የቀደመው ታሪክና ማንነት የተሻረበት፣ ቀድሞ መታወቂያ የነበረው ማንነት ሙሉ በሙሉ የተወገደበት፣ ማዕረግ ያልነበረን ባለማዕረግ የሆንበት፣ ይህም በአንዱ በክርስቶስ በእግዚአብሔር ልጅ ያገኘነው ልጅነት ነው።
ባርነት ያውም የኃጢአት ባሪያ፣ የአለም ባሪያ፣ የስጋችን ፍላጎት ባሪያ፣ የሠይጣን ባሪያ የነበርነውን አሁን ግን በክርስቶስ አርነት ወጥተን ባርነት የተሻረልን፣ ልጅነትን ግን በክርስቶስ በልባችን አምነን በአፋችን መስክረን የተሠጠን ትልቁ ስጦታችን ልጅነት ነው። ይህ ልጅነት ወደ ቤቱ ያስገባን፣ ወራሽም የሆንንበት ነው።
ልጅ የልጅነት ስልጣኑን ይዞ በአባቱ ቤት እንዳሻው፣ እንደ ልቡ ሐሳብ፣ እንደፈለገ የሚመላለሰበት ትልቅ ማዕረግ ነው። በአባቱ ቤት በጽድቅ እና በቅድስና ይወጣል ይገባል። ምክንያቱም ልጅነቱ የአርነት ምልክትና መብቱ ስለሆነ።
ባሪያ ለራሱ ፈቃድ የማይኖር ለገዛው ፈቃድ ብቻ የሚኖር፣ ለራሱ ሐሳብ የማይገዛ ለሚያስተዳድረው ሐሳብ ብቻ ተገዝቶ የሚኖር፣ ለራሱ ጊዜ የሌለው ለገዢው ብቻ ጊዜውን የሠጠ ነው። አርነት፣ ነፃነት የሌለው፣ መብቱ የተገፈፈ፣ እንዳሻው የማይሆ፣ ነጻነት የተነፈገው ነው።
ወደ ገላትያ ሰዎች 4፥7 "ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።"
"ልጅ ነህ!" ይህ የአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ሥራና ትልቁ ስጦታ ነው።
በልጅነት ውስጥ የተቸረን ስጦታ
1- ልጅነት፦ ልጅነት ከአባትነት ጋር ያለን ቁርኝት የሚገልጽ፣ በክርስቶስ ያገኘነው ትልቁ ማዕረጋችን ነው። በነጻነት ልንኖር በክርስቶስ ነጻነትን ያገኘንበት ማዕረግ ነው።
ይህ ልጅነት እንደ ሰው የስጋ ፈቃድ የሚሆን ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ከመባል በላይ ወይም መሆን በላይ የሚበልጥ ነገር ምን አለ? እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ትልቁ ስጦታ ነው።
እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ገላትያ 4:5
ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም ገላትያ 4:7
2- ወራሽነት፦ ወራሽነት ሰው ከመሞቱ በፊት በቁሙ ኑዛዜ አሊያም በሞቱ አቅራቢያ ለሚቀርቡት የሚሰጥ ነፃ ቸርነት ነው። ውርስ አንዳች ከእግዚአብሔር በኑዛዜ የምናገኘው ሳይሆን፣ ከልጁ ከክርስቶስ ቀጥሎ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተሰጠን ቸርነት ነው። ምንም ዋጋ ያልከፈሉበትን፣ ወጪም ያላወጡበትን፣ አንዳች ልፋት ያልተደረገበት ነፃ ስጦታ ነው፣ ወራሽነት። ይሄ የአንተ፣ የአንቺ ተብሎ የተሰጠን ነው። ይህም ወራሽነት በልጁ በክርስቶስ ደም ታትሞ የተሰጠን፣ በበጎ ፈቃዱ የተለገሰ ስጦታ ነው። ይህም በሰማይ ርስት አለን ብለን የምንናገረው፦
2.1. አገር አለን፦ ዜግነት የተቀየረበት፣ ሰማያዊ ነን፦
እግዚአብሔር ከውድ ልጁ ቀጥሎ ከሰጠን ስጦታዎች እና ቸርነት፣ በረከቶች መካከል አንዱ አገራችን በሰማይ እንደሆነ ነው። አገራችን በሰማይ እንጂ በምድር እንዳልሆነ፣ ዘላለማዊነት በአገራችን በሰማይ እንጂ በዚህች ምድር ሁሉ ከንቱ በሆነባት ምድር እንዳልሆነ እግዚአብሔር በቃሉ አስረግጦ የነገረን ሲሆን፣ ይህም አገራችን እርሱ ያለበት እና የሚኖርበት፣ ጌታ ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲያርግ "እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፣ በዚያም ስፍራን አዘጋጅላችኋለሁ ያለበት"፣ ብርሃኑም እርሱ እግዚአብሔር የሆነበት ያ ስፍራ አገራችን ነው።
ይህ አሁን በስጋ የምንኖርበት ጊዜያዊ ሲሆን ይህም መጻተኛ ሆነን የምንኖርበት፣ በሰማይ ግን ለዘላለም የምንኖርበት፣ መጻተኝነት የሌለበት፣ ባይተዋርነት የሌለበት፣ እንደባለ ሙሉ መብት የምንኖርበት ነው። በዚያ ሃዘን የለም፣ ለቅሶ የለም፣ ብቻ በምድር ኖረን ያየናቸውና የምናያቸው ከዚያኛው አገራችን ጋር ጨርሶ አይገናኝም፣ አይስተካከልም፣ ጫፉንም ጥጉንም አይደርስም። ጳውሎስ እንዳለ፦ "እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን" ፊልጵስዩስ 3:20። ይህችም አገር ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ትባላለች። "ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት..." ዕብራውያን 12:22።
ስለዚህ ድንኳን ለሆነው ምድራዊ ህይወት ለጊዜው ከሆነ ተላቅቀን የሰማዩን ህይወት አጽንዖት እንስጥ። "ድንኳን የሚሆነው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።" 2ኛ ቆሮንቶስ 5:1።
2.2. ቤት አለን፦ በሰው እጅ ያልተሰራ፣ ስፍራ መኖሪያ አለ፦ ይህ ነፍሳችን ያለበት ስጋችን በባህሪው ሲሞት መበስበስን የሚያይ አፈር፣ ይህም ያለንበት አለም ቀን የተቀጠረለት ድንኳን፣ የማንቆይበት ግን ለጊዜው የምንኖርበት ሊጠፋ ቀን የተቀጠረለት ነው። በሰማይ ግን አዲሲቱ እየሩሳሌም አለችን። "ድንኳን የሚሆነው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።" 2ኛ ቆሮንቶስ 5:1።
2.3. ዘላለም አለን፦ ሞት የሌለበት፣ ሁልጊዜ ሐሴት ያለበት ህይወት
አይን ከእንባ ታብሶ፣ ሞትም ከእንዲህ የማይሆንበት፣ ኅዘን፣ ጩኸት፣ ስቃይ የሌለበት፣ የቀደመው የምድር ሥርዓት የማይኖርበት ዘላለም አለን። ራእይ 21:4። "... ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።" ገላትያ 4:7
ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ሮሜ 8:17
3- የልጁን መንፈስ ላከ፦ የታተምንበት መንፈስ ነው፣ የማይሻር ምልክታችን ነው።
እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ስሜታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ ኤፌሶን 1:13
ስለዚህ ይህን የታተምንበትን አናሳዝን።
ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ኤፌሶን 4:30
ልጆችም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ገላትያ 4:7
4- ባርነት የተሻረበት፦ ለተገዙበት አሊያም ለተገዙለት እንደ ንብረት የሚያዙበት ወይም በቁጥጥር ስር ለገዢው ፈቃድ ብቻ የሚኖሩበት ህይወት ነው። ነፃ ያልወጣ ገዢው ወይም ጌታው እንደ ፈቀደ የሚያደርገው ነው። ለራሱ ፈቃድ የማይኖር ለገዛው ፈቃድና ስሜት የሚኖር ማለት ነው።
ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም ገላትያ 4:7
5. የልጅነት መንፈስ ተቀበልን፦ የሚያስፈልገንን የምንለምንበት፣ ለልመና ጥሪ የምናቀርብበት መንፈስ ተቀበልን
አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ 8:15
እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሥራ፣ ሞትና ትንሣኤው አማካኝነት ልጁ አድርጎናል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ይህም እምነት የእግዚአብሔር ፈቃድና የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ዮሐንስ ወንጌል 6፡28-29። እንግዲህ በክርስቶስ በማመን ልጆች ከሆንን ምንም ነገር ተመልሶ ወደ ባርነት ሊወስደን አይችልም። ስለዚህ ደስ ይበለን፥ እኛ ከእግዚአብሔር የተወለድን ልጆቹ ነን እንጂ ባሪያዎች አይደለንም።
ልጅ ከሆንን እንግዲህ የእግዚአብሔር ወራሾ ነን። እግዚአብሔር የሰጠውን የሕይወት እና የመለኮት ባህርይ ተካፋይ እና ወራሾች ነን።
ስለዚህ ይህን ኢየሱስን ለመተዋወቅ ይህንን ጸሎት ይጸልዩ "ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ አንተ ስለ እኔ ተሰቅለሃል፣ ሞተሃል፣ ደግሞም ከሙታን ተነስተሃል። ይህንንም በልቤ አምናለሁ፣ በአፌም እመሰክራለሁ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ፣ ደግሞም ጌታ እንደሆንህ አምናለሁ እመሰክራለሁም። አሜን"
ይህ ጸሎት የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎዎታል። እንኳን ወደዚህ ልጅነት እና ሕይወት ተሻገሩ።
እግዚአብሔር ይባርክዎት!
አገልጋይ በረከት ሱላሞ እና አገልጋይ መከተ ሱላሞ