ሥራ ፈት አንሁን
ሥራ ፈትነት ከምሁራን አንደበት
ሥራ ፈትነትን ከማብራራት አስቀድሜ ነገሬን በዚህ ሥራ በሚለው ጉዳይ ላይ አንድ ምሁር የተናገሩትን ትንሽ ቁም ነገር አዘል ጉዳይ ጠቆም ላድርግና ወደ ተነሳሁበት ሃሳብ ትንሽ ቆየት ብዬ ልመለስ፡፡ ይህ ምሁር ቮልቴር የሚባል ፈረንሳዊ ሊቅና ፈላስፋ ሲሆን ስለ ሥራ የተናገረውን ላንሳ፡- ቮልቴር ሲናገርሥራ ከሶስት ነገሮች የሰውን ልጅ ይጠብቃል ብሎ ይናገራል፡፡
- ከድባቴ ወይም ከድብርት
- ከመጥፎ እኩይ ተጋባርና ድርጊት
- ከድህነት፤ ከችግር ይጠብቃል ይከላከላል በማለት ሙያዊ ምክሩን ይሰጣል፡፡
እውነታው ላይ ተመርኩዘን ስናየውና ስናጤነው ቮልቴር የተናገረው እጅገ እውነት ነው፡፡ በምድራችን አሁን ላይ የምናየው የስራ ፈትነት ካመጣቸው አሉታዊ ችግሮች በይበልጥ ተስተውለው የሚታዩት እነዚህ ናቸው፡፡
ዛሬም በቤተክርስቲያን ውስጥ ከዚህ የተለየ ችግር እያየን አይደለም፡፡ ጉዳዩ የአለማዊ ዕውቀት እና የመንፈሳዊ እውቀት ብለን እንፈርጀው እንጂ በስው ልጅ ላይ እየታየ ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ላይ መንግስታትን እያሳሰበ እና እየተፈታተን ያለው ነገር ቢኖር የሥራ ፈት ቁጥር ማሸቀቡና ለዚህም መፍትሄ ማጣቱ ነው፡፡
ሥራ ፈትነት በአንድ በሀገር ውስጥ ቁጥሩ አሻቀበ ማለት በነዚህ ሥራ በፈቱት በኩል የሚመጣው ችግር ለሀገር ጥልቅ ችግርና ጠንቅ ይዞ ይመጣል፡፡ በተለይም ለሀገር በተቃራኒ ጎራ ለተቀመጠ እጅግ ምቹ መንገድ ይሆናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም ከዚህ የተለየ አይሆንም፤ ልዩነቱ መንፈሳዊነቱ ካልሆነ በስተቀር፡፡
እንደው አንድ መጣጥፍ ሳነብብ ያገኘሁትንና የቃረምኩትን ላውጋችሁ፡ ክፋትና እና ምቀኝነት የስራ ፈቶች ባህሪ ነው። እርሻ ላይ ተጠምደው የሚውሉ በሬዎች ለመዋጋት ጊዜ እንደማይኖራቸው የሰው ልጅም በስራ ውስጥ ሲገኝ እንኳን ሰው ላይ መልካም ያልሆነ ነገር ሊያስብ ቀርቶ ራሱን አረጋግቶ እረፍት የሚወስድበት ጊዜ እንኳን ላይኖረው ይችላል። ስለዚህም እነዚህን መጥፎ ባህሪያት በሰዎችም ውስጥ ይሁን በራሳችን ውስጥ ስናይ ስራ-ፈት እየሆን ነውና እንንቃ።
ሥራ ፈትቶች በጣም ከሚለዩባቸው መለያ ባህሪያት መካከል አንደኛው ልክ የሌለው ስንፍናቸው ነው፡፡
ሥራ ፈትነት ከመፅሐፍ ቅዱስ አንፃር
የእግዚአብሔር ቃል ሥራ ፈትነትን እጅግ አድርጎ ይቃወማል፤ ይጼፋል፡፡ ሥራ ፈትቶችንም እጅግ አድርጎ ይቃወማል፡፡ በተለይ ጳውሎስ እጅግ አድርጎ በመቃወም እንደ ትዕዛዝ አድርጎ ለተሰሎንቄ ሰዎች ደንግጓል፡፡ ደግሞም ከእናንተ ጋር፡- ሊሰራ የማይወድ አይብላ ብለን አዝዘናችሁ ነበርና፡፡ 2ኛ ተሰሎንቄ 3፡10፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያን እየታየ ያለው ቅጥ ያጣ ሥራ ፈትነት፣ እግዚአብሔር አሁን አጀንዳው ያልሆነ ነገር በመስራት፣ ከእግዚአብሔር ፍላጎት ሳይሆን ከራስ በመነጨ ሥራ ላይ ተጠምደን እንገኛለን፤ የራሰችንን ሥራ እንጂ የእግዚአብሔርን ሥራ ስንሰራ አንገኝም፤ ይህም ከሥራ ፈትነት ተለይቶ ሊታይ የማይችል ነገር ነው፡፡
ሥራና ጌታ ኢየሱስ
ጌታ ኢየሱስ ወደ እዚህች ምድር ሲመጣ የአባቱን ፈቃድ ሊያደርግ እንደመጣ እርሱ እራሱ በቃሉ ሲናገር እናነባለን፡፡ እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ… የዮሃንስ ወንጌል 17፡4፡፡ በተጨማሪም እኔ ግን ከየሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈፅመው የሰጠኝ ሥራ፤ አብ እንደላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡ ዮሐንስ 5፡36፡፡
ጊዜ፤ ሥራና ጌታ ኢየሱስ
ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሥራ ከተናገረው በተጨማሪ ጊዜ ላይ አፅንኦት በመስጠት የተናገረውን በመፅሃፍ ቅዱሳችን እናገኛለን፡፡ ከዚህም ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ ላይ ያለውን ንግግሩን መረዳት ይቻላል፡፡ ስለ ቀንና ሌሊት የተናገራቸውን ልናጤነው ይገባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡ ዮሐናስ 9፡4፡፡
ጳውሎስና ሥራ
ከሐዋሪያት መካከል በተለይ ጳውሎስ ስለ ስራ ያለውን አመለካከት ስንመለከት በተለይ ለሌሎች በሚመክረው ንግግሩ የሥራን ነገር መረዳት እንችላለን፡፡ በተለይም ለጢሞቴዎስ ሲመክረው የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ በማለት ምክሩን ሲለግሰው እናነባለን፡፡ አንተ ግን ነገርን በልክ አድርግ መከራን ተቀበል የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን ፈጽም፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡5 በማለት ምክሩን ከጥንቃቄ ጋር እንዲያደርግ ይመክረዋል፡፡
በዚህ ብቻ አላበቃም አክሪጳንም ሲመክረው እንመለከታለን፡- ለአክሪጳም፡- በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈፅመው ተጠንቀቅ በሉልኝ፡፡ ቆላስይስ 4፡17 በማለት ሥራ ፈትንት እንዳይኖር ያስጠነቅቀዋል፡፡
ጴጥሮስና ሥራ ፈትነት
ጴጥሮስ በተለይ ሥራ ፈትነት ከምን አኳያ እንደሚመጣ እና እንደሚከሰት ጭምር በመግለፅ ይናገራል፡፡ በተለይ ሥራ ፈትንትን የሚያመጡ ነገሮችን በመጠቆም ይህ ነገር ባይሆን በእናንተ ዘንድ ሥራ ፈትነት ጨርሶ እንደማይታይ በአንክሮ ይነግራቸዋል፡፡ ስለዚህ በእኛም ሕይወት ጴጥሮስ የጠቆማቸውን፤ ከእኛም ሊጎድሉ እንደማይገባ ማወቅ አለብን፡፡ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና… 2ኛ ጴጥሮስ 1፡8፡፡
ንጉስ ዳዊትና ሥራ
በተለይ ዳዊት የስራን ነገር በእጅጉ የሚያውቅ ንጉስ ነው፡፡ በተለይ ዘመኑን በሙሉ ለእግዚአብሔር ሥራ የኖረ ንጉስ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሥራ እግዚአብሔር ድልንና መከናወንን የሰጠው ንጉስ ነው፡፡ ሥራ ማለት ከንጉስ ዳዊት ህይወት የምንማረው እንዳለና በዘመኑም አንድ ጊዜ ሥራ በመፍታት በእግዚአብሔር ፊት የከፋ ሁለት ኃጢአትን ሰርቷል፡፡ ኦርዮንን ከውጊያ አውድ ከሥራ ላይ በማምጣትና ሥራ በማስፈታት ወደ ከፋ ችግር ሲመራው እናያለን፤ በውጊያ አውድም ሳይገኝ በመቅረቱ የኦርዮንን ሚስት ወሰደ ከእርሷም ጋርተኛ የከፋ ችግር ደረሰበት፡፡ ነገስታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን አስራኤልንም ሁሉ ሰደደ፡፡ የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፤ ረባትንም ከበቡ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፡፡ እንዲህም ሆነ ወደ ማታም ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሳ በንጉሱም ቤት በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች፡፡ ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱም ጠየቀ አንድ ሰውም ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ:: ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት ወደ እርሱም ገባች ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ ወደ ቤትዋም ተመለሰች፡፡ ሴቲቱም አረገዘች ወደ ዳዊትም አርግዣለሁ ብላ ላከች፡፡2ኘ ሳሙኤል 11፡1-5፡፡ በውጊያ ሰዓት በስራ ቦታ አለመሆኑ ለከፋ ችግር ዳዊት ተዳረገ፡፡ በሥራ ሰዓት በሥራ ቦታ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ስህተት ይስራ እንጂ ምልስ ልብ ስለነበረው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ንስሃን አድረጓል፡፡ ከዚህ ስህተቱ በመለስ ዳዊት እጅግ መልካም ስራዎችን አከናውኗል፡፡ የእግዚአብሔር ቤት እንዲሰራ ልቡን አነሳስቷል፤ ሆኖም ግን ቤትን ባይሰራም ለልጁ ለሰለሞን የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዲሰራ አስፈላጊውን ሁሉ ነገር አሟልቶ ለልጁ ለሰለሞን ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን በማቅረብና ሰለሞን ከእግዚአብሔር ሕግ ውልፍ እንዳይል ጭምር ምክር አዘል ሃሳቡን ለግሶታል፡፡ ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ… የሓዋሪያት ሥራ 13፡36፡፡
ሥራ ሁልጊዜ ይብዛልን
እኛ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ፊት በቤተ ክርስቲያን ስንመላለስ በምንም መልኩ ይሁን በእኛ ዘንድ ምንም አይነት ሥራ ፈትነት ሊኖር አይገባም፡፡ ሥራም ሊያንስ ተገቢ አይደለም፡፡ ጳውሎስ እጅግ ትልቅ ምክሩ በማንመ ዘንድ ሥራ ፈትነት እንዲታይ የማይፈልግ ሐዋሪያ ነው፡፡ ለቆረቶንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲመክር፡- ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ የማትነቃነቁም የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ፡፡ 1ኛ ቆሮነቶስ 15፡58፡፡
ሥራና ተቃዋሚ
በተለይ በስራ አለም ላይ ደጋፊ የመኖሩ ያህል ተቃዋሚ መኖሩ ሊታሰብበት የሚገባ እውነታ አዘል ሓቅ ነው፡፡ በሥራ አለም ሥራችን የሚደግፉ እንደመኖራቸው ሥራችን የሚያበሳጫቸው አሉ፡፡ አንድም ቅናት አንድም ምቀኝነት ሊሆን ይችላል፡፡ ጳውሎስ ለዚህ ነው ለሌሎችም ጭምር ይህን እውነታ እንዲረዱና እንዲያውቁ የሚመክረው፡፡ በወገኖች መገፋትም እንደደረሰበት ጭምር ይናገራል፡፡ የብዛታቸውንም ልክ እንድናውቅ ያስጠነቅቀናል፡፡ ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተረከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 16፡9፡፡
ሥራ ተጀምሮ አያፈገፍጉም
ጌታ ኢየሱስ ስለ ሥራ እጅግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለ ሥራ በተለይ በምሳሌ አድርጎ ያስተምረናል፡፡ ኢየሱስ ግን፡- ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግስት የተገባ አይደለም አለው፡፡ ሉቃስ 9፡62፡፡ እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው። ሉቃስ 9፡ 58-62፡፡
ሥራና ለሥራ ራስን መለየት
እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ሥራና ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ የተለየን ነን፤ ማንም ያለስራ ሊቀመጥ አይገባም፤ ሁሉም ሠራተኛ ነው፡፡ ማንም ሠራ አልባ ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም፡፡ ሥራ መስራታችን ለእግዚአብር ምላሽ ባይሆንም ሥራ የተሠራለት ፈጽሞ ሥራ ፈት መሆን ተገቢ አይደለም፡፡ ለሥራ የተለየን ነን፡፡ ለቀደሙት ሓዋሪያት የተተወ አይደለም፡፡ የጀመሩትን ሥራ እኛም የምናስቀጥል ነን፡፡ እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 13፡2፡፡
በዚህም ላይ ጨምረን የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን መፅሃፍትን ማንበብ እጅግ ተገቢ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ፍፁምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሃፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16-17፡፡ እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡ ኤፌሶን 2፡1፡፡
በመጨረሻም
- እርስ በርሳችን እንተያ
ምንም እንኳን አንዳንድ ሥራ በግል ደረጃ የሚሰራ ቢሆንም ግን በእግዚአብሔር ቤት ግን ሥራ የሚሰራው በጋራ መሆኑን መካድ የልብንም፡፡ ነህምያ እንዳለ፡- የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን፡፡እኔም ምልሼ፡- የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን… ነህምያ 2፡20፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ ዕብራውያን 10፡24
2. እርስ በርሳችን እንረዳዳ
ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ የአሞን ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ፡፡ 2ኘ ሳሙኤል 10፡11
አይዞህ ስለ ህዝባችንና ስለ አምላካችን ከተሞች እንበርታ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ፡፡ 2ኘ ሳሙኤል 10፡12፡፡
3. ስለ ወንጌል ሁሉን እናድርግ
እርግጥ ነው ወንጌል ስለ ልጁ ስለ ክርስቶስ ነው፤ ስለዚህ ለወንጌል ማህበርተኝነት ራሳችንን መስጠትና ሁሉን ማድረግ አለብን፡፡ በወንጌል ማህበርተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23፡፡
ተባረኩ
አገልጋይ በረከት ሱላሞ ሱጌቦ