታማ ካልሆነ ግን ትጋቱ በጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እራሱ በትጋቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ ለፀሎት ይተጋ ነበር፡፡ የማይተጋ አገልጋይ አገልግሎቱም እራሱም ከአገልግሎት ይቆማሉ፡፡ ወደ ደቀመዛሙርቱም መጣ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፡- እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን ማቴዎስ 26፡40::
ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ራሱ እየተጋ ክርስቲያን፤ አገልጋይ የማይተጋበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ ለክርስትናችንም ይሁን ለአገልግሎታችን ትጋት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ትጋት
1. ትዕግስትን
2. ጊዜን
3. አላማን
4. ግብን አተኩሮ ይንቀሳቀሳል፡፡
የትጋት ባህሪያት
1. የጊዜ ብክንት የለበትም
2. አይዘናጋም
3. ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው
4. ቸልተኝነት አይታይበትም
5. ትኩረቱ ግቡ ላይ ነው
6. ፅናት ይታይበታል
7. ትዕግስት መለያ ባህሪው ነው
በትጋት ምን እናድርግ
1. ስንገዛ በትጋት እንገዛ
ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ ኤፌሶን 6፡7
2. የምናደርገውን በትጋት እናድርግ
ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉ ቆላስይስ 3፡23
3. እስከመጨረሻ መቆየት
…ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን እብራውያን 6፡11-12
4. እናምልክ
…ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርስ ዘንደ አለኝታ አላቸው የሐዋሪያት ሥራ 26፡7
ትጋት ከየት ይመጣል
ትጋ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው፡፡
ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለእናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፡፡ 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡16
የትጋት ጥቅም
1. ራስን/ ለፍስን ለመጠበቅ
ነፍስህን በትጋት ጠብቅ ዘዳግም 4፡9-10
2. ሥራን ለመሥራት
ያም ሥራ በትጋት ይሠራል ዕዝራ 5፡8
ትጋት ለማን ነው
1. ለራስ ነው፡- የሚተጋ ሰው በስንፍና አይታማም፡፡ ምክንያቱም ስንፍና በራሱ ኃጢያት ነው፡፡ የማይተጋ ተቃራኒው ታካች ነው፡፡ ታካችን ስንፍና ይገድለዋል፡፡ እነሆ በባሪያዎቹ አይታመንም መለእክቱንም ስንፍና ይከሳቸዋል፡፡ ኢዮብ 4፡18 ስለዚህ ክስ ካለ ጥፋተኝነት ታይቷል ማለት ነው፡፡ ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም፡፡ ምሳሌ 27፡22::የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል፡፡ መክብብ 10፡1::
2. ለቤተክርስቲያን ነው፡- ቤተክርስቲያን አደገች ስንል ሥራዋን፣ተልዕኮዋን በትጋት እየፈፀመች መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ የምትተጋ ቤተክርስቲያን ዕድገቷ የሚታይ ነው፡፡ የማትተጋ ቤተ ክርስቲያን ባታድግም ባለበት መሄዷ አሊያም ከሌሎች ካደጉ ቤተክርስቲያናት አንፃር ስትታይ ዘገምተኛ ወይም ወደ ኋላ የቀረች ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አደገች ካልን በፀጋ፣ በቃል ሙላት፣ በወንጌል ስርጭት፣ ቤተክርስቲያን ተከላ፣ የሰዎች መዳን ታየ ካልን በስሯ ያሉ አገልጋዮች በትጋት ስራቸውን እየከወኑ ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፡፡2ኛ ጴጥሮስ 1፡5፡፡
3. ለወንጌል ሥራ፡- እርግጥ ነው ጌታ ኢየሱስ በዋናነት የመጣው ለጠፉት፣ ከጌታም በኃጢያ ምክንያት የተለዩትን ለመፈለግና ለማዳን ስለሆነ ጌታ በሰጠን አደራ ልንተጋ ይገባልም የግድም ነው፡፡ ስለዚህ መትጋት የግድ ነው፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ማርቆስ 16፡15፡፡ እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።ሉቃስ 9፡6፡፡እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።የሐዋሪያት ሥራ 8፡25::
ስለዚህ ትጋታችን በምን ላይ ይሁን?
መፅሃፍ ቅዱሰ ሲናገር ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ ለጌታ ተገዙ ሮሜ 12፡11
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትጋት ብቻ ተናግሮ አያበቃም፤ ይልቁንም የምንተጋበትን ጉዳይና በምን መትጋት እንዳለብን ጭምር ይነግረናል። የእግዚአብሔር ቃል በብዙ ቦታ ትጉ ይላል። የምንተጋባቸውን ሲገልፅልን፡-
- በቃል እንትጋ፡- እኛ ግን ለፀሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 6፡4
- በህብረት እንትጋ፡- በሐዋሪያት ትምርና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየፀሎቱም ይተጉ ነበር፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 2፡42፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማሪያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ የሐዋሪት ሥራ 1፡14::
- በሥራ፦ የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። 5 በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። ምሳሌ 10፥4፡፡ የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች።ምሳሌ 13፥4
- በጸሎት፦ እኛ ግን ለፀሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 6፡4
- በአገልግሎት፦ “ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ።” ሮሜ 12፥11፡፡
- በመልካም ሥራ፦ “ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።” 1ኛ ተሰ. 5፥15::
መትጋት ያለብን ለምንድነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የትጋትን አስፈላጊነት በግልጽ እና በአንክሮ ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል መትጋት ያለብንን ሲያስተምረን፦
- ለክርስቶስ ምፅአት ለመዘጋጀት፡- "ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።" ማር. 13፥32-36
- ወደፈተና እንዳንገባ ነው። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።” ማር. 14፥38
- ወደፊት ሊመጣ ካለው፣ከሚመጣው ሁሉ ለማምለጥና በሰው ልጅ ፊት ለመቆም ነው። “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” ሉቃ. 21፥36
- መጠራታችንንና መመረጣችንን ለማጽናት ነው። “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።” 2ኛ ጴጥ. 1፥10
- ለመግዛት ነው። “የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።” ምሳ. 12፥24
- ለባለጠግነት/ ባለጠጋ ለመሆን ነው። “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች።” ምሳሌ 10፥4
የትጋት ጠላት ወይም ፀር
1. መታከት
የታካች እጅ ጭግረኛ ታደርጋለጭ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች ምስሌ 10፡4
2. ስንፍና
ከስንፍናዬ የተነሳ ቁስሌ ሸተተ በሰበሰም መዝሙር 38፡5፡፡ የሰው ስንፍና መንገዱን ታጠምምበታለች ልቡም በእግዚአብሄር ላይ ይቆጣል፡፡ ምሳሌ 19፡3
3. ሥራ ፈትነት
ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣበታለች የታካች ነፍስ ትራባለች፡፡ ምሳሌ 19፡15
4. ዳተኝነት
በእምነትና በትዕግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እሰኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፡፡ ዕብራውያን 6፡11-12፡፡
5. ሥጋ
ወደ ፈተና እዳትገቡ ትጉና ፀልዩ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው፡፡ ማቴዎስ 26፡41
የሚተጉ ሰዎች ምልክት
1. ስለ ጊዜ ጠንቅቀው ያውቃሉ
2. ታጋሾች ናቸው
3. ስንፍና አይታይባቸውም
4. ለዓላማቸው ጨከኞች ናቸው
5. የሚያዘናጉአቸውን አይሰሙም
6. ከአላማቸው ጋር ከሚግባባና ከሚስማማ ጋር አብረው ይሠራሉ፣ ይዘልቃሉ
7. ትኩረታቸው ሥራቸው ላይ ነው
8. ትኩረታቸው ግብ ላይ ነው
9. ለሚቃረኑዋቸው መልሰ አይሰጡም
የሚተጉ ሰዎች ከምንም በላይ ዋጋ የሚሰጡባቸው
1. ለፀሎት ዋጋ ይሰጣሉ
2. ለእግዚአብሔር ቃል ዋጋ ይሰጣሉ
3. ለፀሎት ሰፊ ጊዜ ይሰጣሉ
በመጨረሻም
ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፡፡ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡10::
ተባረኩ
አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ
+25102910126/ +251911835440/ +251916276339
---------------------------------------------------------------------
