
ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋይ፤ አገልግሎትና አደራ
ቤተ ክርስቲያን ባለቤቷ እግዚአብሔር እንደሆነ በሁሉም ዘንድ እሙንነት እና ተአማኒነት ያለው ሐቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በምድር ላይ ሲተክል የራሱን አላማ፤እቅድና ግብ ኖሮት ሊያሳካ የመሰረታት ናት፡፡ ይህችም ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች እና የተገዛች ነች፡፡
ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ መገኘቷ የእግዚአብሔርን የልቡን አጀንዳ ለማሳካት ሲሆን ለቤተክርስቲያንም የተሰጣት ተልዕኮ የዘላለም አጀንዳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቤተክርስቲያን በምድር መሆኑኣ ለምን ዓላማ እንደሆነ ካልተገነዘበችና ካልተረዳች የእግዚአብሔርን ሃሰብ ልታሳካ ቀርቶ ልትጀምር ትቸገራለች፡፡
ቤተክርስቲያን ስንል በውስጧ የሯሷ የሆነ አደረጃጀትና አወቃቀር ያላት ሲሆን ይህም አደረጃጀት ለቤተክርስቲያን ስራና ተልዕኮ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ አደረጃጀት ውስጥ የስራ ድርሻ እና ተልዕኮ ያነገበና ያዘለ ሲሆን ሁልጊዜም ለዓላማና ለግብ ይተጉበታል፡፡
በተለይ በዋናነት ሊተኮርበት የሚገባ ወሳኝ ነገር የአገልጋይ አቋም እና የስራ ድርሻን በዋናነት ማጤኑ እጅግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ስራ የሚሰራው አንድም በሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሲሆን አንድም በበጎ ፈቃድ አገልጋይ ነው፡፡ ይህም ሲባል በአገልግሎት ላይ ያልተሰማራን ምዕመን አገልጋይን አይመለከትም ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ድብቅና ስውር አገልግሎት የሚያገለግሉ እንዳሉ በእርግጥም የሚታመን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ትልቁን ተልዕኮዋን የምትከውነውና የምታሳካው በተለይም የቤተ ክርስቲያንን አደራና ተልዕኮ በውል በተረዳ እና ባወቀ አገልጋይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሁሉም አገልጋይ ላይባል ይችላል የሚባለው፤ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን አደራና ተልዕኮ በተረዱና ባወቁ ሰዎች ብቻ መከወኑ ስለሚታመን፡፡
በብሉይ ኪዳን እንኳን የአደራነትን ጉዳይ እንዲህ በማለት ሙሴ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ የደነገገው ሕግ አለ፤ ይህም ሕግ በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ላይ መልካም ተግባቦት እንዲኖርና አደራነትን እንዴት ማየት እንዳለባቸው ማሳያውንና ሕጉ ቢጣስ ምን ብያኔ እንደሚበየን ጭምር ደንግጓል፡፡
ሰው በባለንጀራው ዘንድ ብር ወይም ሌላ ነገር እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር ከቤቱም ቢሰረቅ ሌባው ቢገኝ ስለአንድ ሁለት ይከፍላል፡፡ ዘፀአት 22፡7
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን እና አደራዋን በታማኝና ቅን በሆኑ አገልጋዮችዋ ብቻ ነው ማሳካት የምትችለው፡፡ ስለነዚህ አገልጋዮች በአብነት ማንሳት የምንችለውን ከእግዚአብሔር ቃል ማትና መማር የምንችለው፡፡
የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውን ያደረገ ጥቂት ይገረፋል፡፡ ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙም አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል፡፡ ሉቃስ 12፡47-48
አገልጋይ የእግዚአብሔርን ሃሳብና የቤተ ክርስቲያንን አደራና ተልዕኮ በውል ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ ለዚህ ነው መፅሐፍ ቅዱሳችን የጌታ ኢየሱስን እና የጴጥሮስን ንግግር እንድንረዳ የግድ ብሎ የሚነግረን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአገልጎዮችዋ በኩል የማሰማራት፤የመጠበቅ ግዴታ አለባት፡፡
ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። 16ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። 17ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ። የዮሐንስ ወንጌል 21፡15-17
አገልጋይና አደራ
አገልጋይ አደራ የተሰጠው ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፤ የቤተ ክርስቲያን ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ አገልጋይ የተሰጠውን አደራ መጠበቅ አለበት፡፡ ለዚህም ነው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አደራውን እንዲጠብቅ የግድ የሚለው፤ ምክንያቱም ወንጌል ባለአደራን እያነቁ እያስጠነቀቁ የሚቀጥሉበት እምነት ነው፡፡
ጢሞቴዎስ ሆይ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡18
መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14
አገልጋይና ታማኝነት
ቤተ ክርስቲያን አደራን ለሁሉም ሰዎች አንስታ የምትሰጠው አይደለም፡፡ በዋናነት አገልጋዩ ለአደራነት የሚበቃና ቁመናውም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ማጤን አለባት፡፡ በተለይም ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ወንጌልን በማዳረስ ደረጃ የተጠመደች መሆኑዋን የምታጤን ሲሆን ለዚህም ይሆኑኛል የምትላቸውን በትኩረት በማጤንና በማሰማራት መስራት እንዳለባት የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ እንደሚነግረንና ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያመላክተን፡፡
ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡2
አገልጋይ፤ ሥራ እና አገልግሎት
እነዚህ አቢይ ጉዳዮች ተነጣጥለው የማይታዩ ወሳኝ ጉዳዮች ሲሆኑ አገልጋይ ካለ ስራና አገልግሎት፤ ሥራ ካለ አገልጋይና አገልግሎት፤ አገልግሎት ካለ ሥራና አገልጋይ እንዳለ የታወቀ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን ማድረግ እንዳለበት ምክር ጭምር በማስቀመጥ ስለ ሥራና ስለ አገልግሎት አፅንኦት በመስጠት የነገረው፡፡
አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም፡፡2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡5
በመጨረሻም
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነውን አደራ ከግብ ለማድረስ እጅጉን መትጋትና መመበርታት እነዳለብን የግድ ነው፡፡ ወንጌልን ለዓለም ማድረስ አደራ ጭምር የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ የራስን የግል ክርስትናችንን ሳንዘነጋ፤ በግል የሚጠበቅብንን ለቅፅበት ቸል ሳንል፤ ሩጫችንን እየሮጥን አገልግሎታችንን እንፈፅም፡፡
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈፅም ዘንድ ነፍሴ በእኔ ዘንደ እነደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቅጥራለሁ፡፡
የሐዋሪያት ሥራ 20፡24