Home/መነሻ ገጽ
መሰረተ እምነት (2)
- Details
- Written by: Bereket Sulamo
- Category: ነገረ ድነት/ Salvation
መሰረተ እምነት
መሠረታዊ ጉዳዮች
በሕይወት ውስጥ ልንሰራቸው፣ ልንከውናቸው የሚገቡ እጅግ ብዙ ጉዳዮች አሉን። በሥራ ጉዳይ ይሁን፣ በሕይወት እንቅስቃሴያችን ይሁን፣ በሐይማኖታዊ ጉዳይ ይሁን ሁሉም ነገሮች ሊከወኑ የሚችሉትና የሚገባቸው ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ብቻ ነው ሊከወኑ የሚችሉት እና ተሳክተው ለግብ የሚደርሱት።
ብዙውን ጊዜ እኛ ሰዎች ነገሮችን መከወን የምንፈልገው መሠረታዊውን ነገር ወደ ጎን በማድረግና ገሸሽ በማድረግ ነው፣ ይህ ግን ተገቢ ያልሆነ ከእውነታው እጅግ ያፈነገጠ መረዳት ነው።
እኛ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነትና መስተጋብር፣ በቤተክርስቲያን የምናደርጋቸው ማንኛውም እንቅስቃሴ በተለይ አገለግሎት መሠረታዊውን ነገሮች ከእውነታው ነጥለን የምንከውናቸው ከንቱ ልፋቶች ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም ከሰዎች ጋር ያለን ቁርኝትና ተግባቦት በነዚህ መሠረታዊ ነገሮች የተዋዛ እና የተከሸነ አይደለም። ከዚህም የተነሳ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እያገኘንበት አይደለም።
እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች እጅግ ቀልለውብን በመገኘታቸው ዋጋ አንሰጥም፣ ዋጋም አለመስጠት ተላምደነዋል። እነዚህንም ነገሮች ከግምት አለማስገባት "ታናሽ ነገር መስሎናል" ይህንንም በማድረጋችን "እግዚአብሔርን የሚያስቆጣውን ነገር እያበዛን" ነን።
መሠረት ሳይኖረው የቆመ ሕንፃ የለም፣ ስር ሳይሰድድ የቆመ ዛፍ የለም፣ ሳይማር የተፈተነ ተማሪም እንደሌለ መረዳቱ ተገቢ ነው። መሠረታዊ ነገሮች ይቅደሙና በተገቢው ክርስትና እንኑረው፣ ጌታችንን ክርስቶስንም እናገልግለው።
እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች መከተላችን በሕይወታችን ከንቱነት እንዳይኖረን ያደርጋል።
መሠረታዊ ጉዳዮችም
1) ፍቅር
በህይወታችንና በአገልግሎታችን እጅግ የዘነጋነውና የከሰርነበት ትልቁ ጉዳይ ቢኖር ፍቅር ነው። “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”— 1ኛ ዮሐንስ 4፥8። ፍቅር በማጣታችን ነገሮቻችን ውበት አጡ፣ በሌሎችም ዘንድ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይና ደቀመዝሙር መሆናችን አልታወቀም፣ ይልቁኑ በነቀፌታ ታጀበ፣ ከሁሉ በላይ መገለጫችን የሆነውን ፍቅር ትተናል። ከአመፃም ብዛት የብዙዎቻችን ፍቅር ቀዝቅዟል፣ ይህም ከአመፀኞች ጋር መተባበራችን፣ አመፀኛም መሆናችን በእኛ ዘንድ ፍቅር ቀዘቀዘ። ፍቅር በእኛ ዘንድ መኖሩ ምንም እንኳን በእኛ ቢገለጥም በዋናነት ክርስቶስን ማሳያ ነው። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” — ዮሐንስ 13፥35። ፍቅርን አጣን እግዚአብሔርን አጣን።
በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች በሌሎች ዘንድ መታወቂያችን የሆነው አመፀኝነታችን እና ፀበኞች መሆናችን አንዱ የአንዱን ጥል በማግነን ክርክርን ማንሳት እንጂ አንዱን በፍቅር የመያዝና ኃጢአትን የመክደን ልማዱ የለንም። በፍቅርም የተቃኘን አይደለንም። “ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች።” — ምሳሌ 10፥12። “ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል።”— ምሳሌ 17፥9።
ሌላኛው ባህሪያችን በተለይ ወረተኛ የሆን እንቅስቃሴ ያችን እና ድርጊታችን ነው። "የአፋችን ቃልና የልባችን ሃሳብ" አንድ አለመሆን እና ያማረ አለመሆን" በሌሎች በሚሰሙንና በሚያዩን ዘንድ እጅግ ወረተኞች መሆናችንን ያሳብቅብናል።“ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው።” — ምሳሌ 26፥23።
ፍቅር የህብረት አንድነት መግመጃው እና ማሠሪያው መሆኑ በአብዛኞቻችን ዘንድ መዘንጋቱ በጠላትነት መፈራሩጁን እና መለያየቱን አስፍቶ አባብሶታል። ጠብ ይዞ ሥጋ መብላቱን ተያይዘን ተክነንበታል፣ ፍቅሩ ኖሮ በሠላም ጎመን መብላቱ እንዴት እርካታና ሠላም በሆነልን። የሁሉ ማሠሪያ ነበር።
አገልግሎት
ምንም ያህል ጫፍ የወጣ ሰማይን የጫረ አገልግሎት እንኳ ቢኖረኝ፣ በሰዎች ዘንድ አንቱታን እና እውቅና ቢኖረኝ መሠረታዊ የሆነውን ፍቅር ባይኖረኝ ከልፋት ያለፈ ድካም ቢኖረውም ከንቱ ነኝ። መለኮትም ይህን አይቀበለውም። “ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።” — 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥2።
ሕይወት
በማህበራዊ ሕይወታችን በሰዎች ዘንድ ባለን ቸርነትና በጎነት ይሁን ደግነት የገነነ ዕውቅናና ስም ቢኖረን መሠረታዊ የሆነውን ፍቅር ባይኖረን የምናደርገው ቅን ነገር ሁሉ ምንም አይጠቅምም። “ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥3።
ስለዚህ ከሁሉ የሚበልጠውን ጸንቶ የሚኖረውን ፍቅር መያዝ ይሁንልን። “እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” — 1ኛ ቆሮንቶስ 13፥13። “ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።” — 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥1። “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 16፥14።
ስለዚህ፦ “እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።” — 2ኛ ዮሐንስ 1፥6። “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” — ይሁዳ 1፥21።
2) ቅድስና
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ከሚነግረንና ከሚያስተምረን ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ቅድስና ነው። ምክንያቱም ቅድስና የእግዚአብሔር መገለጫው ባህሪውና ማንነቱ ኑሮውም ጭምር ነው። “በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅድስና ትኖራለህ።”— መዝሙር 22፥3።
እግዚአብሔር ከእኛ ከክርስቲያኖች የሚፈልገው፣ እንድንሆንለት የሚሻው፣ እንድናደርገውም በጽኑ የሚፈልገው አብይ ጉዳይ ቅድስና ነው። ምክንያቱም ቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር አግባብቶን እንድንኖር የሚያደርገን አንዱ የክርስትና ዘይቤ ነው።
ብዙውን ጊዜ በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ የተዘነጋ እና ጨርሶ በሰው አእምሮ ውስጥ የሌለና የተረሳው ነገር ቢኖር የተጠራንበት የቅድስና ጉዳይ ነው። ይህም ቅድስና ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ ጨርሶ ጠፍቶብናል። “ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።”
— 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥7።
በብሉይ ኪዳን ሌዋውያን በቤተመቅደስ በነበራቸው አገልግሎት አስቀድመው የቅድስናን ጉዳይ አንስተው እርግጠኛ እና ንፁህ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ አገልግሎታቸውን ይጀምራሉ፣ ይፈፅማሉ። ሌዋውያን የቅድስናን ጉዳይ በቀላሉ የሚያዩት አይደለም፣ እጅግ የህይወታቸው እና የአገልግሎታቸው አካልና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በቅድስናው ስፍራ ማንም መቆምና መገኘት እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ነው ንጉሥ ዳዊት ይህንን በመረዳቱ በእግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? ምን መተማመኛ ያለው ነው የሚደፍር፣ ይህ ገብቶት እንዲህ አለ፦ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል?” — መዝሙር 24፥3። ይህንንም ብቻ አይደለም ያለው፣ የአካላዊ ነገርንም አንስቶ ተናግሯል። ሁለንተናችን ለእግዚአብሔር የነጹ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለብን ጭምር ገብቶታል። “እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።” — መዝሙር 24፥4።
በኦሪት ዘመን በነበረው የቤተመቅደስ አገልግሎት የሚፈፅሙ ከአልባሳት ጀምሮ ምን መደረግ እንዳለበት ተደንግጎ የተነገራቸው። በተለይ በዋናነት ትኩረታቸው መሆን ያለበትን የቅድስና ጉዳይ ሁሉ እንዲያየውና እንዲመለከተው "ቅድስና ለእግዚአብሔር" የሚለው በግንባራቸው እንዲደረግ ተደንግጓል። “ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ።” — ዘጸአት 28፥36።
“በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን።”— ዘጸአት 28፥38።
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት።” — ዘጸአት 39፥30።
እርግጥ ሁላችን መፅሐፍ ቅዱስ እንደሚለን በሁሉም ዘንድ እንዲታይ፣ እንዲታወቅ ቅድስና መታወቂያችን ነውን?
ቅድስና ቦታ አይመርጥም
1- ዮሴፍ
በኃጢአት ግብዣ ላይ የጨከነ፣ ወደ እርሱ ኃጢአት ሲመጣ የሸሸ፦ “ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች፦ ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።” — ዘፍጥረት 39፥7። “እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት፦ እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤” — ዘፍጥረት 39፥8። “ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” — ዘፍጥረት 39፥9።
2- ዳንኤል
ለቀረበለት ግብዣ ለሆዱ እምቢ ያለ፣ ከእምነቱ ውጪ በሆነ አመጋገብ ላለመርከስ የተጠነቀቀ እና እምቢ ያለ፦ “ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ፤ እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ።” — ዳንኤል 1፥8።
3- ዳዊት
ባየው ነገር ተወስዶ ልቡን ባለመጠበቁ የሌላውን ኪዳን ያስጣሰ፦ “እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች።” — 2ኛ ሳሙኤል 11፥2። “ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም፦ ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ።” — 2ኛ ሳሙኤል 11፥3። “ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች።” — 2ኛ ሳሙኤል 11፥4።
4- ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ ከብደናጎ
ከእግዚአብሔር ሊለያቸው ከመጣ አስገዳጅ ነገር ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡ፣ ለምስሉ ስገድ ለሚል አሻፈረኝ ባዮች፦ “ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።” — ዳንኤል 3፥18።
5- ሳምሶን
ቅድስናን ቀዳሚ ያላደረገ ሶምሶን ይልቁኑ ወደ ኃጢአት የተጓዘ፣ የቤተሰቡን ምክር ያልሰማ፦ “ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ።” — መሳፍንት 14፥1።“ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ፦ በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው።” — መሳፍንት 14፥2። “አባቱና እናቱም፦ ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን፦ ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው።”— መሳፍንት 14፥3።
ስለዚህ፦ “ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።”— 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥7። “ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።”— 1ኛ ተሰሎንቄ 3፥12-13።
3) ይቅርታ
በተለይ በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን እናውቃለን የምንል ክርስቲያኖች ከይቅርታ አኳያ እራሳችንን ስንመለከተው እናውቀዋለን የምንለውን እግዚአብሔርን ጨርሶ ከናውቀውም። እኛ እግዚአብሔር ምሮን "ቸርነትህና ምህረትህ በህይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል" እያልን የምንኖር ከጥቅማችን አንፃር እንጂ በተዋረድ ለሌሎች ምህረትን በማድረግ አንታወቅም። ትልቁ ጉድለታችንና ኪሳራችን ይህ ነው።
በይቅርታና በምህረት ላይ ያለን አመለካከት እጅግ ደካማ እና ተግባራዊ የምህረትና የይቅርታ ጉዳይ ግን የባሰ የወረደ ነው። ብዙውን ጊዜ ይቅርታ ከማድረግ "ኧረ ሲኦል ብገባ" እያሉ መወራረዱ ምን ያህል ህይወታችን እና ክርስትናችን መውረዱን ማሳያ ነው።
ይቅርታን እና ምህረትን ማድረግ ጥቅማችን እንደሆነ ጨርሶ አንረዳም። ባይሆን ይቅርታና ምህረት ማድረግ ምህረትና ይቅርታ የተደረገለት ክርስቲያን መለያ ነው። ይቅርታና ምህረት የማያደርግ እራሱን በዘላለም ጥፋት ውስጥ እራሱን ማስቀመጥ ነው፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ህብረት የለውም። “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።” — ማቴዎስ 18፥35። “እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” — ማርቆስ 11፥26።
ይቅርታና ምህረት ማድረግ የዘላለም ህይወት አጀንዳ ያለበት እውነታና የእግዚአብሔር ዕቅዱም የልቡም ሃሳብ ነው። “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤” — ማቴዎስ 6፥14። “ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።”— ማቴዎስ 6፥15።
ስለዚህ፦ “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።” — ኤፌሶን 4፥32።
በመጨረሻም፦
“ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።” — ዕብራውያን 2፥1።
እግዚአብሔር ይባርካችሁ!
ወንድም በረከት ሱላሞ ሱጌቦ
የተፅእኖ ሰው
- Details
- Written by: BEREKET SULAMO SUGEBO
- Category: The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
የተፅእኖ ሰው
እነርሱ በእምነት መንግስታትን ድል ነሡ ጽድቅን አደረጉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ
ዕብራውያን 11፡33
በምድራችን ላይ በየትኛውም ዘመን በታሪክ መዛግብት እና በአፈ ታሪክ እንደሚነገረን፣ ከኖርንባቸው ዘመናት ቀድመው የኖሩ በፍልስፍናቸው አመለካከት ይሁን፣ በÞለቲካ አመለካከታቸውና ፍልስፍናቸው ይሁን፣ በፈጠራ ሥራና ግኝት ልህቀት ይሁን፣ ብቻ በተሰማሩበት በየትኛውም ዘርፍ ተፅዕኖን ፈጥረው ለዓለም የሚጠቅም አዎንታዊ ይሁን፣ የማይጠቅም አሉታዊ ጉዳይ ይሁን ሰርተው አልፈዋል፣ አንቱታንም ተችረው፣ ተሞግሰው ለበጎ ነገር ይሁን ለዕኩይ አንድ አሻራ ጥለው አልፈዋል፡፡
በክርስቶስ የተገኘ ልጅነት እና ትሩፋቶቹ
- Details
- Written by: Mekete Sugebo
- Category: The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
የቀደመው ታሪክና ማንነት የተሻረበት፣ ቀድሞ መታወቂያ የነበረው ማንነት ሙሉ በሙሉ የተወገደበት፣ ማዕረግ ያልነበረን ባለማዕረግ የሆንበት፣ ይህም በአንዱ በክርስቶስ በእግዚአብሔር ልጅ ያገኘነው ልጅነት ነው።
የምትሰማው ድምጽ
- Details
- Written by: Mekete Sugebo
- Category: The Feast of the Word/ከቃሉ ማዕድ
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 17
አሰላለፍሀን ቀይር፣
ፍልስጤም እንደ ተሰለፈ አትሰለፍ፣ ፍልስጤም እንደ ተከማቸ አትከማች፤
Page 1 of 5